
ከ 9 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ህገወጥ” ሲሉ በጠሯቸው ተቃውሞዎች የሚሳተፉ የውጭ አገራት ተማሪዎችን ለህግ እንደሚያቀርቡ እና ከአገር እንደሚያባርሩ አስጠነቀቁ።
ፕሬዚዳንቱ እነዚህን ተቃውሞዎች የሚፈቅዱ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ አቋርጣለሁ ብለዋል።
ትራምፕ ተማሪዎች በህገወጥ መንገድ ተቃውሞ እንዲያደርጉ ለሚፈቅዱ ትምህርት ቤቶች “ሁሉም የፌደራል ፈንድ ይቆማል” ሲሉ ትሩዝ በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ መድረካቸው ላይ ጽፈዋል።
ትራምፕ ይህንን ያሉት እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጦርነት በመቃወም ከፍተኛ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ እና ዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ (ዩሲኤልኤ)ን ጨምሮ በመላው አሜሪካ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ለአመት ያህል መካሄዱን ተከትሎ ነው።
የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን የዘር ጭፍጨፋ በጦር መሳሪያ እና በሌሎች ነገሮች እያገዙ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክናቸውን ዩኒቨርስቲዎች እንዲያቆሙ እየጠየቁ ይገኛሉ።
እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው የሚለውን አትቀበለውም።
ትራምፕ በነዚህ ተቃውሞዎች ላይ የሚሳተፉ አሜሪካውያን ተማሪዎች እንደሚባረሩ አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕን ተቃውሞን “ህገወጥ” የሚያደርጉ ሁኔታዎች ምን እንደሆነ አልገለጹም። በአሜሪካ የትኛውንም ተቃውሞ ማድረግ በህገ መንግሥቱ ፈቃድ ያለው ነው።
የግለሰቦችን ሃሳብ በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የሚሰራው ‘ዘ ፋውንዴሽን ፎር ኢንዲቪዡዋል ራይትስ ኤንድ ኤክስፕረሽን’ የትራምፕን ማስጠንቀቂያ አውግዟል።
- https://www.bbc.com/amharic/extra/diyd5gtsh3/demolished_heritages_amharic
- ዜሌንስኪ በፕሬዚዳንት ትራምፕ “ጠንካራ አመራር” ስር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ5 መጋቢት 2025
- የአረብ መሪዎች ጋዛን መልሶ ለመገንባት 53 ቢሊዮን ዶላር አማራጭ እቅድ አፀደቁ5 መጋቢት 2025
“ኮሌጆች ለህገወጥ ድርጊቶች ምላሽ መስጠት ይችላሉ፤ እንዲሁም አለባቸው። ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ የፌደራል ፈንድን የማቋረጥ ስልጣን የላቸውም፤ ‘ህገወጥ ተቃውሞ’ ለሚፈቅዱትም ጭምር” ሲል መግለጫው አክሏል።
በእስራኤል አና ፍልስጤም ጦርነት ተቃውሞዎችን እያሰሙ ያሉ ተማሪዎች ላይ ድንጋጤን የሚፈጥር እንደሆነ ድርጅቱ አክሏል።
በተያያዘ ዜና የአሜሪካ የትምህርት መምሪያ፣ አጠቃላይ አገልግሎቶች አስተዳደር በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የፌደራል ውሎች ላይ “አጠቃላይ ግምገማ” አካሂዳለሁ ብሏል። ዩኒቨርስቲው በዘር ወይም በብሄር ላይ የተመሰረተ መድልዎን የሚከላከለው የፌደራሉን ህግ እያከበረ መሆኑ ጋር በተያያዘ ምርመራ ተከፍቶበታል።
መስሪያ ቤቱ ከዩኒቨርስቲው ጋር የተገባውን 51.2 ሚሊዮን ዶላር ውል ለማቋረጥ እንዲሁም ለዩኒቨርስቲው የሚሰጠውን 5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚገግም ገልጿል።
“አይሁዳውያን ተማሪዎች ስመ ጥር በሆኑ ዪኒቨርስቲዎች ጥቃቶች እንዲሁም ትንኮሳ ሲደርስባቸው፤ በተደጋጋሚ በጸረ ሴማዊ ተማሪዎች እና ተሟጋቾች ሲተነኮሱ ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ወቅት አሜሪካውያን በፍርሃት ተመልከተዋል” ሲሉ የትራምፕ የትምህርት ሚኒስቴር ጸሀፊ ሊንዳን ማክ ማሆን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም “በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተዘረጉ ህጋዊ ያልሆኑ ድንኳኖች እንዲሁም ተቃውሞዎች የዕለት ተዕለት የካምፓስ ስራዎችን ሙሉ ለሙሉ ሽባ አድርገዋል። በዚህም የአይሁዳዊ ተማሪዎች የመማር መብታቸውን እድል ነፍገዋቸዋል” ብለዋል።
በመላው አሜሪካ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች የፍልስጤም ድጋፎች እየተቀጣጠሉ እና በግቢዎቻቸው ውስጥ ድንኳን አድረው ሌት ተቀን የሚቃወሙ ተማሪዎች ታይተዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በያሊ እና በሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች ታስረዋል። አንድ ዩኒቨርስቲም በድጋፍ ሰልፉ የተነሳ ሲዘጋ ስመ ጥሩው ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ወደ ግቢው መግባት ላይ ገደብ ጥሎ ነበር።
ትራምፕ በጥር ወር ላይ በተቃውሞ ሰልፎች የሚሳተፉ የውጭ አገር ተማሪዎች እንዲባረሩ የሚጠይቅ የስራ አስፈጸሚ ትዕዛዝን ፈርመዋል።
ትዕዛዙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለትምህርት ተቋማቱ “በውጭ ተማሪዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን እንዲከታተሉ እና ሪፖርት እንዲያደርጉ እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ እንዲያባርሯቸው” የሚያስችላቸውን ምክሮች እንዲያቀርቡ መመሪያ ሰጥቷል።