ዜና
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ወደ ኬንያ ከምትልከው ይልቅ የምታስገባው ምርት ከፍተኛ መሆኑ…

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: March 5, 2025

በሃይማኖት ደስታ

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ወደ ኬንያ ምርት በመላክ ያገኘችው ድምር ገቢ፣ በአንድ ዓመት (በ2010 ዓ.ም.)  ብቻ ያገኘችውን መብለጥ አለመቻሉን በተደረገ አንድ ጥናት መታወቁ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራትና በኬንያ አምራቾች ማኅበር (KAM) አስተባባሪነት ሰኞ የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል በተዘጋጀው ሁለተኛው የኢትዮ ኬንያ የቢዝነስ ፎረም ላይ ነው።

ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አማካይነት ‹‹በኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎች›› በሚል ርዕስ በፎረሙ ላይ የቀረበው ጥናት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2018 ወደ ኬንያ ከላከችው ዓመታዊ ምርት 276,892,888 ዶላር ገቢ ያገኘች የነበረ ሲሆን፣ በቀጣዩ ዓመት (በ2019) ያገኘችው ገቢ ግን ወደ 20,329,838  ዶላር  መውረዱን ያሳያል።

በጥናቱ መሠረት ኢትዮጵያ በዋናነት የግብርና ምርቶች ማለትም እንደ ስንዴ፣ ቡና፣ ቅመማ ቅመም፣ የኤሌክትሪክ ግብዓቶች፣ የቆዳ ውጤቶችና ሌሎች ምርቶችን በመላክ፣ እ.ኤ.አ. በ2020 11,527,284 ዶላር፣ በ2021 17,032,758 ዶላር፣ በ2022 28,826,232 ዶላር፣ በ2023 73,885,126 ዶላር፣ በ2024 ደግሞ 65,880,834 ዶላር  ገቢ ማግኘቷ መለየቱን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የምርምርና ፕሮጀክት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ደንድር ናቸው።

እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2018 ወደ አገር ውስጥ ያስገባችው ምርት 23,532,254 ዶላር ብቻ የነበረ ቢሆንም፣ ከኬንያ በተከታታይ ዓመታት ግን ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት አስገብታለቸ።

ኬንያ በዋናነት የፋብሪካ ውጤቶችና መሰል ምርቶችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ በ2019 63,816,348 ዶላር፣ በ2020 76,223,890 ዶላር፣ በ2021 115,112,409 ዶላር፣ በ2023 ደግሞ 95,655,839 እንዲሁም በ2024 ሙሉ ዓመት 77,83,702 ዶላር  ገቢ ማግኘቷን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የጥናት ሪፖርቱ የኢትዮጵያና የኬንያ የንግድና የኢንቨስትመንት ልውውጥ ሚዛን ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ኬንያ እያጋደለ መምጣቱን ማመላከቱ ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጄኔራል ዳይሬክተር ዮሐንስ ፋንታ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያና የኬንያ ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህም ሁለቱ አገሮች ካላቸው ታሪካዊ ግንኙነት አንፃር፣ ኢትዮጵያ ብዙ መሥራት እንዳለባት የሚያሳይ በመሆኑ ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር አብሮ ከመሥራት ይልቅ ባህር ማዶ ካሉ አገሮች ጋር የበለጠ ትኩረት መስጠቷ የታየው አለመመጣጠን እንዲመጣ  አንዱ መንስዔ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን የተናገሩት ጄኔራል ዳይሬክተሩ፣ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ይህን ሁኔታ ለመቀየር አገሮች የበለጠ ቅርብ ግንኙነት ፈጥረው እንዲሠሩና የንግድ ልውውጣቸውን እንዲያሳድጉ አስቻይ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ተፈጻሚ መሆን፣ አገሮች አንዳቸው ከአንዳቸው የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያደርጉትን ፍትጊያና ሽሚያ በመጠኑም ቢሆን የሚያስቀር ስለሆነ፣ የነበረውን መራራቅ አስቀርቶ የተሻለ የንግድ ልውውጥ የሚኖርበትን ዕድል ይዞ ይመጣል ብለው እንደሚያስቡም ዮሐንስ (አምባሳደር) አመልክተዋል።

የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በተለይ በእነዚህ አገሮች መካከል ለሚኖር ግብይት አማራጭ የሚሆንበት ዕድል መኖሩንም አክለዋል። በቀጣይም የግብርና ምርቶች መጠንን ከፍ ማድረግ፣ የፋብሪካ ውጤቶች ላይ እሴት ጨምሮ በመላክ የተዛባውን የንግድ ሚዛን ማስተካከል እንደሚገባ ጄኔራል ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ  የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ ኦሪና በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያና ኬንያ ረዥም ዓመታት ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ቢኖራቸውም፣ ዓመታዊ የንግድ ልውውጣቸው ሲታይ ግን አሁንም ዝቅተኛ ሆኖ መቀጠሉን አውስተዋል፡፡ ይህን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ይዞ መምጣቱን ጠቁመው፣ ኬንያውያን ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም በኬንያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሲነሳ ድንበር ላይ  የሚስተዋል ሕገወጥ ንግድ ተጠቃሽ መሆኑን በመግለጽ አስተያየታቸውን የሰጡት ዮሐንስ (አምባሳደር)፣ ሕገወጥ ንግድ የአንድ አገር የኢኮኖሚ ነቀርሳ መሆኑን ጠቁመው በዚሁ ረገድ ሕገወጥ የድንበር ንግድን ለመከላከልና የሞያሌ የአንድ መስኮት ስምምነት ተፈርሞ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ፣ የአፍሪካ አገሮች ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት፣ የአኅጉሪቱን የንግድ ልውውጥ የሚያስፋፋና የንግድ ችግሮችን የሚቀርፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እ.ኤ.አ. በ2018 የአፍሪካ አገሮች መሪዎችና የአገሮቹ ተወካዮች አኅጉሪቱን በነፃ የንግድ ልውውጥ ሊያስተሳስር የሚችል ስምምነት መፈረማቸው የሚዘነጋ አይደለም:: ስምምነቱ 1.2 ቢሊዮን አፍሪካውያንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ለአገሮች ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

የኢትዮ ኬንያ የንግድ ፎረምን ቋሚ መድረክ ለማድረግ በዓመት አንድ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ፣ በተመሳሳይም በናይሮቢ ወጥ ሆኖ ስለሚካሄድበት ሁኔታ ውይይቶች መደረጋቸውን ዋና ጸሐፊው አቶ ዘካርያስ ገልጸዋል።

ፎረሙን እንደ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና መሰል የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ለማስፋፋት ውጥን ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። በኬንያ የአምራቾች ማኅበር (KAM) እና በአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አስተባባሪነት ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚካሄደው የቢዝነስ ለቢዝነስ ፎረም፣ የሁለቱ አገሮች  የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች እንዲጎለብቱ ለማድረግና መጠኑ አሁን ካለው በላይ የበለጠ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተመልክቷል።

በመድረኩ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ የኬንያ አምራቾች ተሳታፊ ሆነዋል። ተሳታፊዎቹ በሚኖራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን ጨምሮ የአገር ውስጥና የባህር ማዶ አምራች ድርጅቶችን እንደሚጎበኙ ተጠቁሟል። ኮንፈረንሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በአዲስ አበባ የተካሄደው፡፡