
ከ 3 ሰአት በፊት
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳን ወክለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ፤ ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር እስር በኋላ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ከእስር ተፈቱ።
“ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በአመጽ ለመናድ” በመንቀሳቀስ ተከስሰው የነበሩት የምክር ቤት አባሉ፤ ከእስር የተፈቱት ክሳቸው ተቋርጦ መሆኑን ጠበቃቸው አቶ ጌድዮን ቦጋለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጉራጌ ዞን በክልልነት እንዲደራጅ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የሚታወቁት የተቃዋሚው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተወካይ አቶ ታረቀኝ፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. ነበር።
አቶ ታረቀኝ ከመታሰራቸው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ አባል የሆኑበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ ያለመከሰስ መብታቸውን አንስቶ ነበር።
የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብት የተነሳው “በከባድ ወንጀል ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በአመጽ ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ነበር።
አቶ ታረቀኝ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐዋሳ ምድብ ችሎት ስር በሚገኘው የወልቂጤ ከተማ ተዘዋዋሪ ችሎት የቀረበባቸው ክስም ይኸው ነበር።
ጠበቃቸው አቶ ጌድዮን እንደሚያስረዱት አቶ ታረቀኝ እና አቶ ሐይደር ሙራድ የተባሉ ሌላ ግለሰብ ፍርድ ቤት የቀረቡት፤ በ2014 ዓ.ም. በ21 ሰዎች በተመሠረተ ክስ ውስጥ ተካትተው ነው።
- በቱኒዝያ የባህር ዳርቻ በነዳጅ ማቀነባባሪያ ለበርካታ ቀናት ያለ እርዳታ የቀሩ ስደተኞች ተገኙከ 7 ሰአት በፊት
- ዜሌንስኪ በፕሬዚዳንት ትራምፕ “ጠንካራ አመራር” ስር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩከ 9 ሰአት በፊት
- ትራምፕ “በህገ ወጥ ተቃውሞ” የሚሳተፉ የውጭ አገራት ተማሪዎችን ከአገር እንደሚያባርሩ ተናገሩከ 8 ሰአት በፊት
ባለፈው ዓመት በዚህ መዝገብ ውስጥ ከተካተቱት ሁለቱ ግለሰቦች ውጪ ያሉት ሌሎቹ ተከሳሾች በ2015 ዓ.ም. በዋስትና ተለቅቀው የነበረ በመሆኑ ክሳቸውን ሲከታተሉ ከእስር ቤት ውጪ ሆነው ነው።
በእነ አቶ ታረቀኝ መዝገቡ ውስጥ ከተካተቱ በኋላም የክስ ሂደቱ የቀጠለ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ “ከአስር በላይ ምስክሮችን ማሰማቱን” ገልጸዋል።
የመጨረሻው የፍርድ ቤት ውሎ የተካሄደው ከአንድ ወር በፊት ጥር 26/2017 ዓ.ም. እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ጌድዮን፤ ለመጋቢት 1 ቀጠሮ ተሰጥቶ እንደነበረም ጠቅሰዋል።
ለሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ቀጠሮ ተሰጥቶ የነበረው ጠበቃ “ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የሰነድ ማስረጃ ላይ የሚሰጠውን አስተያየት ለመስማት” ነበር።
ዐቃቤ ሕግ እና ጠበቃው ክርክር ባደረጉበት፤”ምስክሮች ለፖሊስ የሰጡት ቃል በማስረጃነት እንዲያዝለት” በዐቃቤ ሕግ በቀረበ ጥያቄ ላይ ብይን መስጠትም ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ የሰጠበት ሌላኛው ጉዳይ ነበር።
ነገር ግን ዐቃቤ ሕግ ሰኞ የካቲት 24/ 2017 ዓ.ም. የምክር ቤት አባሉ የአቶ ታረቀኝን ጨምሮ በመዝገቡ ውስጥ ተካተቱትን 23 ግለሰቦች ክስ ማቋረጡን ጠበቃው አቶ ጌድዮን ገልጸዋል።
በእስር ላይ ነበሩት አቶ ታረቀኝ እና አቶ ሐይደርም ክሱ በተቋረጠበት ዕለት ሰኞ ከእስር መለቀቃቸውን አስታውቀዋል።
የምክር ቤት አባሉ አቶ ታረቀኝ ከአንድ ዓመት ከሁለት ወራት እስር በኋላ ከቤተሰባቸው ጋር መቀላቀላቸውንም አክለዋል።
