

በተመድ ጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ፀጋአብ ከበበው (አምባሳደር)
ዜና በጄኔቫ እየተካሄደ ባለው የተመድ ጉባዔ 44 አገሮች በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ያሳስበናል አሉ
ቀን: March 5, 2025
- የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ማሳሰቢያውን መሠረተ ቢስ ብለውታል
በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 58ኛው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፣ 44 አገሮች በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ያሳስበናል ሲሉ መግለጫ አወጡ።
ኤ.ኤ.አ. ከየካቲት 24 ቀን 2025 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ጉባዔ የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ አገሮቹን በመወከል የካቲት 24 ቀን ባቀረቡት መግለጫ፣ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ፣ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግና መደራጀት ላይ ያሉ ገደቦች በመጥቀስ ጋዜጠኞችን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችንና የመብት ተሟጋቾችን ማፈን አሳሳቢ ናቸው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች አሳሳቢነት እየጨመረ መሆኑን የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን መረጃ ዋቢ በማድረግ እንዲስተካከሉ አሳስበዋል፡፡
የንፁኃን ግድያ፣ ማንገላታት፣ ማሰቃየት፣ በኃይል መሰወር፣ ዜጎችን ከሕግ ውጪ በቁጥጥር ሥር ማዋልና መሠረተ ልማቶችን ማውደም መቆም አለባቸው ብለዋል፡፡
አገሮቹ በተወካዩ አካማይነት ባቀረቡት መግለጫቸው በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ቀጥሏል ባሉት ግጭት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቆም፣ ተፋላሚ ወገኖች ወደ ሰላማዊ ድርድር ሊመጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ አክለውም የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ እንዲሆንና በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2007 ጀምሮ የሞት ቅጣት አለመተግበሩን እንደ መልካም ገጽታ የሚወሰድ መሆኑን የገለጹት አገሮቹ፣ አሁንም የሞት ቅጣት ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ መንግሥት ድንጋጌው እንደገና እንዲያስብበት አሳስበዋል፡፡
አገሮቹ ለኢትዮጵያ ላቀረቡት ጥሪ ምላሽ የሰጡት በተመድ ጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ፀጋአብ ከበበው (አምባሳደር)፣ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ላይ መግለጫ ያወጡ አገሮች ‹‹አሳዛኝ፣ መሠረት የሌለው፣ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የማይገናኝ ነው፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አምባሳደሩ አክለውም፣ የቀረበው መግለጫ በፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆኑን፣ ስምምነቱን በሚያስፈጽሙ አካላት ላይ ጣልቃ የመግባት እንቅስቃሴ ነው ብለውታል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር ገለልተኛ ተቋማት የማቋቋሙ ተግባር በሒደት ላይ ይገኛል ያሉት ቋሚ መልዕክተኛው፣ ኢትዮጵያ ለሰላም፣ ለፍትሕና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ያልተገደበ ቁርጠኝነት አላት ብለዋል። መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
