ኪንና ባህል
‹‹የፒያሳ ቆሌዎች›› የጃፓናዊው በረከት

አበበ ፍቅር

ቀን: March 5, 2025

ኢትሱሺ ካዋሴ (ዶ/ር) ጃፓናዊ አንትሮፖሎጂስት የፊልም ባለሙያና ገጣሚ ነው፡፡  ካዋሴ (ዶ/ር) ሕይወቱ ከሙዚቃ ጋር የተሳሰረች የሙዚቃ ምርኮኛ ነው ይሉታል በቅርበት የሚያውቁት፡፡ ታድያ ‹‹ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነው›› እንደሚባለው ካዋሴ በሰሜን ኢትዮጵያ ስለሚገኙ አዝማሪዎች ዝና ሰምቶ ጊታሩን በጀርባው አዝሎ  ከሩቅ ምሥራቅ ጃፓን ተነስቶ 10 ሺሕ ገደማ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ መዳረሻውን  ኢትዮጵያ ካደረገ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ ካዋሴ (ዶ/ር) ማረፊያውን አዲስ አበባ ያድርጎ ለአንትሮፖሎጂስት ጥናቱ የሚሆነው አካባቢ ሲመርጥ የጎንደር አዝማሪዎች ለግብዓቱ ተመራጭ እንደሆኑ ባገኘው መረጃ መሰረት ሳይውል ሳያድር በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ ተጉዞ  ሸዋ፣ ወሎና ጎጃም አቋርጦ መዳረሻውን  ጎንደር ከተማ ኢትዮጵያ ሆቴል አድርጎ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

‹‹የፒያሳ ቆሌዎች›› የጃፓናዊው በረከት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ስለ ጎንደር ውበትና እንግዳ አቀባበል ተናግሮ የማይጠግበው ካዋሴ (ዶ/ር) ‹‹ጎንደሬዎች እንብላ እንጠጣ ማለት ልዩ ባህላቸው ነው፤›› ይላል፡፡

የመተባበርና የመተጋገዝ እንዲሁም ታላላቆችን የማክበር ባህላቸው ከአገሩ ከጃፓኖች ባህል ጋር ተመሳሳይነት ስለመኖኑ የሚናገረው ካዋሴ (ዶ/ር) ነገር ግን እነዚህ ባህሎች በጃፓን እየተዳከሙ ስለመሆናቸው ያክላል፡፡

ካዋሴ (ዶ/ር) ጎንደርን ከእግር እስከ ራሷ ያውቃታል፡፡ ባህሉን ተላብሶ ከማኅበረሰቡ ጋር ተግባብቶ  የበሉትን በልቶ የጠጡን ጠጥቶ በደስታቸው ተደስቶ በሐዘናቸው አዝኖ ቀላል የማይባሉ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ የጎንደር ፍቅር እንደዋዛ ተጋብቶበት በቀላሉ ሊለቀው  አልቻለም፡፡  ከጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር አብሮ ማዕድ ተቋድሷል የሴተኛ አዳሪዎች ውሎና አዳርን በቅርበት ተመልክቷል፡፡

ከጎንደር አዝማሪዎች ጋር ጓደኝነት ገጥሞ ማሲንቋቸውን በመከርከር ተጫውቷል፡፡ በወቅቱ   በአገሬው ዘንድ ሸክላ ሠሪ ቀጥቃጭ አዝማሪ እየተባሉ ይሰደቡ ከነበሩ ጥበበኞች ጋር በቅርበት ተነጋግሯል፡፡

ከሕፃናት እስከ አዋቂ ከአርሶ አደር እስከ ከተሜ ያሉትን  በገቡበት ገብቶ በወጡበት ወጥቶ  ጎንደሬዎች ጋር  ተዛምዷል፡፡

‹‹ምንም እንኳን መርዳት ባልችል ነገር ግን ሴተኛ አዳሪዎችም ሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለምን ወደዚህ ተግባር እንደገቡ በቅርበት ተረድቼ ብዙ አሳዛኝ  ገጠመኞችን ለማየትና ለመስማት  ሞክሪያለሁ፤›› የሚለው ካዋሴ (ዶ/ር)፣ የዕለት ተዕለት ውሎ አዳሩን ከእነዚህ ሰዎች ጋር ቢያደርግም የመጣበትን ዓላማ አልዘነጋም ነበረ፡፡

ይልቁንስ በሰሜን ኢትዮጵያ ስላሉ አዝማሪዎችና የጎዳና ተዳዳሪዎች  በአጠቃላይ  በጎንደር ከተማ  ተዘዋውሮ የተመለከተውን የኑሮ ውጣ ውረድ በመዘገብ ‹‹ኬዮቶ ሸምቡን (Koyote Shimbum) ከተባለ  የጃፓን ጋዜጣ ላይ ‹‹ሞደርን ወርልድ (Modern Words) በሚል ዓምድ ሥር ያሳትማቸው ነበር፡፡

በዚሁ ጋዜጣ ላይ ታትመው የሚወጡ ታሪኮችንና ሌሎች በቆይታው የታዘባቸውን ሁሉ በማሰባሰብ በጃፓንኛ ቋንቋ በመጽሐፍ መልክ አሳትሞ ለንባብ አብቅቷቸዋል፡፡

በጃፓንኛ ቋንቋ የተጻፈው መጽሐፍ ሚስችፍ ኦፍ ዘ ጋድ (Mischief of the Gods) በሚል ርዕስ ጄፍሪ ጀንሰን የተባለ ሰው ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የቀየረው ሲሆን መጽሐፉ በዓለማየሁ ታዬና በያዕቆብ ብርሃኑ ‹‹የፒያሳ ቆሌዎች›› በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተመልሶ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ተመርቆ ለንባብ በቅቷል፡፡ ደራሲው በመጽሐፍ መግቢያ ላይ ‹‹የደራሲው ቀዳሚ ቃል›› በሚል እንዴት እንደገባና ማኅበረሰቡ ስላደረገለት አቀባበል ገልጿል፡፡

‹‹መጽሐፍ በዋናነት በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ስለከተመችው ጎንደር ከተማ ውሎና አዳር የሚያትት ነው፡፡ ጎንደር ከተማን ለመጀመርያ ጊዜ ያየኋት 2001 እ.ኤ.አ. ነበር፡፡ የመስከረም 11ዱ የኒውዮርክ ከተማ መንትያ ሕንፃዎች ሰቅጣጭ የሽብር አደጋ ከተከሰተ ከቀናት በኋላ ከጃፓን ተነስቼ በካይሮ አድርጌ የአገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ገባሁ፡፡ ዓላማዬ ለአንትሮፖሎጂ ጥናቴ የመስክ ምልከታ ማድረግ ነበር፡፡ ዝንብ እየወረረኝ በአፍሪካ የተራራማና ከረብታማ መልከዓ ምድሮች ላይ ረዥም የአውቶቡስ ጉዞ አደረግኩ፡፡ ገና ከአገሬ ሳልነሳ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ስለሚኖሩ አዝማሪዎች በዝና

ሰምቼ ወደ ጎንደር አቀናሁ፤›› ሲል ስለአመጣጡ አስረድቷል፡፡

‹‹ጎንደር በጥንት ዘመኗ የነገሥታት እና ነገሥታቱን እንዲሁም መኳንንቱን የሚያጫውቱ የአዝማሪዎች ማደሪያ ነበረች፡፡ አዝማሪዎች ዛሬም በከተማዋ ውስጥ አሉ፡፡ ከተማዋ ጥናቴን ለማድረግ የተመቸች መሆኗን ካረጋገጥኩ በኋላ ማረፊያዬን ረከስ ያለ ዋጋ የሚያስወጣኝ በጣሊያን ወረራ ወቅት የተሠራው የኢትዮጵያ ሆቴል አደረግሁ፡፡ ከተማዋ ነዋሪዎች ብዙ ታሪኮችን ተጋራሁ፡፡

‹‹አንዳንዶች የከተማዋ ነዋሪዎች ታሪኮቻቸውን ሳይፈሩና ሳይደብቁ ነገሩኝ፡፡ ሌሎች ሹክሹክታን መረጡ፡፡ ብቻዬን ስሆን ዓይኖቼን ጨፍኜ የሰማኋቸውን ታሪኮች እንደገና አሰላስላቸዋለሁ፡፡ የከተማዋ የመንገድ ላይ ነዋሪዎች ታሪኮች ከበቡኝ ወረሩኝ፡፡ እነዚህ ታሪኮች እኔ በሠለጠንኩበት በአንትሮፖሎጂካዊ ልኬት በቁጥር፣ ወይ በእውነታ ብቻ የሚዳኙ አልሆኑም፡፡ ሆኖም በምችለው ሁሉ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደሆኑት እንደ ልሳን ልሆናቸው ሞክሬያለሁ፡፡ እልፍ ታሪኮችን ሰማሁ፡፡ በንግግር፣ በአጭር ልብወለድ መልክ፣ በግጥም፣ አንዳንድ ጊዜ ስሜት በማይሰጥ መልጎምጎም ጭምር ተገለጡልኝ፡፡›› በማለት ስለጎንደር ቆይታው ያነሳሳል፡፡

‹‹እዚያ የገጠመኝን እውነታ በልኩ ለመረዳት ስለሙዚቃ የነበረኝን የጠጠረ አስተሳሰብ እንደገና አፈራርሼ መሥራት ነበረብኝ፡፡ በጎንደር ሙዚቀኞች እንደ አንጥረኛ፣ እንደ ቀጥቃጭ፣ እንደ ሸማኔ ሁሉ እንደ እጅ ሙያተኞች ይቆጠሩ ነበር፤›› በማለት ትዝብቱን አስቀምጧል፡፡

‹‹የከተማዋ አብዛኞቹ ነዋሪዎች የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው፡፡

ለቅዳሴ፣ ለዝማሬ ለማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት የሚጠቀሙበትን ያሬዳዊ ዜማ የመለኮት ችሮታ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ በማኅበረሰቡ ብዙ ዋጋ የማይሰጣቸው አዝማሪዎች መሰንቋቸውን ይዘው ውር ውር ይላሉ፡፡ ብዙዎቹ ሙዚቃቸውን የሚከውኑት በየጎዳናው እየተዟዟሩ ነው፡፡ የጎንደር ጎዳናዎች ታሪኮች ፍጻሜ የላቸውም፤›› ሲል ስለ ጎንደር ሃይማኖታዊና ባህላዊ ታሪኮች ምስክርነቱን አስቀምጧል፡፡ ‹‹ታሪኮቹ እስከ ጃፓን፣ አሜሪካና አውሮፓ ይሻገራሉ፡፡ ታሪኮቹን የቀሰምንባቸው ባለታሪኮቻችን የዕለት ውሏቸው፣ ግብግባቸው፣ ገጠመኞቻቸው፣ ትግሎቻቸው ሥሪቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች መወዳጀት ቀላል አልነበረም፡፡ የጎዳና ላይ ነዋሪዎቹ ወይ በጋለ ፍላጎት በፍቅር ይቀበሉዎታል ወይ ጭራሽኑ ሊያዩዎት አይፈልጉም፤›› ሲል ደራሲው ጎንደር ላይ ስለነበረው ቆይታ አትቷል፡፡

በሌላ በኩል የመጽሐፉ ተርጓሚዎች ስለ ተረጐሙት መጽሐፍ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ተርጓሚው ያዕቆብ ብርሃኑ ስለ ደራሲው ሲናገር የጻፋቸውን ቃል በቃል ከመቀየር ይልቅ ይዞታና ትርጉማቸውን ሳይቀሩ በጥሩ አማርኛና ለአንባቢ ጆሮ በሚጥም ሁኔታ እንዲጽፉ ነፃነት ሰጥቶኛል ነበር ያለው፡፡

በደራሲው ዘንድ የተሰጠው ነፃነትም መጽሐፉ ትርጉም እንዳይመስል አድርጎታል የሚለው ያዕቆብ፣ ለአንባቢ አመቺና ሳቢ በሆነ መንገድ መተርጐሙን አክሏል፡፡

ሌላኛው ተርጓሚ ዓለማየሁ ታዬ ከካሞሴ (ዶ/ር) ጋር የረዥም ጊዜ ትውውቅ እንዳላቸው ተናግሯል፡፡

ደራሲው መጽሐፉን ሲጽፍ መጽሐፍ ይሆናል ብሎ ሳይሆን በኢትዮጵያና በአፍሪካ ያሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ጃፓን ውስጥ ለሚገኝ ጋዜጣ ግብዓት ይሆናል ተብሎ ስለመጀመሩ ያስታውሳል፡፡

ደራሲው የኢትዮጵያን ባህል ጥሩ አድርጎ ተመልክቶታል የሚለው ዓለማየሁ  ያየውንና የሰማውን ታሪክ እንደ ወረደ ፍጥጥ በማድረግ አስቀምጦት ነበር ብሏል፡፡

ነገር ግን ተርጓሚዎቹ በማኅበረሰቡ ‹‹ነውር›› ወይም ‹‹ፀያፍ›› የሚባሉ በግልጽ የማይነገሩ ቃላትን በማለዘብ እንዳስቀመጡ ያስረዳል፡፡

ካሞሴ (ዶ/ር) በአንትሮፖሎጂስት ዕይታ ነው ቃሎቹን ያሰፈራቸው የሚለው ዓለማየሁ፣ ደራሲው አማርኛ በመቻሉ ለመተርጐም ቀላል እንደሆነላቸው ያስረዳል፡፡

በአጠቃላይ የፒያሳ ቆሌዎች የሚለውን የመጽሐፉን መጠሪያ ጨምሮ  17  የተለያዩ አርዕስትን የያዘ ሲሆን የፀሐይ ቅምጥል፣ የአዝማሪው እግዚኦታ፣ የተስፋዪቱ ምድር፣ የኢትዮጵያ ሆቴል ትዝታዎችና  የቆሎ ተማሪ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በ149 ገጾችን የያዘው መጽሐፉ  በ350 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡