አበበ ፍቅር

March 5, 2025

ምን እየሰሩ ነው?

ቀደም ሲል የቤተሰብ ጤና አገልግሎት ኃላፊነት ለቤተሰብ ጤና መምርያ ብቻ የተጣለ ነበር:: ነገር ግን ከ1992 ዓ.ም. ወዲህ በርካታ ድርጅቶች በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ በስፋት መሥራት ጀመሩ፡፡ በወቅቱ የተለያዩ ድርጅቶች የተመሠረቱ ቢሆንም፣ በተናጠል በመሥራታቸው በሚፈለገው ልክ ውጤት አላስመዘገቡም ነበር፡፡ ጉዳዩ ተደማጭነት እንዲያገኝ ውጤታማ ይሆን ዘንድ በ1993 ዓ.ም. ኮንሰርቲየም ኦፍ ፋሚሊ ፕላኒንግ በሚል የተለያዩ ድርጅቶችን ያቀፈ ድርጅት ተቋቋመ፡፡ በ1994 ዓ.ም. ደግሞ ኮንሰርትየም ኦፍ ሪፕሮዳክቲቭ ሄልዝ አሶሲየሽንስ በሚል ተቋቁሞ በጤና ዙሪያ መሥራት ጀመረ፡፡ አቶ አበበ ከበደ የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ አበበ ፍቅር አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ምን ያህል ድርጅቶችን በአባልነት ያቀፈ ነው? በምን ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጋችሁ ትሠራላችሁ?

አቶ አበበ፡- በአሁኑ ወቅት 88 የሚደርሱ ዓለም አቀፍና አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በአባልነት ያቀፈ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅታችን በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ በእናቶችና ሕፃናት ጤና አጠባበቅ፣ በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ሥነ ተዋልዶ ጤና፣ በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትና በኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል፡፡ ከዚህ ባሻገር በሥርዓተ ፆታ ላይም የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በዋናነት የተቋቋማችሁበት ዓላማ ምንድነው?

አቶ አበበ፡- ስንቋቋም የተሰጠን መመርያ አለ፡፡ ይህም በመጀመሪያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር አንዳንድ መመርያዎች እንዲሻሻሉ፣ የሚወጡ ፖሊሲዎች ላይ አስተያየት በመስጠት እንዲሻሻሉ ተፅዕኖ መፍጠር ነው፡፡ ለአባሎቻችን የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠትና ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ መሥራትም ከዓላማዎቻችን ይጠቀሳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለሥራችሁ ፈተና የሆነባችሁ ነገር ምንድነው?

አቶ አበበ፡- የመጀመርያው በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኩል የአቅም ውስንነት መኖሩ ነው፡፡ ሌላው ከድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር መረጃዎችን ለማግኘት በምንሠራበት ወቅት ከተዛቡ አመለካከቶች በመነሳት ትክክለኛውን መረጃ አለመስጠት ነው፡፡ የብሔር ቁጥርን ለመቀነስ በሚል የተሳሳተ አመለካከት መረጃዎችን ማጥፋት ይገጥመናል፡፡  የሥነ ተዋልዶ ጤና ፍላጎት እያደገ ሲመጣ፣ አቅርቦት አብሮ አለማደግና በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ድርጅቶች በየአካባቢያቸው ተዟዙረው ለመሥራት መገደባቸው እየገጠሙን ካሉ ችግሮች መካከል ናቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- ዩኤስኤአይዲ የሚያደርገውን ድጋፍ አቁሟል፡፡ የድጋፉ መቆም በተለይ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ምንድነው?

አቶ አበበ፡- በዩኤስኤአይዲ ከሚደገፍ ድርጀቶች የተለያዩ መረጃዎች እያሰባሰብን ነው፡፡ ድጋፉ በመቋረጡ ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት ለመጠየቅም ሞክረን ነበር፡፡ የአንዳንዶቹ መረጃ እንደሚያሳየው የድጋፉ መቋረጥ ከፍተኛ የሆነ ችግር ይፈጥራል፡፡  አንዳንዶቹ በኤችአይቪ/ኤድስ ላይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በርካታ ሠራተኞቻቸውን የሚያሰናብቱበት ሁኔታ አለ፡፡

ለምሳሌ አንድ ተጨባጭ የሆነ መረጃ ብጠቀስልህ አንድ ድርጅት ከ21 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና የንፁህ ውኃ አቅርቦትና የተለያዩ የጤና አገልግሎቶችን የሚሰጥ ነበር፡፡ የዚህ ድርጅት ድጋፍ በመቋረጡ አገልግሎት መስጠት ለማቆም ተገዷል፡፡ ከኤችአይቪ ኤድስ ጋር በተያያዘ ለአራት ሺሕ ወጣቶች የሚሰጡት አገልግሎት ይቋረጣል፡፡ አንድ ድርጅት 75 በመቶ የሚሆነው በጀቱ የሚደገፈው በዩስኤአይዲ ስለነበር ድጋፉ በመቋረጡ ብዙ ሠራተኞችን ከሥራ  አሰናብቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የዩኤስኤአይዲ ድጋፍ ከመቋረጡ ጋር ተያይዞ የተጠናከረ መረጃ አላወጡም ለምንድነው?

አቶ አበበ፡- ዕግዱ 90 ቀን ስለተባለ ብዙዎች ያንን ተስፋ አድርገው ስለሚጠይቁ ነው፡፡ በሌላ በኩል መረጃውን እንዳይሰጡ በተለያዩ አካላት ስለሚከለክሉ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ የድጋፍ መቋረጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ማኅረበሰቡን የሚጎዳ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሮችን ለመፍታት ድርጅቶች ምን ማድረግ አለባቸው?

አቶ አበበ፡- ችግሩ በጣም ሰፊ ከመሆኑ አንፃር ከመንግሥትና ከሌሎች አገሮች ጋር በመሆን ምን እናድርግ በሚለው ላይ ለመወየትና ለመመካከር እየሠራን ነው፡፡ ያለንን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም መሞከር ሌላው መፍትሔ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለወጣቶችና ለአፍላ ወጣቶች በአጠቃላይ ለማኅበረሰቡ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በምን መልኩ ነው እየሰጣችሁ ያላችሁት?

አቶ አበበ፡- የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ተደራሽ ለመሆን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ሁሉንም ማኅበረሰብ ተደራሽ የሚያደርግ የኔ ታብ (Yene Tab) የሚል የሞባይል መተግበሪያ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን አዘጋጅተናል፡፡ መተግበሪያው በስድስት የአገር ውስጥ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚህ በተለይ ወጣቱ ክፍል ከቴክኖሎጂ ጋር ባለው ቅርበት ሙሉ በሙሉም ባይሆንም የመነሻ ሐሳቦችን ያስገኛል ብለን እናስባለን፡፡ በተዘጋጀው መተግበሪያ ወጣቶች የአቻ ግፊትን እንዴት መከላከል እንዳለባቸ፣ ስለጤናማ ግንኙነት፣ ስለ ኮንዶም አጠቃቀምና ሌሎችንም የምክር አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ዓመታዊ ኮንፈረንስ ለማድረግ ዕቅድ ይዛችኋል? በኮንፈረንሱ ምን ዓይነት ሐሳቦች ይነሳሉ?

አቶ አበበ፡- በኮንፈረንሱ በጤናው ዘርፍ ላይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በስፋት ይነሳሉ፡፡ እኛም እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምን ምን ጉዳዮችን ማንሳት አለብን የሚሉትን ጉዳዮች በማንሳት እንወያያለን፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ በዩኤስኤይዲ በኩል ይሰጥ የነበረ ድጋፍ ቆሟል፡፡ በድርጅቱ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሲረዳ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ድጋፉ ሲቆም ምንድነው መሠራት ያለበት? ብለን አማራጮችን ማየትና መፈለግ አለብን? ወይስ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ ነው ያለብን? የሚሉትን ጉዳዮች በስፋት ማየት ይኖርብናል፡፡ በሌላ በኩል በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረት አድርገን እንወያያለን፡፡ ከዚህ ባሻገር የጤና ተደራሽነትና ፍትሐዊነትን በተመለከተ የተሠሩ ሥራዎችና ምን ላይ ናቸው የሚሉትን ጉዳዮች በማንሳት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከውይይቱ በኋላ ምን ይጠበቃል?

አቶ አበበ፡- ከውይይቱ የሚወጡ ሐሳቦችን በመሰነድ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት እንዲሠሩባቸው ምክረ ሐሳቦች እንሰጣለን፣ ያሉ ክፍተቶችንም እናሳያለን፡፡ መንግሥት ለሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የሚሰጠውን ገንዘብ እንዲጨምር የማድረግና ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ትኩረት የምንሰጠው ይሆናል፡፡