
March 5, 2025
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጀት ጠቅላላ ገቢ በ12 ቢሊዮን ብር ዝቅ ቢልም፣ ትርፉ በአራት እጥፍ ከፍ ማለቱ ታወቀ፡፡

እስመለዓለም ምሕረት
ድርጅቱ የ2016 ዓ.ም. (June 30, 2024) ኦዲት ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ በድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እስመለዓለም ምሕረት የፀደቀው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡
በዓመቱ የድርጅቱ የነዳጅ ሽያጭ ገቢ ዓምና ከነበረበት 271 ቢሊዮን ብር ወደ 259 ቢሊዮን ብር ወርዷል፡፡
ይሁን እንጂ ድርጅቱ ቅናሹን በተለያዩ መንገዶች በማካካስ፣ ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡ አንደኛው መንገድ ወጪን መቀነስ ሲሆን፣ በተለይ ከሽያጭ ጋር የተገናኙ ወጪዎችን በማሻሻልና በመቆጣጠር፣ ወጪውን ከነበረበት 255 ቢሊዮን ብር ወደ 246 ቢሊዮን ብር በማውረድ ወደ ስምንት ቢሊዮን ብር ገደማ ሊያድን ችሏል፡፡
ሌላው ማካካሻ መንገድ በተለይ መንግሥት የነዳጅ ድጎማን በሒደት በማንሳቱ የመጣ ተጨማሪ ትርፍ ነው፡፡ በዚሁም ድርጅቱ ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር ገደማ ሊያተርፍ ችሏል፡፡ በ2015 ዓ.ም. ድርጅቱ ለነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ 15 ቢሊዮን ብር የከፈለ ሲሆን፣ ድጎማው በከፊል በመነሳቱ በ2016 ዓ.ም. ግን ድርጅቱ 12 ቢሊዮን ብር ብቻ ለነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ከፍሏል፡፡
ድርጅቱ ከሌሎች ምንጮች ያገኛቸው ገቢዎች ተደምረውና የታክስ ገቢ ተቀንሶ በ2016 ዓ.ም. ያስመዘገበው ንፀህ ትርፍ 994 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ዓምና ከነበረበት 236 ሚሊዮን ብር በአራት ዕጥፍ ከፍ ብሏል፡፡
በሌላ በኩል የድርጅቱ ጠቅላላ ሀብት ዓምና ከነበረበት 225 ቢሊዮን ብር፣ በከፍተኛ ቁጥር ቀንሶ ወደ 190 ቢሊዮን ብር ወርዷል፡፡ ይህም በተለይ በነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንዱ ተመላሽ የሚሆንለት ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ እንደሆነም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ፈንዱ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የነዳጅ ዋጋ ልዩነት የማጣጣም ሚና ይወጣል፡፡
በሌላ በኩል የድርጅቱ ጥሬ ገንዘብና ገንዘብ ነክ ሀብት ዓምና ከነበረበት 60 ቢሊዮን ብር ባለፈው ሰኔ 100 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ድርጅቱ በ2016 ዓ.ም. ያስመዘገበውን ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ንፁህ ትርፍ፣ ለመንግሥት ገቢ ድርሻ (State Dividend) ማስተላለፉን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
