
5 መጋቢት 2025, 08:10 EAT
የአረብ አገር መሪዎች “ጋዛን በመውሰድ” እና ሁለት ሚሊዮን ፍልስጤማዊያንን የሚያፈናቅለውን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ሀሳብ የሚቀናቀን የ53 ቢሊዮን ዶላር የመልሶ ግንባታ እቅድ ግብፅ ካይሮ ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ አፅድቀዋል።
የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አሕመድ አቡል ጊቲ ሰዓታት ከዘለቀው ስብሰባ በኋላ “የግብፁ እቅድ አሁን የአረብ እቅድ ነው” ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ትራምፕን ጋዛን የመገንባት ሀሳብ በደፈናው ሳይጠቅሱ የአረብ አቋም የፈቃደኝነትንም ሆነ የግዴታ መፈናቀልን የማይደግፍ” እንደሆነ አስምረዋል።
ግብፅ የአሜሪካን እቅድ የሚቀለብስ 91 ገፆች ያሉት ሰነድ በዛፎች የተከበቡ የመኖሪያ መንደሮችን እና ታላላቅ የህዝብ ህንፃዎችን የያዘ “የመካከለኛው ምስራቅ ሪቪዬራ” የሚል ስያሜ የሰጠችውን ዝርዝር የግንባታ እቅድ አቅርባለች።
ይህን አዲሱን እቅድ ልዩ የሚያደርገው የህንፃዎች ግንባታ ብቻ አለመሆኑ ሲሆን እቅዱ ፖለቲካዊ እና ለፍልስጤማዊያን የመኖር መብትን ለመስጠት ያለመ ነው።
የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ በመክፈቻ ንግግራቸው ከአካላዊ ግንባታ እቅዱ መሳ ለመሳ የሚሄድ የሁለት አገራት መፍትሄ እየተባለ ወደ ሚጠራው የመፍትሄ ሽግግር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ መፍትሄ በሰፊው የአረብ አገራት እና በሌሎችም አብዛኞቹ አገራት ሊቆም ላልቻለው ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ተደርጎ ይታያል። ነገር ግን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ እና አጋሮቻቸው በፅኑ ይቃወሙታል።
አዲሱ እቅድ ጋዛ በጊዜያዊነት ብቁ ከሆኑ ባለሙያዎች የተውጣጣ “በፍልስጤም የጋዛ አስተዳደር ኮሚቴ” በተባለ አስተዳደር እንደሚመራ አስቀምጧል።
- ዜሌንስኪ በፕሬዚዳንት ትራምፕ “ጠንካራ አመራር” ስር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩከ 8 ሰአት በፊት
- በዓለም ላይ በርካታ ሰዎች በሽብር ጥቃት የሚገደሉበት የአፍሪካ የሳህል አካባቢከ 9 ሰአት በፊት
- በዲሞክራቲክ ኮንጎ ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ከ50 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተሰማ4 መጋቢት 2025
እቅዱ ሀማስ ሊጫወተው ስለሚችለው ሚና ጉዳይ ሸፋፍኗል። ታጣቂ ቡድኑ ሊያደርሰው ስለሚችል “መሰናከል” በግልፅ ሳይጠቅስ፤ የእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት ምንጭ ከተወገደ ጉዳዩ መፍትሄ ያገኛል ይላል።
አንዳንድ የአረብ አገራት ሀማስ ሙሉ ለሙሉ ትጥቁን እንዲፈታ ጥሪ በማድረግ የሚታወቁ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ይህ ውሳኔ ለፍልስጤማዊያን የተተወ ነው ብለው ያምናሉ።
ሀማስ በጋዛ መልሶ ግንባታ ምንም ሚና እንደማይጫወት መቀበሉ እየተነገረ ሲሆን፤ ትጥቅ መፍታት ግን ቀይ መስመሩ ነው ተብሏል።
የፕሬዝዳንት ትራምፕን እቅድ “አርቆ አሳቢ” ሲሉ የገለፁት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የፍልስጤምን አስተዳደር ጨምሮ ሀማስ በቀጣይ የሚኖረው ሚናን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል።
ደኅንነትን በሚመለከት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪዎችን ለማሰማራት በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት እንዲቀርብ ሆኗል።
ለመልሶ ግንባታ መርሃ ግብሩ አስፈላጊ ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚቀጥለው ወር ትልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ይካሄዳል።
ባለፀጋ የገልፍ አገራት ለግንባታው ግዙፉን በጀት ለመሸፈን ፈቃደኛ ናቸው። ነገር ግን አንዳንዶች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ በሌላ ጦርነት ህንፃዎቻቸው እንደማይወድሙ ሙሉ በሙሉ እምነት ስላላደረባቸው ዝግጁ አይደሉም።
ያልፀናው የተኩስ አቁም ስምምነት ለመጣስ ጫፍ ላይ መሆኑ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ እያደረጋቸው ነው።
ጋዛን ለመገንባት በወጠነው አዲሱ የአረብ እቅድ ግዙፍ ፍርስራሾችን እና ያልመከኑ ፈንጅዎችን ማስወገድን የያዘ ቅድመ ማገገሚያ የስድስት ወራት ማስጀመሪያ ጊዜን ጨምሮ በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚፈፀም ነው።
በመልሶ ግንታው ጊዜ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ተፈናቃይ ፍልስጤማዊያን በጊዜያዊ መጠለያዎች ይቆያሉ ተብሏል።
የመንግሥታቱ ድርጅት በጋዛ 90 በመቶ ቤቶች ወድመዋል አሊያም ጉዳት ደርሶባቸዋል ይላል።