
https://www.ethiopianreporter.com/138975/
ከግራ ባህሩ ዘውዴ (ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር) ምሕረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) እና ገዛኸኝ ፀጋው (ዶ/ር
ኪንና ባህል የዓድዋ ድል ትሩፋት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲዘከር
ቀን: March 5, 2025
ጎንደር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ገናና ስም አላት፡፡ ጎንደር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ማዕከል ሆና ብዙ የነፃነት፣ የታሪክ፣ የድል፣ የሥነ ጽሑፍና የኪነ ጥበብ ሥራዎችንም አጉልታ ለማሳየት የቻለች ነች፡፡ የኢትዮጵያን ስምና ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ያደረጉ ጀግኖችንም ማኅፀን ለምለም ጎንደር ለማፍራት ችላለች፡፡ በተለያዩ የታሪክ ድርሳንም ስሟ በወርቅ ቀለም ተከትቦ ይገኛል፣ እናትዋ ጎንደር፡፡

በታሪካዊቷ ከተማ የሚገኘው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ ዓመትና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አስመልክቶ ‹‹የኢትዮጵያ ቀን – በኢትዮጵያዊው ተቋም›› በሚል መሪ ቃል 129ኛውን የዓድዋ ድል በዓል የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ዘክሮ ውሏል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሥራት አፀደ ወይን (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በዓድዋ በጠላት ላይ የተቀዳጀነው ድል ለአገር ዕድገት የተደረጉ ተጋድሎዎችና ገድሎች ናቸው፡፡ በፅናትና በማይበገር የኢትዮጵያዊነት ወኔ የተጻፈ የነፃነት ድርሳናት ቢኖር የዓድዋ ድል ነው ብለዋል፡፡
የዓድዋ ጦርነትና ገድል ደርዝ ካላቸውና ደማቅ ከሆኑ የ19ኛው ክፍለ ዘመን የታሪክ ሁነቶች አንዱ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በርካታ የታሪክ ጸሐፍት የሥነ ጥበብና የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ስለዓድዋ ታሪክ በሰፊው ጽፈውና በቀለም ከትበው አኑረውታል፡፡ ገድሉንም በጥናት አስደግፈው አስነብበውናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክን በጥልቀት የፈተሹትና በዘርፉም በርካታ ጥናቶችን ያካሄዱት ባህሩ ዘውዴ (ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ከዓድዋ እስከ ማይጨው›› በሚለው ዘመናዊ የኢትዮጵያ የታሪክ መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድል የቅኝ ገዥዎችን መንፈስ በመስበር ለጎረቤት አገሮች፣ ለአፍሪካ፣ ለቅኝ ገዥዎችና ዘረኝነት ሥር በሰደደባቸው አገሮች ሁሉ ያስገኘውን ውጤትና ፋይዳ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ወራሪ ጠላትን ድል ያደረጉበት ብቻ ሳይሆን አንድነትና ኅብረታቸው ያፀኑበት ነው፡፡ ከዳር እስከ ዳር በአንድ ልብና ሐሳብ በመቆም ለትውልድ የነፃነት ሐውልት አቁመው ያለፉበት ሁኔታ ስለመኖሩም ነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት የተናገሩት፡፡
‹‹የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን የአገር ፍቅር ስሜትና የብሔራዊ ክብር ዓርማ ነው፡፡ ቀደምት እናቶችና አባቶች በመተሳሰብ፣ በመደማመጥና በመግባባት ወራሪውን የፋሺስት ጦር ድባቅ መተው ነፃነትን በደምና በአጥንታቸው እንድንጎናፀፍ አድርገውልናል ብለዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ፣ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፣ የመላ ጥቁር ሕዝቦች ድል ነው፡፡ ዓድዋ በዓለም ታሪክ ውስጥ በተለይ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ የደመቀ ሥፍራ አለው፡፡ በመሆኑም ትውልድ በአንድነትና በትብብር መንፈስ በመቆም የአባቶቹን የጀግንነትና የአንድነት ታሪክ ማፅናት ይኖርበታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ባህሩ ዘውዴ (ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር) ‹‹የዓድዋ ድልና ፓን አፍሪካኒዝም›› በሚል በበዓሉ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ እንደገለጹት፣ ዓድዋ አንድነትና የዓላማ ፅናት የተጋመዱበትና ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን መላ ጥቁር ሕዝቦችን ያስተሳሰረ ታሪካዊ ሁነት ነው፡፡
የዓድዋ ድልን ተከትሎ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ስም በዓለም አደባባይ በደማቅ ቀለም ሊጻፍ ችሏል፡፡ የአፄ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱና የኢትዮጵያውያን ገደል የታሪክ ድርሳናት መዝግበውት ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰሩ፣ ጭቆናና የዘር አድልዎ፣ እንዲሁም ግፍ በበዛባቸው እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካና ሌሎችም በቅኝ ግዛት ውስጥ ለሚኖሩ አገሮች የኢትዮጵያ ድል ለነፃነት ለሚከፍሉት መስዋዕትነት ስንቅ ለመሆን የቻለ ነው፡፡
ዓድዋ ለፓን አፍሪካኒዝም ጥንስስ ነው፡፡ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብንም መስፋፋትን የሰበረ፣ እንዲሁም የነጮች የበላይነትን በመድፈቅ የአፍሪካን አንድነት ዕውን ለማድረግ መንገድ ጠራጊ መሆን የቻለ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ የጀግንነትና የነፃነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትቆጠረው ለፓን አፍሪካኒዝም መመሥረት መሠረት በመሆኗ ነው፤›› የሚሉት ባህሩ (ፕሮፌሰር)፣ ዓድዋ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል በቅኝ ግዛት ሥር ለወደቁ የአፍሪካና ሌሎች ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት ሊሆን በመብቃቱ ከድል በኋላ የፓን አፍሪካኒዝምና ኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴዎች ጎልተው እንዲወጡ ያስቻለ ነው፡፡
እንደ ፕሮፌሰሩ፣ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ለአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት መመሥረት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡ እንቅስቃሴውም ከሰሜን አሜሪካና ከካሪቢያን አገሮች በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ የተደረገውም የዓድዋ የድል መንፈስ ባረበበባቸው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ የጀግንነት፣ የአልበገር ባይነትና የነፃነት ምልክቱ ነው፡፡ ለመላ ጥቁር ሕዝቦችም ካጎነበሱበት አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ ብርታት የሆናቸው ስለመሆኑም ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
በሚኒስትር ደኤታ ማዕረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ምሕረቱ ሻንቆ (ዶ/ር)፣ በበዓሉ ላይ ‹‹ኢትዮጵያዊነትና ብዝኃነት›› የሚል ጽሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡ ‹‹ታሪክ በሦስት እግር ባለው በርጩማ ወንበር ይመሰላል፡፡ ትናንት፣ ዛሬና ነገ መቆሚያ ምርኩዛችን ነው፡፡ ባለሦስት እግር የበርጩማ ወንበር አንዱ ከተሰበረ አገልግሎት እንደማይሰጥ ሁሉ ትናንት ከሌለ ዛሬ፣ ዛሬ ከሌለ ደግሞ ነገን ለማሰብ የሚቸግር ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
በመሆኑም ትናንት አባቶቻችን በደምና በላባቸው አቅልመው የሰጡን የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የብዝኃነት ድል ነው፡፡ ከድሉ ፊትም ሆነ ከድሉ ጀርባ የሚገኘው ብዝኃነት መሆኑንም አስምረውበታል፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ሦስት ነገሮች ናቸው፡፡ እነሱም መገኛ ሕዝብና ሥርዓት ናቸው፤›› የሚሉት ምሕረቱ (ዶ/ር)፣ ‹‹እነዚህም በብዝኃነት የታጀቡ በመሆናቸው በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር የሚገባ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
በብዝኃነት ላይ የተጋረጡ ችግሮችንም ከዛሬ ነገ ይሻላል፡፡ ከመነጣጠል አብሮነት ይሻላል የሚል ዕሳቤ ትውልዱ በመሰነቅ ልዩነትን እያስማማ አገር ማስቀጠል እንዳለበት ምሕረቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ‹‹የኢትዮጵያ ቀን›› በማለት 129ኛውን የዓድዋ ድል በዘከረበት በዓል ገዛኸኝ ፀጋው (ዶ/ር)፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነትና ኪነ ጥበብ›› የሚል ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ አባት አርበኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም የበዓሉ ታዳሚዎች ሆነዋል፡፡