

ዜና ከፖለቲካ ገለልተኛ ባለመሆንና ከዓላማ ውጭ መንቀሳቀስ በሚል ታግደው የነበሩ ድርጅቶች ዕገዳ ተነሳ
ቀን: March 5, 2025
በያሬድ ንጉሤ
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከፖለቲካ ገለልተኛ አለመሆንና ከዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ዕገዳ ጥሎባቸው የነበሩ ሦስት በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ዕገዳ ማንሳቱን አስታወቀ፡፡
የተጣለባቸው ዕገዳ የተነሳላቸው የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች፣ እንዲሁም ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ የተሰኙት ሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ናቸው፡፡
ከሦስቱ ድርጅቶች መካከልም የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ‹‹ከፖለቲካ ገለልተኛ አለመሆኑንና ከዓላማው ውጪ በመንቀሳቀስ›› በሚል ዕግድ ተጥሎበት የነበረ ሲሆን፣ በታኅሳስ 2017 ዓ.ም. ዕገዳው ተነስቶለት ነበር፡፡ ይሁንና ድርጅቱ እንደገና መታገዱም አይዘነጋም፡፡
በተቆጣጣሪው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የቀረበበትን ክስ አስመልክቶም፣ ‹‹ካርድ ከዓላማው ውጪ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ውስጥ አለመሳተፉንና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ገለልተኛ መሆኑን›› በመግለጽ፣ የቀረበበትን ክስ በወቅቱ ስለማስተባበሉም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የተሰኘው የሲቪል ድርጅትም፣ ‹‹ድርጅታችሁ ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መሥራት ሲገባው ከዓላማው ውጪ በመንቀሳቀስ የአገርና የሕዝብን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት ላይ በመሥራቱ ከባድ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን ማረጋገጥ ተችሏል›› የሚለውን የባለሥልጣኑን መግለጫና ዕግድ በወቅቱ አስተባብሎ ዕግዱ ያደረሰበትን ጉዳት መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ድርጅቱ አክሎም፣ ‹‹ግልጽነት የሌለውን ምክንያት በመጥቀስ ማንኛውንም የሥራና የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ታግዶ መቆየቱን፤›› ገልጿል፡፡
‹‹ዕገዳው ለድርጅቱ ፈጽሞ የማይገባ የነበረ ከመሆኑም በላይ ተግባራዊ ሆኖ በቆየባቸው ቀናት በሠራተኞቹ መብትና ጥቅም፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ ሲሰጣቸው በነበሩ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ሊሠራቸው በዕቅድ ይዟቸው በነበሩ መርሐ ግብሮቹ፣ እንዲሁም ከድርጅቱ ጋር ውል አስረው የመጠቀሚያ ዕቃና አገልግሎቶች ባቀረቡ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ አባላትና በመንግሥት ጥቅም ላይ ጭምር ከፍተኛ ጉዳትን ያስከተለ፤›› ስለመሆኑም በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች የተሰኘው የሲቪል ድርጅትም፣ ‹‹ገለልተኛ ያለ መሆንና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ መንቀሳቀስ የሚሉት ክሶች በማስረጃ ያልተረጋገጡ በመሆናቸው፣ ማብራሪያ የሚጠይቅበት እንደሚሆን›› በመጥቀስ በታኅሳስ ወር ዕግዱ ሲነሳለት ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም አደረግኩት ባለው ክትትልና ቁጥጥር፣ ‹‹የተወሰኑ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሕግን ተላልፈው በመገኘታቸው ምክንያት ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፤›› ሲል ነው ሰኞ የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫው ያስታወቀው፡፡
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ፣ ‹‹በታገዱ ድርጅቶች ላይ የምርመራ ሥራውን በማጠናቀቁ፣ በውጤቱ ላይ ከሲቪል ድርጅቶቹ ጋር በመነጋገር መታረም የሚገባቸው እንዲታረሙ፣ እንዲሁም በቀጣይ ጊዜ በጋራ ለመሥራት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፤›› ብሏል፡፡
ሊታረሙ ይገባሉ ስለተባሉት ተግባራት ግን በዚሁ መግለጫ ላይ ያለው ነገር የለም፡፡ ‹‹በዕግዱ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አመራሮች ጋር ምክክር ከተደረገና ኮሚሽኑ የሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦች መሠረት አድርጎ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዘርፉ እንዲጎለብት ካለው ቁርጠኝነት፣ እንዲሁም ከተቋማቱ ጋር የተደረገውን ውይይት ተከትሎ ከየካቲት 24 አንስቶ ዕግዱ በማስጠንቀቂያ እንዲነሳ ስለመደረጉም›› አስታውቋል፡፡
በባለሥልጣኑ ሆነ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኩል ኮሚሽኑ የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ምን እንደሆኑ በግልጽ ይፋ አልተደረገም፡፡
ኢሰመኮ ስለዚሁ ዕግድ መነሳት ሰኞ የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በታኅሳስ ወር በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ ዕገዳዎች በሲቪል ማኅበራት የመደራጀት መብቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ስለማሳሰቡ አስታውሷል፡፡
ኮሚሽኑ በታኅሳስ ወር ባወጣው መግለጫው፣ ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተመሳሳይ ይዘት ባለውና ተቋማቱ የፈጸሟቸውን ከባድ የሕግ ጥሰቶች በዝርዝር ባላስቀመጠ ደብዳቤ መታገዳቸው አሳሳቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤›› ማለቱንም ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ በተለይ በቅርቡ በተሾሙት ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ አማካይነት ጉዳዩን በልዩ ትኩረት በመከታተል፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንና ዕገዳ ከተጣለባቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ ለጉዳዩ መፍትሔ ለማስገኘት ሲሠራ መቆየቱን አስታውቋል፡፡