ልናገር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚደርስ ኪሳራና ውድመት ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው ፈንድ የኢትዮጵያ…

አንባቢ

ቀን: March 5, 2025

በማስታወሻ ምሥጋናው እንግዳው (ዶ/ር)

በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረው የኢንዱስትሪ አብዮት ለሰው ልጆች የኑሮ መሻሻልና መዘመን ትልቅና የማይካድ አስተዋጽኦ ማድረጉ ዕሙንና በእጅጉ የሚመሠገን ነው፡፡ ይኼ ለውጥ የድንጋይ ከሰል፣ የተፈጥሮ ጋዝና የመሳሰሉትን በኃይል ምንጭነት የሚጠቀም መሆኑና ከዚህም ሒደት የሚወጣውና ከባቢ አየርን የሚቀላቀለው የአፋኝ ጋዝ መጠን ከጊዜ ጋር ትይዩ በሆነ ፍጥነት እየጨመረ መምጣት፣ ላለንበት ክፍለ ዘመንና ለሚመጣውም ትውልድ ዋና የችግር ምንጭና ትልቁ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።

የጋዙ ክምችት በጨመረ ቁጥር በአየር ንብረት ላይ የሚያስከትለው ለውጥም በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱ ለሰው ልጆችና ለአካባቢያዊ ደኅንነት አደጋ ጋርጧል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በዋናነት በእነዚህ በካይ ጋዞች ክምችት ምክንያት የሚከሰት መሆኑ ቢታወቅም ተፈጥሯዊ ምክንያቶች፣ ለምሳሌ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታና በ100 ሺሕ ዓመታት የጊዜ ዑደት ውስጥ የሚከሰት በፀሐይና በምድር መካከል ያለ ርቀት በእጅግ አነስተኛ መጠን መቀራረብም አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ ይታወቃል። ነገር ግን በእነዚህ ተፈጥሯዊ ምክንያቶች የሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም

ከዚህም ባሻገር የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከቦታ ቦታ መጠኑ የሚለያይ ቢሆንም፣ አብዛኛው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያቱ ይኼ በሰው ልጆች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር በተያያዘ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ ጋዞች መሆናቸው እውነት ነው። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው ‹‹Intergovernmental Panel on Climate Change IPCC)›› በየአምስት ዓመቱ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ናቸው። ይኼ ድርጅት ለሚያዘጋጃቸው ረፖርቶች በዓለም ላይ የሚደረጉ የተመረጡና ደረጃቸውን የጠበቁ ጥናቶችን ግኝት ተመሥርቶና አሉ የተባሉ የዘርፉን ባለሙያዎች ምልከታ በመጠቀም ነው ወደ ድምዳሜ የሚደርሰው። ድርጅቱ እ.ኤ.አ. ከ1988 ጀምሮ ስድስት ዓበይት ሪፖርቶችን አውጥቷል። እስካሁን ባወጣቸው ሪፖርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እርግጠኝነቱ እየጨመረ ነው የመጣው። እ.ኤ.አ. በ2021 የወጣው የድርጅቱ ሪፖርት ዓለም እያስተናገደችው ያለችው የአየር ንብረት ለውጥ መነሻው እነዚህ በካይ ጋዞች መሆናቸው ‹‹ሀቅ ነው›› ብሎ ደምድሟል።

የአየር ንብረት ለውጥ ሲከሰት ከተለመደው የተለየ የአየር ሁኔታ ውጪ የሆነ እጅግ አደገኛ ሙቀት፣ ድርቅ፣ ከባድ አውሎ ንፋስ፣ ሰደድ እሳት፣ ከባድ ዝናብ፣ ለውርጭ የሚዳርግ ዝቅተኛ ሙቀትና የመሳሰሉት በከፍተኛነትና በድግግሞሽ መከሰት በእጅጉ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ክስተቶች የሚሸፍኑት የቆዳ ስፋት እየጭመረ ነው። ይኼም የሕዝብንና የተፈጥሮን ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸውን ተጋላጭነት በእጅጉ ይጨምረዋል ማለት ነው። በእነዚህ የአየር ንብረት መዛባት መገለጫዎች ምክንያት ዓለማችን በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊና ሰብዓዊ ጉዳቶችን እያስተናገደች ትገኛለች።

ለምሳሌ ያህል በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እስካሁን ከደረሰው ጉዳት ባሻገር የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2050 ድረስ ባሉት ዓመታት ብቻ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ጎርፍና ድርቅ እያንዳንዳቸው ወደ 8.5 ሚሊዮን እና 3.2 ሚሊዮን አካባቢ ለሚሆኑ የሰው ልጆች ሞት ምክንያት እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ከሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ ተያያዥ ከሆኑ ጉዳቶች ጋር ሲጨመር ሞት ወደ 14.5 ሚሊዮን ከፍ ሲል አጠቃላይ የኢኮኖሚ ውድመቱ ደግሞ 12.5 ትሪሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል።

በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣ ጉዳት ለይቶ የሚተወው የዓለም ክፍል አለመኖሩ የሚታወቅ ነው። የአየር ንብረት ለውጥን ለማቆም ለሚደረገው ዓለም አቀፋዊ ጥረት በዳተኝነቷ የምትታወቀውና እ.ኤ.አ. በ2016 የትራምፕ አስተዳደር ጊዜ ‹‹የፓሪስ ስምምነት›› በመባል የሚታወቀውን ትብብር ትታ የወጣችው አሜሪካ እንኳ፣ በካሊፎርኒያ ግዛት በተከሰተው ድርቅ፣ ሙቀትና ፈጣን ንፋስ ያባባሱት ሰደድ እሳት ያስከፈላትን ዋጋ ብዙኃኑ በመገናኝ አውታሮች የተከታተለው ነው።

ይኼ ከተለመደው ውጭ የሆነ የተዘበራረቀና ለመገመት አስቸጋሪ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ጉዳት ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላላቸውና በማደግ ላይ ላሉ አገሮች የሚያስከትለው ጉዳት ደግሞ፣ በእጅጉ ከባድና “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ያለ ነው፡፡ አብዛኞቹን ምናልባት ሁሉም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ድርቅ በተከሰተ ቁትር ለነፍስ አድን የሚሆን ዕርዳታ ለማሰባሰብ፣ የበርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ሀብታም አገሮችን በር ማንኳኳት ማዘውተራቸው የተለመደ ሆኗል። የእነዚህ አገሮች ዝቅተኛ ሰው ሠራሽም የሆነ ተፈጥሯዊ አደጋን የመቋቋም አቅምና ከፍተኛ ተጋላጭነት ለዚህ አነስተኛ ለሆነ የአየር ንብረት ለውጥን ያለመቋቋም ችግር አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። እነዚህ ደሃ አገሮች በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አይደሉም።

ስለዚህ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት የበካይ ጋዝ መጠን በእጅጉ ዝቅተኛና ለዜሮ የተጠጋ ነው። ነገር ግን ከዚህ አነስተኛ ከሆነው የበካይ ጋዝ ልቀት አስተዋጽአቸው ባልተመጣጠነ ሁኔታ የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ ከመሆን አላመለጡም፡፡ ከዚህም ባሻገር እያስተናገዱ ያለው የጉዳት መጠን በእጅጉ ከፍተኛ መሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ የአየር ንብረት ለውት የምክክር ጉባዔዎችን ውጥረት የበዛባቸውና ብዙም የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ለማምጣት በቂ ያልሆኑ ውሳኔዎችና አፈጻጸሞች የሚታዩባቸው ከሆኑ በርከት ያሉ ዓመታት ተቆጥረዋል።

የበለፀጉ አገሮች በተለያየ መጠንና መልኩ ከመተቸት ባያመልጡም፣ እያደረጉት ባለው እጅግ ውስን የገንዘብ ድጋፍ በማደግ ላይ ያሉና ደሃ አገሮችን የአየር ንብረት ለውጥን መቋቁም እንዲችሉ ለማድረግ ሁለት በዋናነት የሚጠቀሱ ‹‹Adaptation Fund (AF) and Green Climate Fund (GCF)›› የሚባሉ የገንዘብ ቋት ድርጅቶች ተቋቁመዋል። ‹‹AF›› በዋናነት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ መገንባት ላይ ትኩርት የሚያደርግ ሲሆን፣ ‹‹GCF›› ደግሞ የበካይ ጋዞችን ልቀት በዘላቂነትና ትርጉም ባለው መጠን መቀነስ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ደሃ አገሮችን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ። መጠኑ ከሚፈለገው አንፃር በእጅጉ አናሳ ቢሆንም፣ የበለፀጉ አገሮች የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ ለእነዚህ እንቅስቃሴዎች አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የበካይ ጋዞች ቅነሳና ለአየር ንብረት ለውጥ መላመድ ላይ ያተኮሩ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል እንቅስቃሴዎች መደረግ ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል፡፡ ‹‹AF›› እና ‹‹GCF›› እንደ ቅደም ተከተላቸው እ.ኤ.አ. በ2001 እና በ2010 ነው የተመሠረቱት። የእነዚህ ድርጅቶች ድኅረ ገጽ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያም በርከት ያለ ገንዘብ ወስዳለች። ከ‹‹GCF›› ወደ 375 ሚሊዮን ዶላርና ከ‹‹AF›› ደግሞ በትንሹ ከአሥር ሚሊዮን በላይ መውሰዷን ያሳያል።

በቅርብ ዓመታት ከተደረጉ ወሳኝ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔዎች መካከል እ.ኤ.አ. የ2016 የፓሪስ ስምምነት፣ የ2021 የካይሮና የ2024 የዱባይ ጉባዔዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ነገር ግን ዛሬም የበካይ ጋዞች ልቀት ከመጨመርና አጥጋቢ ያልሆነ የአየር ንብረት ማላመድ ሥራዎች፣ በዋናነት በደሃ አገሮች የሚኖሩ ዜጎችን ሰለባ የሚያደርገው የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ውድመት በእጅጉ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ታዲያ አንዱና ትልቁ የ2024 የዱባይ ጉባዔ ስኬት ተደርጎ የተቆጠረው በቂ ያልሆኑ የአየር ንብረት ማላመድ ሥራዎች መከላከል ላልቻሉትና የሦስተኛው ዓለም አገሮች እየገጠማቸው ላለው ኪሳራና ውድመት ምላሽ ለመስጠት በዓለም ባንክ ሥር የተቋቋመው ‹‹Fund for Responding to Loss and Damage (FRLD)›› ምሥረታ ነው፡፡ የዚህ የገንዘብ ቋት ከሚወቀስባቸው ጉዳዮች መካከል የበለፀጉ አገሮች ለሰባዊ ዕርዳታና ለዘላቂ ልማት የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ አዲስ ወደ ተቋቋመው ኪሳራና ውድመትን ምላሽ ለመስጠት ወደ ተመሠረተው የገንዘብ ቋት ማዘዋወራቸው ነው።

ደሃ አገሮች ከዚህ የገንዘብ ቋት የሚገባቸውን ለማግኘት አንዱ እንደ ቅድመ ሁኔታ እየተጠቀሰ ያለው (ጊዜያዊ) መሥፈርት ለደረሰባቸው ኪሳራና ውድመት ሳይንሳዊ የሆነ፣ ጠንካራና ታማኝነት ያለው መረጃና ማስረጃ ማቅረብ ነው፡፡ ወጥነት፣ ተገቢነት፣ አካታችነትና ተዓማኒነት ያለው መረጃ አሰባሰብና አያያዝ የአንድ አገር የዕድገትና ውድቀት ምንጭ የሚሆኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች (ከበጀት ድልድልና መሠረተ ልማት ዝርጋታ ጀምሮ) የሚቀረፁትና የሚተገበሩት በዚሁ ላይ ተመርተው ነው፡፡ መንግሥታት የሚያስመዘግቡትን በጎ ለውጥ እንኳን ሳይቀር በአግባቡ ለመመዘን አስቸጋሪ የሚያደርገው እንደ መነሻ በሚያገለግለውና አዲስ በሚመዘገበው ለውጥ መካከል ያለውን ልዩነት ለመለየት የሚያስችል ታማኝነት ያለው የመረጃ እጥረት ነው። በማደግ ላይ ያሉና ደሃ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ደካማ የሆነ የመረጃ አሰባሰብና አያያዝ ሰለባ ናቸው።

በቂ ያልሆነ የሀብት ማነስና ተገቢነት ያለው የባለሙያ እጥረት ከሚመጣ የመረጃና ማስረጃ አሰባሰብና አያያዝ ችግር በተጨማሪ፣ የተረጋጋ ዘላቂ ሰላም ዕጦትና መንግሥታዊ አለመረጋጋት ለመረጃ አሰባሰብና አያያዝ ጉልህ ሚና አላቸው። ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟት የአየር ንብረት መዛባት በአደገኛነታቸው በድግግሞሽ መከሰት ከአየር ንብረት የመረጃ ቋቶች፣ ከሳተላይት ምሥሎችና ድቅል መረጃዎች ስምምነት ማየት ቢቻልም የእነዚህን የአየር ንብረት ተፅዕኖዎች በግብርና ምርት መቀነስ ላይ ወይም በቁም እንስሳት ሞት አልያም ለሕመም በተጋለጡ የሰዎች ቁጥር ላይ ብዙውን ጊዜ አይታይም። ምናልባት ከታየም ትክክለኛውን የአየር ንብረት ተፅዕኖ አያሳይም። ወቅታዊ፣ ለእውነታው የቀረበ ለረሃብና ለችግር የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር፣ ወይም ሌላ ዓይነት ኪሳራና ውድመትን የሚመለከት መረጃ አብዛኛውን ጊዜ የሚገኘው የነፍስ አድን ዕርዳታ ከሚያቀርቡት ድርጅቶችና አገራችን ነው።

በማደግ ላይ ያሉ አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥማቸውን ኪሳራና ውድመት በመመዝገብ ያለባቸውን አጠቃላይ የመረጃ ጥራት ማነስ፣ ሊወስዷቸው ስለሚገቡ ዕርምጃዎች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ አየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው አገራዊ፣ ቀጣናዊና አኅጉራዊ ዕርምጃዎች ‹‹Bridging evidence gaps in attributing loss and damage, and measures to minimize impacts›› የተመላከቱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት ደግሞ በአጠቃላይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥማቸውን ኪሳራና ውድመት  መረጃና ማስረጃ ያለውን ክፍተት ጨምሮ፣ የመረጃ ታማኝነት ችግር ማስረጃም፣ ምላሽም የሚሆነውና መንግሥታዊ የመረጃ አሰባሰብና አያያዝን ምልዑነትና ተዓማኒነት ለማሻሻል በማሰብ መተግበር ስላለባቸው ዕርምጃዎች የሚያትተውና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በጥቅምት እ.ኤ.አ. 2023 ያወጣው ደንብ ነው።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚደርስ ኪሳራና ውድመት ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው ፈንድ በይፋ ከተመሠረት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አራት የሚሆኑ የቦርድ ስብሰባዎችን አካሂዷል። አምስተኛ ስብሰባውን የፊታችን ሚያዚያ መጀመሪያ ውስጥ በባርቤዶስ አንደሚያካሂድ አሳውቋል። በአራተኛው ስብሰባ ከተደረጉት ቁልፍ ውሳኔዎች ውስጥ አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የገጠማቸውን ኪሳራና ውድመት ራሳቸው አጥንተው አንዲያቀርቡ የሚያትተው ሲሆን፣ ይኼም አገሮች የሚገጥማቸውን ኪሳራና ውድመት ለመቀነስ የሚያደርጉትን ጥረት ከማበረታታትና ማጠናከር ኤልፎ ፈንዱ ለሚሰጠው ፈጣን ምላሽ ስኬታማነት አጋዥ ይሆናል ተብሎ ታስቧል። ይኼም ማለት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታትም፣ አሁንም ሆነ ወደፊት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለገጠሟትና ለሚገጥሟት ኢኮኖሚያዊም ሆኑ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ኪሳራዎችና ውድመቶች ማሳያዎች ማቅረብ ይጠበቅባታል። አዲስ ከተመሠረተው ፈንድ የሚገኘው የገንዘብ ከደረሱ ኪሳራዎችና ውድመቶች ለማገገም፣ ጉዳቶችን ለማካካስና ለመልሶ ግንባታ የሚውል ይሆናል። 

ታዲያ ከአየር ንብረት ለውጥና ንክኪ ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ወጥነት፣ ተገቢነት፣ አካታችነትና ተዓማኒነት ያለው መረጃና ማስረጃ አሰባሰብና አያያዝን ለማሻሻል ከሚደረግ ጥረት ባሻገር ያጋጠሟትንና ለሚያጋጥሟት ኪሳራዎችና ውድመቶች ማሳያዎችን ለማቅረብ ምን ዝግጅት አለ? ምንስ ታስቧል? በማለት የሚመለከተውን አካል መጠየቅ ተገቢ ይሆናል።

   ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው mastaweshamisganaw@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡