https://www.ethiopianreporter.com/138911


የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት

ማኅበራዊ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ ክፍያ አልተፈጸመልንም አሉ

የማነ ብርሃኑ

ቀን: March 5, 2025

በፌዴራል መንግሥት ከጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ከተፈቀደው የደመወዝ ማስተካከያ ክፍያ የሁለት ወራት አልተፈጸመልንም ሲሉ፣ በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፓዌ ወረዳ የፓዌ መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ትዕዛዙ ወልደ ማርያም፣ መንግሥት የኑሮ ውድነትን ታሳቢ በማድረግ በመላ ኢትዮጵያ ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ከጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግ መፍቀዱን አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም የክልሉ መንግሥት መመርያውን ወደኋላ በመተው፣ ከታኅሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ክፍያ እንዲፈጸም መመርያ በማውጣት የጥቅምትና የኅዳር ወራት የደመወዝ ማስተካከያ ክፍያ እንዳናገኝ ተደርገናል በማለት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡  

‹‹የደመወዝ ማስተካከያ ከተደረገ በኋላ በአንድ ዓመት ውስጥ ሌላ ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅም ማግኘት አይቻልም የሚል መመርያ በማውጣት፣ ቀደም ሲል በትምህርት ሚኒስቴር ተፈቅዶልን የነበረውን የደረጃ ዕድገትና የዕርከን ጭማሪም እንድናጣ ተደረገናል፤›› ያሉት መምህሩ፣ ‹‹ይህም የተጣለብንን አገራዊ ኃላፊነት እንዳንወጣ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድርና የሥራ ተነሳሽነታችንን የሚጎዳ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ የመንግሥት ቢሮዎች ውስጥ በአንዱ በማገልገል ላይ መሆኗንና ስሟ እንዳይለገጽ የፈለገች አስተያየት ሰጪ ለሪፖርተር እንደተናገረችው፣ በአገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ከጥቅምት ወር ጀምሮ የደመወዝ ማስተካከያ ክፍያ ሲፈጸምላቸው፣ በክልሉ የሚገኙ ሠራተኞች ግን ከታኅሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ክፍያ የተፈጸመላቸው፡፡ ‹‹የጥቅምትና የኅዳር ማስተካከያ ክፍያ እንደማናገኝ ተነግሮናል፤›› ብላለች፡፡

‹‹የኑሮ ውድነቱ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ተመሳሳይ በሆነበት በዚህ ጊዜ፣  በመንግሥት የተወሰነን የኑሮ መደጎሚያ የደመወዝ ማስተካከያ ክፍያ መከልከል በምንም ሁኔታ አግባብ አይሆንም፤›› ያለችው አስተያየት ሰጪዋ፣ ‹‹ድርጊቱ የመንግሥት ሠራተኞችን ያሳዘነና ሞራላችንንም የነካ ነው፤›› በማለት አስረድታለች፡፡

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፌዴራል መንግሥት በጥቅምት 2017 ዓ.ም. ለመንግሥት ሠራተኞች ያደረገውን የደመወዝ ማስተካከያ ክፍያ የክልሉ ካቢኔ ከታኅሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲከፈል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ‹‹ክልሉ የሁለት ወራት ክፍያ ለመፈጸም ለምን ፈቃደኛ እንዳልሆነ እኛም ሊገባን አልቻለም፤›› ብለዋል፡፡

መብራቱ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ከፌዴራል መንግሥት የሚመጡ መመርያዎችን የክልሉ መንግሥት መሻር አይችልም፡፡ የክልሉ መንግሥት ገንዘቡን ለኮሪደር ልማት ሊያውለው ፈልጎ፣ ወይም በጀት የለም በሚል ምክንያት እንዳስቀረው ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸው፣ ድርጅታቸው ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ውሳኔው ተገቢነት አለው ብሎ እንደማያምንም ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂና ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግሥት ደቢሳ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በእጅ ስልካቸው በተደጋጋሚ ቢደወልና በአጭር የጽሑፍ መልዕክት (ኤስኤምኤስ) ለማግኘት ጥረት ቢደረግም፣ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡