ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቁጣ፣ ተግሳጽና ክርክር የተሞላበት ውይይት ከፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ጋር አድርገዋል (ጌቲ ኢሜጅ)

ዓለም ዘለንስኪን ጨምሮ የትራምፕና የአውሮፓ መሪዎች ፍጥጫ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: March 5, 2025

ሰኞ (እ.ኤ.አ. ማርች 3) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ ለጊዜው ማቋረጧን አስታውቀዋል፡፡ ትዕዛዙ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በዝውውር የሚገኝን የጦር መሣሪያዎች ይመለከታል ሲሉ የዓለም አቀፍ መገናኛ አውታሮች የትራምፕን ከፍተኛ አማካሪዎች ዋቢ በማድረግ ዘግበዋል፡፡

ዘለንስኪን ጨምሮ የትራምፕና የአውሮፓ መሪዎች ፍጥጫ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በአሜሪካ ፊት ለተነሱት ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በለንደን አቀባበል አድርገውላቸዋል (ጌቲ ኢሜጅ)

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ባለፈው ዓርብ አሜሪካን ሲጎበኙ በነጩ ቤተ መንግሥት ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ከምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር፣ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ የተላለፈ ቆይታ አደረጉ፡፡ ዘለንስኪና ትራምፕ እጅግ የተወራለትን የዩክሬንን እጅግ ውድ ማዕድናት ለአሜሪካ አልሚዎች ክፍት የሚያደርግ ውል ይፈርማሉ ተብሎ ነበር፡፡ ከፊርማው በፊት ግን ዘለንስኪ አሜሪካ ለዩክሬን የደኅንነት ጥበቃ ቃል እንድትገባ ሲጠይቁ ትራምፕ ተቆጡ፡፡ ጭቅጭቅና ጩኸት ሰፈነ፡፡ ዓለም ከመጋረጃ ጀርባ ሊሆን የሚችልን ክስተት በቀጥታ ተመለከተ፣ አዳመጠ፡፡ ‹‹ሆነ ብዬ ነው ያረዘምኩት ቆይታችንን፣ የአሜሪካ ሕዝብ ይህን መስማት ይኖርበታል፤›› ሲሉ የተደመጡት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ለ‹‹ፖለቲካ ትክክለኛነት›› (Political Correctness) ቁብ የማይሰጡ፣ አቅጣጫቸውን ከማፍረጥ ወደኋላ የማይሉ መሪ መሆናቸውን በድጋሚ አስመሰከሩ፡፡

የዓርቡ አጨቃጫቂ ጉዳይ ግን እቅጩን ከማፍረጥ አልፎ የአሜሪካንና የዩክሬንን የወደፊት ግንኙነት የሚወስን ከመሆኑ ባሻገር፣ ተሻጋሪውን የአትላንቲክ ውቅያኖስ (Trans Atlantic) የአሜሪካንና የአውሮፓን ግንኙነት ሊጎዳ እንደሚችል ይታመናል፡፡ ለዚህ ነበር ከጭቅጭቁ በኋላ ለአለመግባባቱ ማን ምክንያት እንደሆነ በአሜሪካ ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች መካከል ሰፊ የአመለካከት ልዩነቶች ከመንፀባረቃቸው ባሻገር፣ በርካታ የአውሮፓ መሪዎች ደግሞ ዘለንስኪን ከማሞካሸት ባለፈ አጋርነታቸውን እየገለጹላቸው ነው፡፡

ዓርብ ዋሽንግተን የነበሩት ዘለንስኪ የተያዘላቸው መርሐ ግብር ከመጠናቀቁ በፊት ነጩን ቤተ መንግሥት ለቀው እንዲወጡ ‹‹ከተጋበዙ›› በኋላ ነበር፣ በረው ሰፊውን አትላንቲክ በማቋረጥ ቅዳሜ በእንግሊዝ ዋና ከተማ ለንደን የደረሱት፡፡ እዚያ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር የዘለንስኪን የዋሽንግተን ዲሲ ስብራት ባይጠግንም፣ መፅናኛ ሊሆን በሚችል ሁኔታ ብሎም ለአሜሪካ አመራሮች ትምህርት እንዲሆን የታለመ ትዕምርታዊ አቀባበል ያደረጉላቸው፡፡ ወትሮ የለንደን እንግዶች ዳውኒንግ ጎዳና (Downing Street) በሚገኘው አሥር ቁጥር ያለበት ከውጭ ሲመለከቱት እዚህ ግባ የማይባል ጠየም ያለ በር ላይ ከመኪና እንዲወርዱ ይደረጋል፣ በሩ ይከፈታል፣ እዚያው ይገባሉ፡፡ ስታርመር ዘለንስኪን የተቀበሉት ግን እንዲያ አልነበረም፡፡ በሩ ላይ ቆመው ጠበቋቸው፣ የዘለንስኪ መኪና አሥር ቁጥር በር ከመድረሱ በርካታ ሜትሮች በፊት ቆመ፣ ዘለንስኪ ወረዱ፡፡ ስታርመር ወደ ዘለንስኪ ፈጠኑ፣ መሀል መንገድ ተገናኙ፣ በፈገግታ አቀፏቸው፡፡ ይዘዋቸውም ወደ ታዋቂው አሥር ቁጥር ቢሯቸው ዘለቁ፡፡ ቢቢሲ ይህን አቀባበል ‹‹በእጅጉ ትዕምርታዊ አንድምታ ያለው›› ሲል ገልጾታል፡፡

የስታርመርና የዘለንስኪ ውይይት ለዩክሬን መሣሪያ ግዥ የሚሆን 2.2 ቢሊዮን ፓውንድ ዩናይትድ ኪንግደም የለገሰችበት ነበር፡፡ የዩናይትድ ኪንግደም የጦር ዕርዳታ ባልተገመተ ሁኔታ ዳጎስ ያለ ቢመስልም፣ ዩክሬን ከአሜሪካ ካገኘችውና ልታገኝ ከምትችለው ሲነፃፀር ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ትራምፕ ዩክሬን ከአውሮፓ ልታገኝ የምትችለው የትኛውም ከፍተኛ መጠን ዕርዳታ ጦርነቱን ሊያሸንፍላት እንደማይችል ጠንቅቀው በማወቃቸው ነው በነጩ ቤተ መንግሥት ውይይታቸው፣ ‹‹አንተ መጫወቻ ካርድ አልቆብሃል፣ ከእኛ ጋር ስትሆን ካርዶቹን ማግኘት ትጀምራለህ፤›› ብለው ዘለንስኪን ሲያንኳስሱ የተደመጡት፡፡ የሆነ ሆኖ ስታርመር ወደ ዩክሬን ወታደሮችና ጄቶች በመላክ ሩሲያን እንዋጋለን እስከማለት ደርሰዋል፡፡

እዚህ ጋ ከነበረው እሰጥ አገባ በቀጥታ አማርኛ ትርጉም መቋደስ አይከፋም፣ (ተቀንጭቦ የቀረበ ነው)፡፡

ዘለንስኪ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ጦርነት ለማንም ቢሆን ችግር ነው፣ ለእናንተም  (ለአሜሪካም) ሳይቀር፡፡ ግን ለእናንተ ውቅያኖሱ (በመሀል) አለ፣ እናም አሁን አይሰማችሁም፡፡ ለወደፊት ግን ታዩታላችሁ (ይሰማችኋል…)፡፡

ትራምፕ፡- ምኑን አውቀኸው? ምኑን አውቀኸው? ምን እንደሚሰማን አትንገረን፡፡ እኛ ችግር ለመፍታት ነው እየጣርን የምንገኘው፡፡ ምን ሊሰማን እንደሚችል አትንገረን፡፡

ዘለንስኪ፡- እየነገርኳችሁ አይደለም፡፡ ጥያቄዎቹን እየመለስሁ ነኝ፡፡

ትራምፕ፡- ምክንያቱም አንተ ያን ለማለት የሚያበቃ ሁኔታ ላይ አይደለህም፡፡

ቫንስ፡- እያደረግህ ያለኸው ያንኑ ነው፡፡

ትራምፕ፡- ምን ሊሰማን እንደሚችል ለእኛ የመንገር ሁኔታ ላይ አይደለህም ያለኸው፡፡ እኛ በእጅጉ ጥሩ (ማለፊያ) ነው የሚሰማን፡፡

ዘለንስኪ፡- ጫና እንዳደረባችሁ ይሰማችኋል፡፡

ትራምፕ፡- እኛ እጅግ ማለፊያ ስሜትና ጥንካሬ ነው የሚሰማን፡፡

ዘለንስኪ፡- ምን አለ በሉኝ ጫና ምን እንደሆነ ይሰማችኋል፡፡

ትራምፕ፡- አሁን አበዛኸው፣ ጥሩ ሁኔታ ላይ አይለህም፡፡ ራስህን መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ከተትህ፡፡

ዘለንስኪ፡- ከጦርነቱ ከመጀመሪያ አንስቶ…

ትራምፕ፡- ጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለህም፣ አሁን (መጫወቻ) ካርዶች የሉህም፡፡ ከእኛ ጋ ካርዶቹን ማግኘት ትጀምራለህ፡፡

ዘለንስኪ፡- ‹‹ካርታ እየተጫወትሁ አይደለሁም፣ እጅግ ከምሬ ነው፣ ሚስተር ፕሬዚዳንት፣ እጅግ የምሬን ነው የምነግርህ፡፡

ትራምፕ፡- ካርታ እየተጫወትህ ነህ፡፡ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እየተጫወትህ ነህ፡፡ በሦስተኛ የዓለም ጦርነት እየቆመርህ ነህ፡፡

ዘለንስኪ፡- ስለምንድነው እየተናገርህ ያለኸው?

ትራምፕ፡- በሦስተኛ የዓለም ጦርነት እየቆመርህ ነው፡፡ በርካታ ሌሎች እኛ ማድረግ የነበረብን ብለው ከሚያስቡት እጅግ በላቀ የደገፈህን ይህንን አገር፣ ለዚህ አገር ንቀት ነው እያሳየህ ያለኸው፡፡

ቫንስ፡- አንዴ እንኳን አመሠግናለሁ ብለሃል?

ዘለንስኪ፡- ብዙ ጊዜ፣ ዛሬም ሳይቀር ብያለሁ፡፡

ቫንስ፡- በዚህ ስብሰባ እስካሁን አላልክም፣ ባለፈው ጥቅምት ፔንሲልቫኒያ ሄደህ ለተቀናቃኙ የምርጫ ቅስቀሳ አድርገሃል፡፡

ዘለንስኪ፡- አላደረግሁም፡፡

ቫንስ፡- እስቲ አገርህን ለማዳን እየሞከሩ ላሉት ለዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካና ለፕሬዚዳንቱ ትንሽ እንኳን አድናቆት ብትገልጽ?

ዘለንስኪ፡- እባክህ፣ ይመስልሃል (?) ስለጦርነቱ ጮክ ብለህ ስለተናገርህ…

ትምራፕ፡- አልጮህኩም፣ አልጮህክም፣ አገርህ ትልቅ አደጋ ውስጥ ናት፡፡

ዘለንስኪ፡- መልስ መስጠት እችላለሁ (?)

ትራምፕ፡- የለም፣ የለም፡፡ ብዙ ተናግረሃል፡፡ አገርህ ትልቅ አደጋ ውስጥ ናት፡፡

ዘለንስኪ፡- አውቃለሁ፣ አውቃለሁ፡፡

ትራምፕ፡- እያሸነፍህ አይደለህም፡፡ ይህንን (ጦርነት) እያሸነፍህ አይደለህም፡፡ እኛ ስላለን ነው (አገርህ) መትረፍ የቻለችው፡፡

ዘለንስኪ፡- ሚስተር ፕሬዚዳንት እኛ አገራችን ውስጥ በጥንካሬ ፀንተናል፡፡ ከጦርነቱ ጅማሮ አንስቶ ብቻችንን ነን፡፡ ደግሞ እኮ ምሥጋናም አልነፈግንም፣ እናመሠግናለን፡፡

ትራምፕ፡- የእኛን የጦር መሣሪያ ባታገኝ ኖሮ ጦርነቱ በሁለት ሳምንት ባለቀ ነበር፡፡

ዘለንስኪ፡- በሦስት ቀን፣ ከፑቲን (የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን) ሰምቻለሁ፣ በሦስት ቀናት፡፡

ትራምፕ፡- ምናልባትም ባነሰ፡፡ በእንዲህ ባለ ሁኔታ ተግባብቶ አብሮ መሥራት እጅግ አዳጋች ነው የሚሆነው፣ ነገርኩህ፡፡

ቫንስ፡- በቃ፣ አመሥግን (አመሠግናለሁ በል)

ዘለንስኪ፡- ብዙ ጊዜ አልሁ፡፡ አመሠግናለሁ፣ የአሜሪካን ሕዝብ፡፡ 

ቫንስ፡- አለመግባባት እንዳለ ተቀበል፣ ከዚያም እነዚያን አለመግባባቶች እንፍታቸው፡፡ ስህተት እንደሠራህ እናውቃለን፣ እናም እሰጥ አገባውን ካሜራ ፊት ከማድረግ ይልቅ…

ትራምፕ፡- ግን ልብ በሉ፡፡ የአሜሪካ ሕዝብም ምን እንደተካሄደ ማወቁ ጥሩ ነው፡፡ እጅግ ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚያም ነው ይህን እስካሁን እንዲዘልቅ ያደረግሁት፡፡ አመሥጋኝ መሆን ይኖርብሃል (ለዘለንስኪ)፡፡

ዘለንስኪ፡- አመሥግኛለሁ፡፡

ትራምፕ፡- ካርዶች ጨርሰሃል፣ እዚያ ተቀብረሃል፡፡ ሰዎች እየሞቱ ነው፣ ወታደሮችህ ተመናምነዋል፡፡ (እኛ የምንልህ) መልካም ሆኖ ሳለ አንተ ግን ‹‹ተኩስ አቁም አልፈልግም፣ ይኼ ይሻለኛል፣ እሄዳለሁ…›› ሰማህ አሁኑኑ ተኩስ አቁም፣ ማድረግ ከቻልክ ተቀበል፣ ከዚያ ቀለሆች አይወነጨፉም፣ ወታደሮችህም (እየተማገዱ) አይሞቱም፡፡

ዘለንስኪ፡- እርግጥ ነው ጦርነቱ እንዲቆም እንፈልጋለን፣ ሆኖም እንደነገርኩህ ከመተማመኛ ጋር፡፡

ይህ የመጨረሻው የዘለንስኪ ‹‹እምቢተኝነት›› ለ15 ደቂቃ አካባቢ ለዘለቀው ጭቅጭቅ እንደ ጡዘት የሚቆጠር ነበር፡፡ ሰውየው በጄ አይልም፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ ይዞ የመጣው የዩክሬንን አቋም ብቻ ሳይሆን የአውሮፓን መሪዎች (የእንግሊዝ፣ የፈረንሣይ፣ የፖላንድ፣ የኔዘርላንድስ፣ የስፔን፣ ወዘተ) አደራ ጭምር ነው፡፡ እነዚህ የአውሮፓ ኃያላን ቀድሞውኑ የዩክሬን ደኅንነት የአውሮፓ ደኅንነት አካል መሆኑን ሲናገሩ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡

እናም የነጩ ቤተ መንግሥት ጭቅጭቅ ብዙም ሳይዘልቅ በአጭር ተቀጨ፡፡ የዩክሬንን ‹‹ሬር ኧርዝ›› ማዕድናት ለአሜሪካ ክፍት በማድረግ ከሚገኘው ገቢ ከፊሉን ለዩክሬን መልሶ ግንባታ እንዲውል ያስችል እንደነበር ብዙ የተነገረለትና የተጓጓለት ስምምነትም ውኃ በላው፡፡ ዘለንስኪም ምሳ እንኳ ሳይቀምሱ ‹‹ለሰላም ዝግጁ ሲሆኑ ተመለሱ›› ተብለው በተዘጋጀላቸው ሼቭሮሌት ጥቁር ኤስዩቪ እብስ አሉ፡፡ የነጩ ቤተ መንግሥት ሞላላው ሳሎን መጋረጃ ወረደ፡፡

ሊንዚ ግራሃም የሪፐብሊካን ሴናተር ናቸው፡፡ የማዕድኑን የውል ሐሳብ ያመነጩትና ውሉንም በወረቀት ያዋቀሩ እሳቸው እንደሆኑ ይነገራል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የዓርቡ የሞላላው ሳሎን እሰጥ አገባ አሜሪካ ለወደፊት ለኪየቩ ልትሰጥ የነበረውን የጦር ዕርዳታ አደጋ ላይ የጣለ ነው፡፡ በክርክሩ ወቅት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጥሩ አድርገዋል፡፡ የአሜሪካን ፍላጎት አስጠብቀዋል፡፡ አሜሪካ ለወደፊት ከዘለንስኪ ጋር መሥራት ትችል እንደሁ እንጃ…›› በማለት ዘለንስኪ ሥልጣን መልቀቅ እንደሚኖርባቸው መናገራቸውን ቢቢሲን ጨምሮ በርካታ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ዘግበዋል፡፡

ቴነሲን በመወከል የሪፐብሊካን ሴናተር የሆኑት ቢል ሃገርቲ በኤክስ ገጻቸው፣ ‹‹ዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ ከእንግዲህ እንደተፈለገች የምትሾር አትሆንም፤›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡

የአላባማ ሴናተር ቶሚ ቱበርቪል በበኩላቸው በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት አስተያየት፣ ‹‹እስካሁን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከከወኗቸው ሥራዎች ውስጥ ምርጡ ያንን ዩክሬናዊ ዓይጠ መጎጥ (Weasel) ከነጩ ቤተ መንግሥት ጠልዘው ማባረራቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዴሞክራቶች ግን በትራምፕና በምክትላቸው ላይ የሰሉ ትችቶች ሰንዝረዋል፡፡ የሴኔት ህዳጣን መሪ የሆኑት ቸክ ሹመር፣ ‹‹ትራምፕና ቫንስ የፑቲንን ቆሻሻ ሥራ እያስፈጸሙ ነው፤›› ሲሉ፣ ሴናተር ክሪስ ኩንስ ደግሞ የሞላላው ሳሎን ሁኔታ ለዘለንስኪ አይገባም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እሑድ (እ.ኤ.አ. March 2) የአውሮፓ መሪዎች፣ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽንና የአውሮፓ ኅብረት ካውንስል ኃላፊዎች፣ የካናዳው ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (NATO) ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ የስብሰባው ታዳሚ ለሆኑት ዘለንስኪ ውዳሴና የአጋርነት ቃል ተዥጎድጉዶላቸዋል፡፡ ሐሙስ (እ.ኤ.አ. ማርች 6) ለዩክሬን ልዩ የአውሮፓ ኮሚሽን የመከላከያ ዕርዳታ ጥቅል የሚቀርብላቸው መሆኑን የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ይህ በአውሮፓ፣ በካናዳና በዩክሬን መካከል የሚደረግ የተጠናከረ አጋርነት በአሜሪካ መንግሥት ቅቡልነት የሚቸረው አይመስልም፡፡ ለአሁኑ በትራምፕ ዓይን ከዘለንስኪ ይልቅ የሩሲያው ፑቲን ለሰላም የተሻለ ዝግጁ ናቸው፡፡

(ጥንቅር፡- በአዲስ ጌታቸው)