

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት (ጆቤ)
ዜና ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ግጭት ሊያመሩ እንደሚችሉ የቀድሞ ከፍተኛ የጦር አዛዥ ተናገሩ
ቀን: March 5, 2025
የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት (ጆቤ)፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት መጀመሪያውንም ያልተቀደሰ ግንኙነት እንደነበር ጠቁመው፣ ወደ ግጭት ሊያመሩ እንደሚችሉ የሚያመላክቱ ፍንጮች እንዳሉ ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያ የወደብ ተጠቃሚ መሆን የምትችልባቸውን ሁኔታዎች በተመለከተ ከሦስት ዓመታት በፊት የሠሩትን ጥናታዊ ጽሑፍ አስታውሰው፣ ጥያቄው ግን በጉልበት መመለስ የለበትም ብለዋል፡፡ በአገሮቹ መካከል ጦርነት ቢቀሰቀስ አቅጣጫው ምን ይሆናል የሚለው ጉዳይ የሚታወቀው የጦርነቱ ዓላማ ሲታወቅ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ‹‹ጦርነቱ አንድም አሰብን መያዝ፣ ሁለተኛው ደግሞ ሻዕቢያን ማስወገድ ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የጦርነቱ ዓላማ አሰብን መያዝ ከሆነ የሁለቱን አገሮች የመሣሪያና የቴክኖሎጂ አቅም መገምገም እንደሚገባ ጠቅሰው፣ የሻዕቢያን መንግሥት የመጣል ዓላማ ካለ ደግሞ፣ የኤርትራ ዕጣ ፈንታ የሚያሳስባቸው እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች ጣልቃ ገብነት የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹እነ አሜሪካ፣ ቻይናና ሩሲያ ጉዳዩን እንዴት ያዩታል? ግብፅስ ለማን ትወግናለች? የሚለውም ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሰብን ልያዝ ብትል፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ ቢደግፏት፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ግን ደስተኛ ላትሆን ትችላለች፡፡ እንዲህ ዓይነት ቀውስ ግብፅንም መጋበዙ አይቀርም፡፡ የሶማሊያና የሶማሌላንድን ፍላጎት የቱርክ አሸማጋይ ሆኖ በቀጣናው ውስጥ መገኘት፣ እንዲሁም የዶናልድ ትራምፕን ወደ ሥልጣን መምጣትን ማመዛዘን ያስፈልጋል፡፡ የቀጣናው አሠላለፍ ይቀየር ቢባል እንኳን፣ አሠላለፉን በቀይ ባህር ብቻ መቀየር አይቻልም፡፡ አሰብን መያዝ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከ28 ዓመታት በፊት በተካሄደው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ሻዕቢያን የመደምሰስ አቅም የነበረ ቢሆንም ይህ አለመደረጉ ትልቅ ስህተት እንደነበር የገለጹት የቀድሞው የአየር ኃይል ዋና አዛዥ፣ ከዚያ በኋላ በነበሩት 18 ዓመታት የተሠራው ጠላትን በዝምታ የማቆየት ትልቅ ስህተት ከባድ ዋጋ ማስከፈሉን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የትግራይ ሕዝብ ዋጋ እንዲከፍል ምክንያት ሆኗል ብለው፣ አሁንም ጦርነት ከተቀሰቀሰ የትግራይ ክልል የጦርነት ዓውድማ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት ሠራዊት ቲዲኤፍ ከሚባለው የክልሉ ሠራዊት ጋር ሳይስማማ ወደ ትግራይ መግባት ይችላል ወይ? የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከ28 ዓመታት በፊት ‹‹ኢትዮጵያ በፌደራሊዝም ሥርዓት ተሳስራለች፡፡ የአየር ኃይልም የላትም በሚል ሻዕቢያ ወረራ ፈጽሟል፤›› ያሉት ሜጀር ጄኔራል አበበ፣ በወቅቱ የመከላከያ ሠራዊቱ የማዕከላዊ ኮማንድ አባል እንደነበሩና ሻዕቢያን አስመራ ድረስ ገብቶ የመደምሰስ ውሳኔ ላይ ተደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ውሳኔ መሠረት፣ ‹‹ኤርትራን ማዳከም በቂ ነው›› ተብሎ እንዲመለሱ መታዘዛቸውን ያስታወሱት ጄኔራሉ፣ በወቅቱ የተሠራው ስህተት ‹‹ዛሬ እንደ አገር ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ በእኛ ጥፋት ምክንያት ሻዕቢያ ነፍስ ዘርቷል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት 18 ዓመታት ‹‹የትግራይን ሕዝብን አጠፋለሁ፣ ኢትዮጵያን እወጋለሁ›› የሚል የጠላት ኃይል ከጀርባ እያለ ዝምታ መመረጡ ትልቅ ስህተት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በማከልም ‹‹ኢትዮጵያ የባህር በር ይገባታል፡፡ አሰብን መጠቀም ይገባታል፡፡ ነገር ግን በኃይል መሆን የለበትም፤›› ብለው፣ የቀጣናውን አሠላለፍ ለመቀየር ያለመ ጦርነት ቢሆን እንኳን፣ ‹‹ጨዋታው በኢትዮጵያና በኤርትራ አያበቃም፡፡ ጦርነት መጀመር ቀላል ቢሆንም ማቆም ከባድ ነው፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ በሁለቱም ወገን የሚወሰድ የኃይል ዕርምጃ ቀጣናዊ አደጋው የጎላ እንደሆነም አክለዋል፡፡
የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል መቃቃር መፈጠሩን መታዘባቸውን ገልጸው፣ ቀይ ባህርን ማዕከል ያደረጉ የቃላት ልውውጦች መኖራቸውን ከሁለት ቀናት በፊት ተናግረዋል፡፡
‹‹ዝግጅት የሚመስሉ ወታደራዊ ትዕይንቶችን እያየን ነው፤›› ያሉት አቶ አማኑኤል፣ በጦርነት የሚፈታ ጥያቄ የለም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥታት ነገሮችን በሰከነ መንገድ መመልከት እንዳለባቸው በማሳሰብ፣ ትግራይን የጦርነት ዓውድማ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን የሚያመጣው ጂኦ ፖለቲካዊ አደጋም ከግምት መግባት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ሒዩማን ራይትስ ኮንሰርን ፎር ኤርትራ የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ የኤርትራ መንግሥት ከ60 ዓመት በታች ያሉ ዜጎች ለወታደራዊ ሥልጠና እንዲከቱ ለየአካባቢው አስተዳደሮች ትዕዛዝ ማስተላለፉን ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡