

የዓለም የዱር እንስሳት ቀን በጉለሌ ዕፀዋት ማዕከል ተከብሯል
ማኅበራዊ ፈተና ያልተለየው የዱር እንስሳት ሀብት
ቀን: March 5, 2025
የዱር እንስሳት ሀብት ለሰው ልጆችና ለምድር ህልውና በጣም ወሳኝ ለሆኑት ንፁህ አየር፣ ውኃና ለም አፈር ጥበቃ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም፣ በጥብቅ ቦታዎች ውስጥ የሚታየው ቸልተኝነትና ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ ሥጋት ውስጥ በመግባቷ የዱር እንስሳት ሀብት ከጊዜ በኋላ ውጤት አልባ እየሆነ መጥቷል፡፡
ፓርኮች፣ እንስሳት፣ ዕፀዋትና የጥበቃ ቦታዎች በሚገባ የማይጠበቁና እንክብካቤ የማያገኙ በመሆኑም፣ ሕገወጥ ሰፈራ፣ ንግድ እንዲሁም ልቅ ግጦሽ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንደገለጹት፣ እ.ኤ.አ. 2030 የምድሪቱን የዱር እንስሳት ጥበቃ ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው፡፡
በየዓመቱ የሚከበረው የዓለም የዱር እንስሳት ቀን የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ታስቦ በዋለበት ሥነ ሥርዓት ላይ ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፣ ለዱር እንስሳት ጥበቃ የሚሆን የዓለም የደን ጥበቃ ቦታ ሽፋን በአማካይ 17 በመቶ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደግሞ 14 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡
የምድሪቱ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታ ሽፋንን እ.ኤ.አ በ2030፣ 30 በመቶ ማድረስ ካልቻለ ለሰው ልጅ ጤና ጠንቅ የሆኑ ክስተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ በቀጣይም የኢትዮጵያን የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታ የደን ሽፋን ከፍ በማድረግ ለዓለም የዱር እንስሳት ጥበቃ ሽፋን አስተዋጽኦ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታዎች ሥራ ማከናወኛ 800 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀት ሲታይ ግን በዓመት ከሦስት ሚሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ፣ በተለያዩ የጥብቅ ቦታዎች ውስጥ መሠረተ ልማቶችን ያካተተ ሥራ ለመሥራት ካስፈለገ በጀቱ ወደ 300 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ፣ የበጀት ክፍተቱን ለመሙላት በዱር እንስሳት ጥበቃ ላይ ከተሰማሩት ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ተገቢው ድጋፍና ትብብር በመደረግ ላይ ነው፡፡
ከዚህም ሌላ የኮንሰርቬሽን ትረስት ፈንድ ተረቅቆ ለመንግሥት መቅረቡን፣ በቅርቡም ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅና ከፀደቀ የበጀት ክፍተቱን ለመሙላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የበርካታ የዱር እንስሳት ባለቤት ብትሆንም ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ የተነሳ በሚፈለገው መልክ ተጠቃሚ አልሆነችም ብለዋል፡፡
ካለፉት የለውጥ ዓመታት ወዲህ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኝ በስፋት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ከተከናወኑትም ሥራዎች መካከል የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ አንዱ መሆኑንና ይህም መንግሥት ብቻውን ይሠራ የነበረውን ዘርፍ የግል ባለሀብቱ እንዲሳተፍበት ማድረጉን ለአብነት አውስተዋል፡፡
‹‹ፋይናንስ ለዱር ሕይወት ጥበቃ፣ ለሰዎችና ለፕላኔቶች ደኅንነት›› በሚል ርዕስ ታስቦ የዋለው ይህ የዓለም የዱር ሕይወት ቀን፣ በኢትዮጵያ የሚኙ የዱር እንስሳትንና የመኖሪያ አካባቢያቸውን በመጠበቅና በማልማት ኢትዮጵያ ከዘርፉ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የምታገኝባቸውን አማራጮች ለማስፋት ነው፡፡
ከዚህም ሌላ ማኅበረሰቡን ባሳተፈና ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ሥነ ምኅዳራዊ ሀብት ተጠብቆ ለትውልድ የሚተላለፉበትን ዓውድ ለመፍጠር ለዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ምቹ መዳረሻና አማራጭ በመሆን ለቱሪዝም ዕድገት ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳየት ያለመ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
