
March 5, 2025

የብሔራዊ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት
የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ እንዲገበያይ ከተወሰነ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ ልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ አካሂዷል፡፡ 60 ሚሊዮን ዶላር በቀረበበት በዚህ ጨረታ 27 ባንኮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ለአንድ ዶላር የተሰጠው አማካይ የጨረታ ዋጋ 135.6 ብር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
በጨረታው የተሰጠው አማካይ ዋጋ በጨረታው ዕለት ባንኮች ሲያገበያዩበት ከነበረው አማካይ ዋጋ ከአሥር ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑን ያመለክታል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደለገጹት፣ በዕለቱ ተሳታፊ ከሆኑ 27 ባንኮች ውስጥ በዕለቱ የተጫረቱበትን የውጭ ምንዛሪ ያገኙት 12 ባንኮች ናቸው፡፡ እነዚህ አሥራ ሁለት ባንኮች አሸናፊ የሆኑት ለአንድ ዶላር ከ130 እስከ 141 ብር ዋጋ በመስጠት ነው፡፡ በዚህ ጨረታ ላይ አንድ ባንክ ከፍተኛ ዋጋ በመስጠት 200 ሺሕ ዶላር ማግኘቱን እኚሁ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ በሰሞኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የፋይናንስ ባለሙያዎች እንደገለጹት በጨረታው የተሳተፉ ባንኮች በጥቅሉ የሰጡት ዋጋ ከፍተኛ የሚባል መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ጨረታ አንድ ዶላር በ141 ብር ለመግዛት የተጫረተ ባንክ እንደነበር ጭምር ገልጸዋል፡፡ ይህ ዋጋ ትልቅ እንደሆነ የሚገልጹት የፋይናንስ ባለሙያዎቹ፣ ብሔራዊ ባንክ የጨረታውን ውጤት ይፋ ባደረገበት መግለጫ ላይ የተጠቀሰው አማካይ ዋጋ በራሱ በአሁኑ ወቅት ባንኮች አንድ ዶላር ከሚገዙበትና ከሚሸጡበት ተመን በላይ ነው። ይህ የሚያሳየው የባንኮች የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ያለውን ጨረታ የሚያካሂድበት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ የገለጹት ባለሙያው አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገበያውን ለማረጋጋት ነው፡፡ የተወሰነ መጠን የለው የውጭ ምንዛሪ እያወጣ ባንኮች እንዲጫረቱ ማድረግ ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ፣ በተለይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሚኖርበት ጊዜ እንዲህ ያለውን ጨረታ ማድረጉ ተጠባቂ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
በሰሞኑ ጨረታ ግን ያልተጠበቀና ከፍ ያለ ዋጋ ተሰጥቷል ብለው ያምናሉ፡፡ አንዳንድ ባንኮች በአንድ ዶላር የሰጡት ዋጋ እስከ 141 ብር ነው፡፡ ባንኮቹ በዚህን ያህል ደረጃ ዋጋቸውን ከፍ አድርገው የተጫረቱበት የየራሳቸው ምክንያት ሊኖርባቸውም በዋናነት የሚያስፈልገው ክፍያዎቻቸውን ለመሸፈን ከዚህ ጨረታ የተሻለ ዕድል ላይኖር ይችላል በሚል ከፍ ባለ ዋታ ተጫርተው የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲሉ የወሰዱት ዕርምጃ እንደሆነም አክለዋል፡፡
በተለይ አንዳንድ ባንኮች በዚህን ያህል ዋጋ ጨረታ ውስጥ የገቡት ከነዳጅ ግዥ ጋር በተያያዘ ለከፈቱት ኤልሲ የክፍያ ለመፈጸም እንዲያስችላቸው ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ መክፈል ያለባቸው የክፍያ ጊዜ ስለደረሰ ይህንን ለመሸፈን ሲሉ ከፍ ያለ ዋጋ መስጠታቸውን እኚሁ የፋይናንስ ባለሙያ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
አነስተኛ መጠን ያለውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የተጫረቱ አንዳንድ አነስተኛ ባንኮች ዋጋ ከፍ አድርገው ለመጫረታቸው አንዱ ምክንያት የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሪ ከባንኮች ጋር ቢገበያዩ ሊከፍሉ የሚችሉትን ኮሚሽንና ተያያዥ ክፍያዎች በማሥላት የተሻለ በዚህ ጨረታ ላይ መሳተፍ የተሻለ መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡
ከነዳጅ ግዥ ጋር የተያዘውን የውጭ ምንዛሪ ክፍያ ለመፈጸም ያስችለናል ያሉ ባንኮች በጨረታው ከፍ ያለ ዋጋ በሰጡ ተጠባቂ ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውንም ሲያብራሩ ለነዳጅ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን በቀላሉ በገበያ ውስጥ ማግኘት ስለማይችሉ እንዲህ ያለው የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ላይ ዋጋ ከፍ አድርገው ቀርበዋል ብለዋል፡፡ የነዳጅ ግዥ ኤልሲ በመክፈት የውጭ ምንዛሪ ክፍያ ያለባቸው ባንኮች አሁን ላይ ቁጥራቸው በርካት ያለ ሲሆን፣ ይህንን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደ ሰሞኑ ያለ ጨረታ እንደ መልካም ዕድል የሚታይ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ባንኮቹ የነዳጅ የውጭ ምንዛሪ ክፍያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪያቸውን የሚያውሉበት እየሆነ መምጣቱም ታውቋል፡፡
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ለነዳጅ ግዥ ለሚከፍቱት ኤልሲ ይሰጣቸው የነበረውን ዋስትና በማንሳቱና ባንኮች ለከፈቱት ኤልሲ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ባንኮቹ ራሳቸው እንዲከፍሉ አዲስ አሠራር በመዘርጋቱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ያሉ ጨረታዎችን ማውጣቱ እውነታዊና አሉታዊ ተፅዕኖን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ ደግሞ የጨረታው አስፈላጊነት ባያጠራጥርም ለጨረታው እየተሰጠ ያለው ዋጋ ግን ይዞት ሊመጣ የሚችለው ተፅዕኖ ይኖራል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡
ይህንንም ሲያብራሩ በጨረታው በአማካይ የ136 ብር አካባቢ ስለደረሰ ባንኮችም ወደዚህ የምንዛሪ ዋጋ መምጣታቸው ስለማይቀር አንዳንድ ላኪዎች ምርቶቻቸውን ከመላክ ያዝ እንዲያደርጉ ሊገፋፋቸው ይችላል የሚለው ሥጋታቸው አንዱ ነው፡፡ ይህ ምልከታ አሁንም እየታየ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ምርቶችን (ሆርድ) የማድረግ አዝማሚያም እንዲታይ ስለሚያደርግ አንዳንድ ምርቶች ላይ የዋጋ ለውጥ ወይም ወይም ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡
ጨረታው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ያለው መሆኑን ቢያምኑም፣ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ጨረታውን በቋሚነት ማካሄድ የማይችል በመሆኑ እንደ ሰሞኑ ዓይነት ጨረታ በድንገት በሚወጣበት ጊዜ ባንኮች ዕድሉ እንዳያመልጣቸው የተጋነነ ዋጋ በመስጠት በጨረታው መሳተፍን እንደሚመርጡ ጠቅሰዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ በገበያ ዋጋ እንዲገበያይ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ሲያወጣ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
የመጀመርያውን ጨረታ ባለፈው ነሐሴ 2016 ዓ.ም. ላይ የተካሄደ ሲሆን በዚህም በአጠቃላይ የቀረበው የውጭ ምንዛሪ መጠን 35 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ምንጮቹ ገልጸዋል። ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ የተካሄደውን የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ያወጣው ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ መሆኑን አስታውሰዋል።
ሰሞኑን በተካሄደው ጨረታም ባንኮች ከፍተኛ የሚባለውን ዋጋ ሊሰጡ የቻሉበት አንዱ ምክንያት ብሔራዊ ባንክ ከዚህ በኋላ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ስለማውጣቱ እርግጠኛ ባለመሆናቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
ብሔራዊ ባንክ በቋሚነት የውጭ ምንዛሪ በጨረታ የማያቀርብ በመሆኑ ባንኮች ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም የውጭ ምንዛሪ ክምችታቸውን ለማሳደግና ላለባቸው የውጭ ዕዳ ክፍያ መፈጸሚያ በቂ የውጭ ምንዛሪ ስንቅ ለመያዝ ሲሉ ከፍተኛ ዋጋ ሰጥተው በጨረታው መወዳደራቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ያካሄደውን ጨረታ በማስመልከት ባወጣው መግለጫ በጨረታው ከፍተኛ የባንኮች ተሳትፎ መታየቱን አስታውቋል፡፡ አያይዞም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝና ከዋጋና ከውጭ ምንዛሪ መረጋጋት ጋር በሚስማማ ሁኔታ ተጨማሪ ተመሳሳይ ጨረታዎችን ሊያካሂድ እንደሚችል ገልጿል፡፡
