

በደቡባዊ ቀይ ባህር ዳርቻ ላይ የሚገኘው የአሰብ ወደብ
March 5, 2025
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመጀመሪያውን መደመር መጽሐፍ ባስመረቁ ዕለት ስለሰላም በብዙ ተናግረው ነበር፡፡ በዚሁ ዕለት ከተናገሩት መካከል ደግሞ ‹‹ሰላም ሰላም የምንለው ጦርነትን ስለምንፈራ ሳይሆን ሰላምን አብዝተን ስለምንወድ ነው፡፡ ጦርነት ጥፋት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ተነሱ እንዋጋ ካልን በኋላ የሞተውንና የቆሰለውን የመናገር ልምድ ስለሌለን እንጂ ከወንድም የኤርትራ ሕዝብ ጋር ተጣልተን ያጠፋነው ሕይወት ራሱ ከፍተኛ ቁስል ነው ተጨማሪ ቁስልና ጉዳት ሳይሆን ተጨማሪ ሐሳብ ነው የሚያስፈልገን፤›› የሚል መልዕክትም የያዘ ሐሳብ ይገኝበት ነበር፡፡

ኤርትራና ኢትዮጵያ ከ1990 እስከ 1992 ዓ.ም. ባደረጉት ከባድ ጦርነት በይፋዊ መረጃዎች መሠረት 100 ሺሕ ሰዎች ከሁለቱም ወገን ማለቃቸው ይነገራል፡፡ በጊዜው ሁለቱ በድህነት የሚታወቁ አገሮች ቢሆኑም ለዚህ ጦርነት ግን ኢትዮጵያ ወታደራዊ ወጪዋን በዓመት ወደ 480 ሚሊዮን ዶላር ስታሳድግ፣ ኤርትራ ደግሞ ወታደራዊ በጀቷን ወደ 306 ሚሊዮን ዶላር አድርሳው እንደነበር የለንደኑ ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም መረጃ አመልክቷል፡፡
በዚያ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ባደረሰ ጦርነት ሰፊ ተሳትፎ የነበራቸው ሁለቱ አገሮች ለ20 ዓመታት በጦርነት ሥጋት ተፋጠው የዘለቁበትን ሁነት ያጠኑት ሌተና ጄኔራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል በቅርቡ ባሳተሙት ‹‹አዙሪት፡- ኢትዮጵያና ጦርነት ፍቺ የሚያስፈልገው ጋብቻ›› በተባለው መጽሐፋቸው፣ ከአልጀርስ ስምምነት መፈረም በኋላም አገሮቹ በድንበራቸው የቀጠለውን ችግር ገምግመውታል፡፡ ጦርነቱ ሲጀመር ኤርትራ ወደ 70 ሺሕ ኢትዮጵያውያንን ስታባርር ኢትዮጵያም በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ኤርትራዊያንን አባራለች ይላሉ፡፡ ትግራይ ክልል ከኤርትራ ጋር በሚዋሰንባቸውና ጦርነት በተካሄደባቸው ቀጣናዎች፣ ወደ 1.5 ሚሊዮን ዜጎች ከመደበኛ ሕይወታቸው ተፈናቅለው እንደነበርም ይጠቅሳሉ፡፡ አፋር ክልል ከኤርትራ ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ደግሞ ወደ 300 ሺሕ ሰዎች ከመደበኛ ሕይወታቸው ውጪ ሆነው ተፈናቅለው ለመኖር ተገደው እንደነበር ይተርካሉ፡፡ በኤርትራም ወገን ጥናት ቢደረግ በግጭት ቀጣና ያሉ በርካታ ዜጎች ሕይወት መቃወሱ የሚጠበቅ መሆኑን በመጠቆም፣ ሁለቱ አገሮች በሁለት ዓመት ውጊያና በ20 ዓመታት ፍጥጫ ውስጥ ሲያሳልፉ ካተረፉት ይልቅ ያጡት እጅግ ብዙ መሆኑን በሰፊው አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሲመጡ ይህ መቆም አለበት በሚል የሰላም ጥረት መጀመራቸውን በርካቶች ያወሳሉ፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ግጭት በማስቆም ሰላም የሰፈነበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ጀግና ከማሰኘት፣ እንዲሁም ከሁለቱ አገሮች ሕዝቦች መደሰት ባለፈ በመላው አፍሪካ ቀንድም ትልቅ ተስፋ የፈጠረ አዲስ ክስተት ሆኖ ነበር፡፡
በጥቂት ዓመታት ልዩነት ግን ይህ ሁሉ ተስፋ ተመልሶ ጠወለገ፡፡ የትግራይ ጦርነት አድማሱን አስፍቶ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎችን ናጠ፡፡ ኤርትራ በዚህ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ሆና ተከሰተች፡፡ በሒደት ጦርነቱን ለመቋጨት የሰላም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ቢፈረምም፣ ነገር ግን ስምምነቱም ቢሆን ሌላ መልክ ያለው ውጥረትና የኃይል አሠላለፍ መፍጠሩ ነው የሚነገረው፡፡ አሁን ኤርትራና ኢትዮጵያ ወደ ቀደመው በውጥረት ወደ ተሞላ ግንኙነት ተመልሰው የገቡ ይመስላል፡፡
በአጭር ዓመታት የተፈጠረውን ይህንን የሁለቱ አገሮች ዕርቅና ፍጥጫ መፈራረቅ፣ ‹‹ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ የትብብርና የውዝግብ አዙሪት›› በሚለው መጽሐፋቸው የፖለቲካ ምሁሩ በለጠ በላቸው (ዶ/ር) ትኩረት በሚስብ መንገድ ገልጸውታል፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜውን ዕርቅ ከሁለቱ አገሮች ፍላጎት ይልቅ፣ በውጭ ኃያላን ግፊትና ተፅዕኖ የመጣ ለውጥ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
‹‹ከስምምነቱ ወዲህ ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚጠበቀው መንገድ አለመስተናገዱ አያከራክርም፡፡ በአስመራና በሪያድ ስምምነቶች መሠረት የጋራ ኮሚሽኖች ሊቋቋሙ አልቻሉም፡፡ ተስፋ የተጣለባቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ መስተጋብሮች በአግባቡ አልተተገበሩም፡፡ አጨቃጫቂው የድንበር ጉዳይ ዕልባት አልተበጀለትም፡፡ የዲፕሎማሲ ግንኙነቱም በታለመለት መስመር አልሄደም፡፡ እስከ ትግራይ ጦርነት መጀመሪያ ድረስ ምንም እንኳን ኤምባሲዎች ቢከፈቱም ሆነ አምባሳደሮች ቢሾሙም ከይስሙላ የዘለለ ፋይዳ አልነበራቸውም፡፡ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ወደ ምድብ ቦታቸው ጭምር መሄድ አልቻሉም፡፡ ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ደግሞ ይህ ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ተቋረጠ፡፡ በስምምነቱ ወቅት ይታይ የነበረው የመሪዎች ቅርርብና ግንኙነትም መቀጠል አልቻለም፡፡ ከሁሉም በላይ ኤርትራ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንድትገባና በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንድትሳተፍ መደረጉ የሚያስከትላቸው ውስብስብ ውጤቶች በቅጡ ሊጤን ይገባዋል፤›› በማለት በለጠ (ዶ/ር) ከትበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተጋበዙበት የሚሊኒየም አዳራሽ መድረክ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ‹‹እኔና ኢሱ ስንደመር አሰብ ይሆናል›› የሚል በታዳሚያን ብዙ ያስጨበጨበ ንግግርም አሰምተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ባለፈው ዓመት የባህር በር ጉዳይን ዋና የመንግሥታቸው አጀንዳ አድርገው ዓብይ (ዶ/ር) ካነሱ ወዲህ ደግሞ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው መጠራጠርና ውጥረት የበለጠ መባባሱ ይነገራል፡፡ የባህር በር ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግሥት መነሳት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላት ግንኙነት መቀየር መጀመሩ በሰፊው ያነጋግራል፡፡
የኤርትራ ባላሥልጣናትም ቢሆኑ ኢትዮጵያ አሰብን መከጀል ጀምራለች በሚል በፕሮፓጋንዳና በዲፕሎማሲ አፀፋ መስጠት ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ ይኸው የሁለቱ አገሮች የግንኙነት መላላት አሁን ላይ የበለጠ ተባብሶ ደግሞ የጦርነት ሥጋት መሆን የጀመረ ይመስላል፡፡ በተለይ በቅርቡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በአልጄዚራ ላይ ኤርትራን የቀጣናው በጥባጭ ናት ብለው ሌላ ዙር ግጭት በአካባቢው ከመቀስቀሱ በፊት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያስታግሳት የሚል ሰፊ ሀተታ ማስነበባቸውን ተከትሎ በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል አዲስ ጦርነት እያንጃበበ ነው የሚል መላምት ጎልቶ መሰማት ቀጥሏል፡፡ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ለዚህ ጽሑፍ ከሰጡት ፈጣን ምላሽ በተጨማሪ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የኤርትራ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን ማውገዛቸውን ሲቀጥሉ ታይተዋል፡፡
‹‹ኤርትራ ደሃ አገር ናት፡፡ ቀጣናችን ካለበት ውስብስብ ጂኦ ፖለቲካዊ ኢንተረስት [ፍላጎት] አንፃር የኤርትራ መንግሥት የራሱን ሕዝብ ሳይሆን፣ የሌሎች ኃይሎችን ፍላጎት የሚያስፈጽም መንግሥት ነው፡፡ ይህ መንግሥት እስካለ ድረስ ደግሞ የአካባቢያችን ችግር የሚቀጥል ነው የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር ቢኖራት አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር ኖሯት በሰላምና በጉርብትና ብንኖር የሚጠቀሙት ብዙ ነው፡፡ እንቁላልና ዶሮ ወይም ጤፍ መለዋወጥ ብቻ አይደለም ነገሩ፡፡ የሰጥቶ መቀበል ነው ጉዳዩ፡፡ ከእነሱ የባህር በር እንደምንፈልገው ሁሉ እኛም መስጠት የምንችለው ብዙ የተፈጥሮ ፀጋ አለ፡፡ ኤርትራዊያን በዚህ አይጎዱም ይጠቀማሉ እንጂ፡፡ ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚፈልጉ ብዙ ኃይሎች አሉ፡፡ አሁን ካለንበት ችግር በጋራ ልንወጣ ይገባል፣ በጋራ ልንለማ ይገባል በሚል ነው እኔ የባህር በር ከኤርትራ በማግኘት በልዋጩ አብሮ ማደግን የደገፍኩት፤›› የሚል ይዘት ያለው የአቶ ስዬ አብረሃ ንግግር ከሰሞኑ በማኅበራዊ መገናኛ ገጾች በሰፊው ሲሠራጭ ነበር፡፡
የቀድሞው የሕወሓት ታጋይ ስዬ አብረሃ በ1990ዎቹ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያን ታሪካዊ የባህር በር የሆነውን አሰብ ወደብን ማስመለስ አለብን የሚል አቋም ካንፀባረቁ አመራሮች ጋር ስማቸው የሚጠቀስ ሲሆን፣ በዚህ አቋማቸውም በወቅቱ ከነበረው የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ቡድን ጋር ተጋጭተው ከቡድኑ እንዲወጡ ከተደረጉ ሰዎች መካከል አንዱ ስለመሆናቸው ብዙ ሲነገር ቆይቷል፡፡
ከረዥም ጊዜ በኋላ ተቆፍረው ከወጡ የቀድሞ ባለሥልጣናት ንግግሮች በተጨማሪ አሰብ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ማሳኪያ መንገድ ይሆናል የሚለውን ጉዳይ ከግራም ከቀኝም የሚያራግቡ የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክቶች በሰፊው በበረከቱበት በዚህ ወቅት፣ ኤርትራና ኢትዮጵያ ለአሰብ ዳግም መፋለማቸው አይቀርም የሚለውን ግምት የበለጠ የሚያጠናክሩ ንግግሮች አሁን በአመራርነት ካሉ ሹማምንትም እየተደመጡ ናቸው፡፡
የዓድዋ ድል 129ኛ ዓመት መታሰቢያ በአል ሲከበር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ ‹‹የጊዜ ጉዳይ እንጂ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ማኅበረሰብ አባል መሆኗ የማይቀር ነው፤›› የሚለው ንግግራቸው፣ ኢትዮጵያ በአሰብ ላይ ያላት ፍላጎት የጠነከረ ነው የሚለውን ግምት የበለጠ አጠናክሮታል፡፡ ‹‹አገራዊ ጥቅም ለማስከበር ነው እየተዘጋጀን ያለነው›› በማለት የተናገሩት ፊልድ ማርሻሉ፣ የባህር በር ጥያቄ ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሩ አብርሀም በላይ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በትግርኛ በሰጡት ቃለ መጠይቅም ቢሆን፣ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ኤርትራን ወንጅለዋል፡፡ ‹‹ኤርትራ ከትግራይ መሬት ለቃ አልወጣችም፡፡ የኤርትራ ሠራዊት ትግራይን እንደያዘ ነው፡፡ የትግራይ ባለሥልጣናት የፌደራል መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲጣስ አደረገ እያሉ ቢከሱም፣ ቦታውን እነሱ እንዲቆጣጠሩት ሲፈቀድላቸው ግን አያደርጉትም፡፡ የፌደራል መንግሥት ኃይል ካስጠጋ ቦታውን የወረረው ኃይል በዚያ ቦታ አይቆይም፡፡ የኤርትራ ኃይል በያዘው ቦታ እቆያለሁ የሚል ከሆነም ልክ ለማስገባት የሚቸገር ኃይል የለንም፤›› በማለት ነበር ለኤርትራ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ያስተላለፉት፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዓድዋ በዓል መታሰቢያ መድረክ ላይ ባሰሙት ንግግር ደግሞ፣ ‹‹የአገራችንን መሻትና ፍላጎት የሚመጥን ተለዋዋጭ የሆነውን ስትራቴጂካዊ፣ ጂኦ ፖለቲካዊና ጂኦ ስትራቴጂካዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ ጠንካራ መከላከያ መገንባታችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ፤›› በማለት አጠገባቸው ለነበሩ የመከላከያ አመራሮች መልዕክት ማስተላለፋቸውም ቢሆን፣ አንድ ነገር እየተደገሠ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች እንዲበራከቱ ነው ያደረገው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ኤርትራ የቀጣናው ጠብ ጫሪ ናት ሲል መክሰሱ ተደጋግሟል፡፡ ኤርትራ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን በመቀጠል አማፂያንን ትደግፋለች፣ እንዲሁም ግንባር ለመፍጠር ትሞክራለች በማለት በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ እየተስተጋባ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይን ማንሳት ከጀመረች ወዲህ የበለጠ የተጋጋለው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት አሁን ደግሞ ወደ ዳግም ጦርነት ሊገቡ ነው የሚል ግምት ማሰጠት ጀምሯል፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ እንደገና ወደ ጦርነት መግባት በዋናነት አሰብ ወደብን ያማከለ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
ኤርትራና ኢትዮጵያ እንደ ባድሜ ባሉ መሬቶች ይገባኛል ያደረጉት የቀደመው ጦርነት ቁስል ዛሬ ድረስ ያልሻረና ቀውሱም ያልተፈወሰ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ ሁኔታ ጨርሶ መፍትሔ ሳያገኝ ወደ እንደገና ጦርነት በአሰብ ጉዳይ ከተገባ ሊከሰት የሚችለው ቀውስና አደጋ ደግሞ በርካቶችን እያሠጋ ነው፡፡