

ዜና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዓርማንና የበርታ ብሔርን ስያሜ ይቀይራል የተባለ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተቃውሞ…
ቀን: March 5, 2025
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ሦስት መቀመጫና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ መቀመጫ ያለው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በክልሉ ተደረገ ያለውን ሕግን ያልተከተለ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በመቃወም አቤቱታ አሰማ፡፡ ጉዳዩ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተቋቋመው የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጥበት አቤቱታውን አስገብቷል፡፡
ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ከሰሞኑ ሁለት አዋጆች በአብላጫ ድምፅ መፅደቃቸውን ጠቁሟል፡፡ ከእነዚህ አዋጆች አንዱ ደግሞ የክልሉን ሕገ መንግሥት አንቀጾች የሚያሻሽል አዋጅ መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ቅደም ተከተልን ያልተከተለ ነው በሚል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አቤቱታ እንዲያስገባ ገፊ ምክንያት እንደሆነው ጠቁሟል፡፡
ቦሮ በመግለጫው ክልሉ የሕገ መንግሥት አንቀጾች ላይ ማሻሻያ ያደረገው አዋጅ በዋናነት ሦስት ጉዳዮችንን ይቀይራል ብሏል፡፡ አንደኛው የበርታ ብሔረሰብ ስያሜን ወደ ቤኒሻንጉልነት የሚቀይር አንቀጽ ተካቶበታል ብሏል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ የክልሉን ዓርማ የሚቀይር አንቀጽ አለበት ብሏል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ማሻሻያ አዋጁ የክልሉን ምክር ቤት መቀመጫዎች ቁጥር ከ99 ወደ 165 የሚቀይር እንደሆነም ጠቁሟል፡፡
ሕገ መንግሥት ሲሻሻል በአዋጅ ማፅደቅ በድምፅ ብልጫ ብቻ ግብታዊ በሆነና ጥድፊያ በታከለበት መንገድ መሆን የለበትም ያለው ፓርቲው፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መፍትሔ እንዲሰጥበት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ አቅርበናል ብሏል፡፡
ሁለተኛውና ከሰሞኑ በተመሳሳይ ሁኔታ የፀደቀው አዋጅ ደግሞ የምርጫ ጣቢያዎችን ቁጥር ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሚጨምር እንደሆነ ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጠቁሟል፡፡ በቀደመው የክልል ሕገ መንግሥት ማሻሻያ አዋጅ ውስጥ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር ከ99 ወደ 165 የሚያሳድግ የሕግ አንቀጽ መግባቱን ተከትሎ፣ የምርጫ ጣቢያዎች በወረዳ ደረጃ እንዲጨምሩ የሚያስችል ተጨማሪ አዋጅ ተረቆ መፅደቁን ፓርቲው ተቃውሞታል፡፡
በተለይ አሶሳ ዞን ላይ ባለፉት አምስት ዓመታት ለአስተዳደር ምቹነት ተብሎ አምስት ወረዳዎች እንዲቋቋሙ መደረጉን ፓርቲው አመልክቷል፡፡ እነዚህ ወረዳዎች ለአስተዳደር ምቹነት በሚል የተመሠረቱ ቢሆንም፣ ነገር ግን የክልሉ ምክር ቤት እነዚህ ወረዳዎችን ልክ እንደ ምርጫ ወረዳዎች በመቁጠር ብቻ የክልሉን ምክር ቤት ወንበር በ31 እንዲያድግ በማድረግ ማፅደቁን ጠቅሷል፡፡
የሕዝብና ቤት ቆጠራ ጥናት ተካሂዶ፣ እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ታክሎበት የክልሉ ምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር እንዲያድግ መደረግ ነበረበት ሲል የገለጸው ፓርቲው፣ ሆኖም ከዚህ በተቃራኒው የክልሉ ምክር ቤት አዋጅ በማፅደቅ ይህን ለመተግበር እየሞከረ ነው ሲል ተቃውሞታል፡፡
ሁለቱንም አዋጆች በተመለከተ የአካሄድ ችግር ያለባቸውና መደበኛውን አሠራር የሚጥሱ መሆናቸውን ፓርቲው ገልጿል፡፡ በራሱ በምክር ቤቱ አዋጆቹ ሲፀድቁ ለምን ድምፃችሁን አላሰማችሁም ተብለው የተጠየቁት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ተሰማ፣ ከ95 ወንበር 88 የሚሆነው በገዥው ፓርቲ አባላት መሞላቱንና የእነርሱ ሦስት መቀመጫ ቢቃወሙም ውሳኔውን ለማስቀየር የሚያስችል አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ የሁለቱ አዋጆች አፀዳደቅ ሒደት የክልሉን ሕገ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ሕጎችን የሚያሟላ ነው ብለው ስለማያምኑ፣ ጉዳዩ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በኩል ውሳኔ እንዲሰጥበት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይዘውት እንዳመሩ ነው የተናገሩት፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሥር ወደ አራት ነባር ብሔረሰቦችና ሌሎች ሕዝቦች በጋራ እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ጉሙዝ፣ በርታ፣ ሺናሻና ማኦ ኮሞ ሕዝቦች ከነባሮቹ ውስጥ ሲሆኑ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬና ሌሎችም ማኅበረሰቦች በክልሉ ተሰባጥረው እንደሚኖሩ ይነገራል፡፡
ክልሉ በከርሰ ምድሩ ከፍተኛ የወርቅ ሀብት ያከማቸ ሲሆን፣ በገፀ ምድሩ ደግሞ ቀርከሀና ማንጎን ጨምሮ ብዙ ዓይነት የተፈጥሮ ሀብቶች ያለው መሆኑ ይነገራል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገንቢያ ቦታ የጉባ ባለቤት የሆነው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች ብቻ ሳይሆን ከደቡብና ሰሜን ሱዳን ጋርም ይዋሰናል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የክልሉ ፀጥታና ሰላም ሁኔታ መሻሻል እያሳየ ቢመጣም፣ ክልሉ ለበርካታ የፀጥታ ችግሮችና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ተጋላጭ ከሆኑ ክልሎች አንዱ መሆኑ ይነገራል፡፡