ዳዊት ታዬ

March 5, 2025

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተለያዩ ዘርፎች ለሚሰጠው ብድር ያስከፍል በነበረው የብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ከግብርና ዘርፍና ኮንዶሚኒየም ቤቶች በስተቀር በሁሉም ብድሮች ላይ ጭማሪ ማድረጉን አስታወቀ::

ከኮንዶሚኒየም ቤቶችና ግብርና ዘርፍ በስተቀር የብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ጭማሪ ማድረጉን ንግድ ባንክ አስታወቀ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር ወለድ ምጣኔ ማሻሻያ ስለማድረጉ ትናንት ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ከግብርና ዘርፍና ከኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች በስተቀር በሌሎች ዘርፎች ብድሮች ላይ ያስከፍል በነበረው የብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ጭማሪ መደረጉን አመልክቷል:: በተለይ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር የተያያዘ ግንኙነት ያላቸው ድርጅት ሠራተኞች፣ በማሻሻያው ይከፍሉ የነበረው የብድር ወለድ ምጣኔ ከፍተኛ የሚባል ጭማሪ የተደረገበት ስለመሆኑ ታውቋል::

የውጭ ምንዛሪ ለሚያቀርቡ የድርጅት ሠራተኞች የሚሰጡ የግል ብድሮች፣ በስምምነት ውሉ ላይ የተመሠረቱትም ሆነ ያልተመሠረቱት ብድሮች ከዚህ ቀደም ይከፈልበት ከነበረው የሰባት በመቶ ወለድ አሁን አሥራ አንድ፣ አሥራ ሁለትና አሥራ ሦስት በመቶ የብድር ወለድ ይከፈልባቸዋል ተብሏል:: ይህም በዚህ ዘርፍ የተደረገው የወለድ ጭማሪ በመቶ ሲሰላ 57፣ 71 እና 85 በመቶ መሆኑን ያመለክታል::

በዚሁ ዘርፍ Personal Loan Employees or Exceptionally Big Value Customers ብሎ ላስቀመጣቸው የረዥም ጊዜ ተበዳሪዎች ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም ሲያስከፍል የነበረውን 12 በመቶ በዚያው መጠን እንዲቀጥል መደረጉን አስታውቋል::

ከየካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ በሚደረገው የባንኩ የብድር ወለድ ምጣኔ ማሻሻያ መሠረት፣ ከፍተኛ ጭማሪ ተደርጎበታል የተባለው ለማክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚሰጠው ብድር ላይ ነው::

በመረጃው መሠረት የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከባንኩ ለሚበደሩት የአጭር ጊዜ ብድር እስካሁን ሲከፍሉ የነበረው የብድር ወለድ ምጣኔ 11.50 በመቶ ነበር:: በተሻሻለው ዋጋ መሠረት ግን ተቋማቱ ለአጭር ጊዜ ለሚወስዱት ብድር ከዚህ በኋላ መክፈል የሚጠበቅባቸው የብድር ወለድ ምጣኔ 14 በመቶ ሆኗል:: ይህም በአንድ ጊዜ የ2.5 በመቶ ጭማሪ መደረጉን ያመለክታል::

እነዚሁ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለመካከለኛ ጊዜ ለሚበደሩት ብድር ከዚህ በኋላ መክፈል የሚጠበቅባቸው የብድር ወለድ ምጣኔ 14.50 በመቶ ሆኗል:: እስካሁን ለመካከለኛ ጊዜ ብድር ሲከፍሉ የነበረው የብድር ወለድ 12.00 ነበር:: 12.50 በመቶ የብድር ወለድ ምጣኔ ይከፍሉበት የነበረው የረዥም ጊዜ ብድር ደግሞ አሁን ወደ 15.50 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉ ታውቋል::

ለማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለሚሰጠው ብድር የረዥም ጊዜ ብድር የሚጠየቀው የብድር ወለድ ምጣኔ ከ12.50 በመቶ ወደ 15.50 በመቶ ማደጉ በመቶኛ ሲሰላ 24 በመቶ ጭማሪ መደረጉን ያመለክታል::

ከወጪ ንግዱ ጋር የተያያዙ የብድር ወለዶችም ከፍተኛ ለውጥ የተደረገባቸው ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍ የተደረገው ጭማሪ እስከ ሦስት በመቶ የሚደርስ ነው:: በዚህም መሠረት ለወጪ ንግድ ተበዳሪዎች ከዚህ ቀደም ለአጭር ጊዜ ብድር (ኦቨር ድራፍትን ጨምሮ) ይከፈልበት የነበረው 8.50 በመቶ የብድር ወለድ ወደ 12 በመቶ ከፍ ብሏል:: አሥር በመቶ ይከፈልበት የነበረው የመካከለኛ ጊዜ ብድር ወደ 13 በመቶ፣ የረዥም ጊዜ ብድር ደግሞ ከ11.50 በመቶ ወደ 14 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል::

በአዲስ አሠራር ሊሰጣቸው ላቀዳቸው የግለሰብ የሞርጌጅ ብድሮች ወለድ 14 በመቶ እንዲሁም የመኪናና የግል ብድር የወለድ ምጣኔ ደግሞ 15 በመቶ የወለድ ምጣኔ የሚከፈልበት እንደሚሆንም ባንኩ አስታውቋል::

ከንግድ ሥራ ጋር የተያያዙ ብድሮችን በተመለከተም በአጭር ጊዜ ለሚከፈል የንግድ ብድር ያስከፍል የነበረውን 14 በመቶ የብድር ወለድ ወደ 15 በመቶ ከፍ አድርጎታል:: ለመካከለኛ ጊዜ ብድሮች እስካሁን ይታሰብ የነበረውን የ15.5 በመቶ የወለድ ምጣኔ አሁን ወደ 15.75 በመቶ አሳድጎታል:: የረዥም ጊዜ የንግድ ብድሮች የብድር ወለድ ምጣኔ ግን ባለበት 16.50 በመቶ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቋል::

ለቅድመ ጭነትና ንግድ የሚሆኑ ዕቃዎች ለአጭር ጊዜ ብድር ከዚህ ቀደም ይከፈል የነበረው የ8.5 በመቶ የብድር ወለድ ምጣኔ አሁን 12 በመቶ ሆኗል:: ይህም መቶኛ ሥሌቱ በ41 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ነው::

የንግድ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን በተመለከተው የ40/60 ኮንዶሚኒየም የንግድ ቤቶችና የ20/80 የኮንዶሚኒየም የንግድ ቤቶች የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን ማሻሻሉን ገልጿል:: በዚህ ማሻሻያ መሠረት የሁለቱም ዓይነት ንግድ ኮንዶሚኒየም ቤቶች እስካሁን ሲከፈልባቸው የነበረውን የ15.50 በመቶ የብድር ወለድ ምጣኔ በአንድ በመቶ በመጨመር 16.50 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል:: ይህ ማለት የብድር ወለድ ምጣኔያቸው 6.4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው::

ከንግድ ውጭ ላሉት የ40/60፣ የ20/80 እና የ10/90 የኮንዶሚኒየም መኖሪያዎች ግን የወለድ ምጣኔው እንደ ቀድሞው በ12.00 በመቶ እንዲቀጥል መደረጉን የባንኩ መረጃ ያመለክታል:: ከወጪ ንግድ ውጭ (Non Export) ዘርፎች ለአድቫንስ ኦን ኢምፖርት ቢልስ የአጭር ጊዜ ብድር ወለድ ከ17 በመቶ ወደ 18 በመቶ፣ የጅምላ ንግድ ብድር ከ15.50 በመቶ ወደ 16.5 በመቶ እንዲሆን መደረጉንም ይኸው የባንኩ መረጃ ያመለክታል:: ባንኩ ጭማሪ ካደረገበት የብድር ወለድ ሌላ ለግብርና ዘርፍ የሚሰጡ ብድር ወለድ ላይ ቅናሽ አድርጓል:: በዚህ ዘርፍ ከዚህ ቀደም ለአጭር ጊዜ (ኦቨር ድራፍትን ጨምሮ) ይጠየቅ የነበረው የብድር ወለድ 14 በመቶ ሲሆን አሁንም በዚሁ እንዲቀጥል ተወስኗል:: ለግብርና ሥራ፣ ለመካከለኛ ጊዜ ብር ይጠየቅ የነበረውን የ15.50 በመቶ ወለድ አሁን ወደ 14.5 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን አስታውቋል:: በተመሳሳይ ለግብርናና ለማዳበሪያ የሚሰጥ የረዥም ጊዜ ብድር ወለድም ከ16.5 በመቶ ወደ 15.5 በመቶ ዝቅ ተደርጓል::

ባንኩ ወደዚህ ዕርምጃ የገባበትን ምክንያት በተመለከተ በሰጠው ማብራሪያ፣ መንግሥት የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ተወዳዳሪና ሳቢ ለማድረግ ገበያ መር የሆኑ ፖሊሲዎችንና እስትራቴጂዎችን በመቅረፅ ተግባራዊ እያደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣  በባንክ ሥራ ዘርፍ በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ ሲሆን፣ የባንክ ኢንዱስትሪውም በአቅርቦትና ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የዋጋ ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ነው::

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በገበያው ውስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲዘልቅና በአገራችን የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ያለውን የጎላ ድርሻ አጎልብቶ መዝለቅ ይችል ዘንድ፣ በተለይ በተለያየ ምክንያት እየተከሰተ ያለው አጠቃላይ የቁጠባ ማሳሰቢያ ወጪ ከፍተኛ መሆንና ባንኩ ለሚሰጠው የብድር አገልግሎት የሚያስከፍለው የወለድ ምጣኔ በገበያ ላይ ከሚታየው የወለድ ምጣኔ አንፃር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ባንኩ ዘላቂ ትርፋማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በመፍጠሩ ማስተካከያው መደረጉን ይገልጻል::

በዚህም መሠረት ይህንን ለማስተካከልና የባንኩ በፋይናንስ ዘርፉ የሚገባውን ሚና እንዲጫወት ለማስቻል ለሚሰጠው የብድር አገልግሎት፣ ወጪውን ታሳቢ ያደረገ መጠነኛ የብድር ወለድ ምጣኔ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ የወሰደው ዕርምጃ ስለመሆኑም አስታውቋል:: አያይዞም ይህ ማስተካከያ የግብርና ዘርፉን ከማበረታታት አንፃር፣ የወለድ ምጣኔው የተቀነሰ ሲሆን፣ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ ለኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች ብድር የሚከፈለው የወለድ መጠን ባለበት እንዲቀጥል መወሰኑንም አስታውሷል::