
ከ 2 ሰአት በፊት
የአሜሪካ አቃቤ ሕጎች በአገሪቱ የሚገኙ የቻይና መንግሥት ተቃዋሚዎችን መረጃ በመመንተፍ ለቤጂንግ መንግሥት በመሸጥ የተጠረጠሩ 12 ቻይናውያን ላይ ክስ መሰረቱ።
የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ “በመንግሥት የተደገፈው” የሳይበር ጥቃት የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት ላይም ያነጣጠረ ነበር።
የአሜሪካ የሃይማኖት ተቋማት እና በሆንግ ኮንግ የሚገኝ አንድ ጋዜጣም የጥቃቶቹ ሰለባዎች መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መግለጫ አስረድቷል።
ቻይና ይህንን ክስ በተመለከተ ምላሽ ባትሰጥም ከዚህ ቀደም የቀረቡባትን ተመሳሳይ ክሶች ውድቅ አድርጋለች።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ በቻይና በተደገፉ ጠላፊዎች “ትልቅ” ጥቃት እንደደረሰበት ገልጾ ነበር።
በዚህ ጥቃት መረጃ መንታፊዎቹ የሠራተኞችን የስራ መሳሪያዎችን እንዲሁም ምንነታቸው ያልተገለጹ ሰነዶችን ማግኘት እንደቻሉ አስታውቆ ነበር።
በወቅቱ ቻይና፤ ክሱን “መሰረተ ቢስ” ስትል ያጣጣለች ሲሆን “የትኛውንም ዓይነት የሳይበር ጠለፋ በቋሚነት እንደምትቃወም” በመግለጽ በድርጊቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላት አስታውቃለች።
የፍትህ ሚኒስቴር ይህንን ክስ የመሰረተው የት እንደሆነ ባይታወቅም፤ ረቡዕ ዕለት ክሱ የተከፈተው ግን በማንሃተን በሚገኝ የፌደራል ፍርድ ቤት ነው።
ክስ የቀረበው እነማን ላይ ነው?
ክስ ከቀረበበባቸው ግለሰቦች መከካል የቻይና የሕዝብ ደህንነት ሚኒስቴር ሠራተኞች የነበሩ ሁለት ሰዎች ይገኙበታል።
‘i-Soon’ የተባለ ኩባንያን የወከሉ መስለው የቀረቡት እነዚህ ጠላፊዎች፤ “በመዘበሩት” በእያንዳንዱ የኢሜይል መልዕክት ሳጥን ከቻይና የመንግሥት ተቋማት ከ10 ሺህ እስከ 75 ሺህ ዶላር ሲቀበሉ እንደነበር የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በቻይና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ትዕዛዝ እና በራሳቸው ተነሳሽነት “የኮምፒውተር ጥሰት ፈጽመዋል” የተባሉት እነዚህ ተከሳሾች “ለሰረቁት መረጃ ጥሩ ክፍያ እንደተቀበሉም” ተገልጿል።
የፍትህ ሚኒስቴር የብሔራዊ ደህንነት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሱ ጄ ባይ “ዛሬ፤ በዓለም ላይ የሚገኙ ኮምፒውተሮች እና የግንኙነት መስመሮች ላይ ማንንም ያለየ እና ግድየለሽ ጥቃት ሲመሩ እና ሲፈጽሙ የነበሩ የቻይና መንግሥት ሠራተኞችን አጋልጠናል” ብለዋል።
“የሳይበር ቅጥረኞችን የስራ ከባቢ ለማፍረስ እና ብሔራዊ ደህነታችንን ለማስጠበቅ የምደርገውን ትግል እንቀጥላለን” ሲሉም አክለዋል።
- ኢሉሚናቲዎች መነሻቸው ከየት ነው? ዓለምንስ በምሥጢር ‘ይቆጣጠራሉ’?ከ 6 ሰአት በፊት
- አሜሪካ የታገቱ ሰዎችን በተመለከተ ከሐማስ ጋር ቀጥተኛ ድርድር ማድረጓን ገለፀችከ 5 ሰአት በፊት
- አውሮፓ “የታሪክ እጥፋት ላይ ትገኛለች” ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት አስጠነቀቁከ 4 ሰአት በፊት
እነማን ዒላማ ተደረጉ?
በአሜሪካ የሚገኙትን ተቃዋሚዎች በተመለከተ ከዚህ ቀደም ከተሰጠው የተለየ ተጨማሪ መረጃ ይፋ አልተደረገም።
በጠላፊዎች ጥቃት የደረሰበት የሃይማኖት ተቋም “ከዚህ ቀደም ወደ ቻይና ሚሽነሪዎችን ልኮ የነበረ እና የቻይና መንግሥትን በግልጽ የሚቃወም” እንደሆነ ተገልጾ ነበር።
በሆንግ ኮንግ የሚገኝ ጋዜጣም ጥቃት ከደረሰባቸው ተቋማት ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል።
ስሙ ባይገለጽም ጋዜጣው “የቻይና መንግሥትን የሚቃወም ተደርጎ እንደሚቆጠር” ተጠቅሷል።
ጠላፊዎቹ፤ ከአሜሪካ ተቋማት ባሻገር የታይዋን፣ ሕንድ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ኢንዶኔዥያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ዒላማ አድርገው ነበር ተብሏል።
ኤፍቢአይ እንዲሁም የሳይበር ደህንንት እና መሰረተ ልማት ደህንነት ኤጀንሲ፤ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሁለት ዋና ዘመቻዎችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች “ከቻይና ጋር ግንኙነት ባላቸው አካላት” እንደተፈጸሙ ባለፈው ጥቅምት ወር ተናግረው ነበር።
ለ14 ዓመታት የዘለቀ የጠለፋ ኦፕሬሽን በመምራት እንዲሁም የውጭ አገር ዜጋ የሆኑ ቻይና ተቺዎች ዒላማ በማድረግ የተጠረጠሩ ሰባት የቻይና ዜጎች ባለፈው ዓመት ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ምዕራባውያን መንግሥታት ከቻይና ጋር የተገናኙ እንደሆኑ የገለጿቸው ጥቃቶች ከዚህ ቀደም የዩኬ ምርጫ ኮሚሽንን እንዲሁም ዩኬን እና የኒው ዚላንድን ፓርላማዎች ዒላማ አድርገው ነበር።