ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) እና አቶ ካሳሁን ጎንፋ ትምህርት በቴሌቪዥን ሥርጭቱን አስመልክቶ የሥራ ስምምነት ተፈራርመዋል

ማኅበራዊ አጋዥ የሒሳብና የእንግሊዝኛ ትምህርቶች በቴሌቪዥን መሠራጨት ሊጀምሩ ነው ትምህርቶቹ በማኅበራዊ ሚዲያ…

ምሕረት ሞገስ

ቀን: March 5, 2025

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በመተባበር ‹‹ተማሪዎችን በሒሳብና በእንግሊዝኛ ትምህርት ውጤታማ ያደርጋል››ያለውን የትምህርት በቴሌቪዥን ፕሮግራም ሥርጭት ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደሚያስጀምር አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ሥርጭትቱን አስመልክተው እንዳሉት፣ ቢሮው የተማሪዎችን የሒሳብና የእንግሊዝኛ ትምህርት ውጤት ለማሻሻል 13 ግቦችንና 31 ዋና ዋና ተግባራትን ያካተተ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ ሲሆን፣ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በመተባበር የሚጀምረው የትምህርት በቴሌቪዥን ፕሮግራምም የዚሁ ስትራቴጂ አካል ነው፡፡

በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ‹‹AMN ፕላስ›› የቴሌቪዥን ቻናል መተላለፍ በሚጀምረው የትምህርት ፕሮግራም፣ ከ4ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ሒሳብ በአማርኛ፣ ከ4ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ሔሬጋ (ሒሳብ በአፋን ኦሮሞ)፣ ከ7ኛ እስከ 8ኛ ሒሳብ እንዲሁም ከ4ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የእንግሊዝኛ ትምህርት የሚሰጥ ይሆናል፡፡

በሳምንት 30 ክፍለ ጊዜ ሥርጭት ሲኖር፣ የትምህርት ሥርጭቱ ከቴሌቪዥን ባሻገር በትምህርት ቢሮና በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች እንደሚተላለፍ ተገልጿል።

የቴሌቪዥን ትምህርቱ ውጤታማ እንዲሆን ቢሮው ከአዲስ ሚዲያ ጋር በመሆን ኮሚቴ በማዋቀር፣ በትምህርት ዓይነቶቹ ብቁ የሆኑ መምህራንን በመመልመልና የትምህርቶቹን ይዘቶች በማዘጋጀት ወደ ቀረፃ መግባቱን ዘላለም (ዶ/ር) ገልጸው፣ ተማሪዎች የቴሌቪዥን ትምህርቱን በንቃት እንዲከታተሉ ወላጆችን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የቴሌቪዥን ትምህርቱ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ‹‹AMN ፕላስ›› ቻናል ከሰኞ እስከ ዓርብ ከ11፡00 እስከ 12 ሰዓት እንዲሁም ዘወትር ቅዳሜና እሑድ ከጥዋቱ 2፡00 ሰዓት እስከ 6፡00 ሰዓት የሚተላለፍ መሆኑንም የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ጎንፋ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም (ዶ/ር) እና የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን በዕለቱ ትምህርት በቴሌቪዥን ሥርጭቱን አስመልክቶ የሥራ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ኢትዮጵያ የትምህርት በቴሌቪዥን ሥርጭት የጀመረችው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመርያ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. 1960ዎች ብዙዎቹ የዓለም አገሮች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ድጋፍ ትምህርት በቴሌቪዥን የጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡ ኢትዮጵያም የዚሁ አንድ አካል ናት፡፡

የትምህርት በቴሌቪዥን የማጠናሪያ ፕሮግራም በደርግ ዘመን በኋላም በኢሕአዴግ በ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ሁሉም ትምህርት በፕላዝማ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ጊዜም አጋዥ ትምህርት በቴሌቪዥን ይሠራጭ እንደነበር ይታወሳል፡፡