ማዕድን አውጪዎች

ከ 6 ሰአት በፊት

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በኮባልት ማዕድን ላይ ለአራት ወራት የሚፀና የወጭ ንግድ ዕቀባ ጣለች።

ይህን ተከትሎ የስልክ፣ ላፕቶፕ እና የኤሌክትሪክ መኪና ዋጋ ላይ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ እንዳይፈጠር ተሰግቷል።

የኮባልት ማዕድን ለበርካታ ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ግብዓት ሆኖ ያገለግላል።

የዚህ ማዕድን ከፍተኛ አምራች ደግሞ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናት።

ኮባልት ተፈጥሮው ጠንካራ፣ ቀለሙ አብረቅራቂ እና ፈካ ያለ ግራጫነት የሚያደላ የከበረ ማዕድን ነው። የሚገኘውም ከኒኬል እና ከመዳብ ተረፈ ምርት ነው።

ማናቸውም ኃይል ተቀብለው የሚሞሉ (rechargeable) የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ለመሥራት እጅግ አስፈላጊ ሲሆን፣ በተለይ ዘመናዊ ስልክ፣ ላፕቶፕ እና የኤሌክትሪክ መሣሪያዎች ካለዚህ ማዕድን የሚታሰቡ አይደሉም።

ከዚህ ባሻገር ማዕድኑ የጄት ሞተር አካልን ለመሥራት ይውላል።

ከፍተኛ ኃይልን መቋቋም መቻሉ ደግሞ ማንኛውንም ከባድ ነገሮች ለመቆራረጥ የሚውሉ ከባድ እና ቀላል መሣሪያዎች ለመሥራት ያገለግላል።

በሕክምናው ዘርፍ ደግሞ በቀዶ ሕክምና ለሚገቡ ቅይጥ አርቴፊሻል ሥራዎች (ለምሳሌ ለተተኪ ጥርስ) ተመራጭ ያደርገዋል።

ይህ እጅግ አስፈላጊ ማዕድን 70 ከመቶ የሚመረተው ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነው።

ኮንጎ በዚህ ማዕድን የወጭ ንግድ ላይ የአራት ወራት ዕቀባ የጣልኩት በዓለም ገበያ ላይ ‘የምርት መትረፍረፍ ስላጋጠመ ነው’ ብላለች።

ይህም በመሆኑ የዚህ ማዕድን ዋጋ አሽቆልቁሏል።

የወጪ ንግድ ዕቀባው ለ4 ወራት ይዘልቃል
የምስሉ መግለጫ,የወጪ ንግድ ዕቀባው ለ4 ወራት ይዘልቃል

በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2022 አንድ ሜትሪክ ቶን ኮባልት 82 ሺህ ዶላር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ዋጋው ወደ 21ሺህ ዶላር ዝቅ ብሏል።

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውሳኔ ዋጋውን ወደ ነበረበት ሊመልሰው ይችላል።

”በኮባልት የገበያ ሰንሰለት ላይ ማንኛውም እክል ሲገጥም የምርት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል” ይላሉ፣ የዓለም አቀፍ ገበያ ተንታኝ አኒታ ሜንሳህ፣ ለቢቢሲ።

“በዚህ ጊዜ የኤሌክትሮኒክ አምራቾች ሁለት አማራጭ አላቸው። አንዱ የዋጋ ልዩነቱን በራሳቸው መሸፈን፣ አልያም ወጪውን ወደ ሸማቾች ማሸጋገር።”

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይህን ውሳኔ ማሳወቋን ተከትሎ ኮባልት በሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ከወዲሁ የዋጋ ቀውስ ተፈጥሯል።

በተለይ ሊትዬም ባትሪን የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች በውሳኔው ዋና ተጎጂ ናቸው።

በአንድ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት የሚሠሩት ፒተር ዣንግ ውሳኔው ከወዲሁ ተጽዕኖው እየተሰማን ነው ይላሉ።

“ዕቀባው ከሦስት ወራት በላይ ከቆየ በኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር ይችላል፤ ወይም ደግሞ የባትሪ ጥራት ላይ ለውጥ ይከሰታል” ይላሉ።

ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ አሁን በገበያው ላይ የተትረፈረፈ ምርት ስላለ ዕቀባው ብዙ ካልዘለቀ ተጽዕኖው ከባድ ላይሆን ይችላል ባይ ናቸው።

በቻይና ዠቪያንግ ግዛት የኤሌክትሪክ መኪናዎች  ምርት
የምስሉ መግለጫ,በቻይና ዠቪያንግ ግዛት የኤሌክትሪክ መኪናዎች ምርት

ማን የበለጠ ይጎዳል?

በኮንጎ የኮባልት ምርት ጊዜያዊ ዕቀባ ዋና ተጎጂ ቻይና ትሆናለች።

ምክንያቱም ቻይና የኮንጎን ኮባልት የምትጠቀም ዋነኛ አገር ናት።

አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና ታይዋን እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ምርቱን የሚያገኙት ከተለያዩ አገራት ነው።

ይህን ያደረጉት ሆን ብለው በአንድ አገር ተጽዕኖ ውስጥ ላለመውደቅ ነው።

ነገር ግን ዕቀባው ዘለግ ላለ ጊዜ ከጸና በስልክ፣ በላፕቶፕ እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ላይ ከባድ የዋጋ ለውጥ ሊከሰት ይችላል።

ሌሎች ተንታኞች በበኩላቸው በሩዋንዳ እንደሚደገፈው የሚገመተው ኤም23 የተሰኘው አማጺ ቡድን ገፍቶ እየመጣ መሆኑ ኪንሻሳ አጋር እንድትሻ እያስገደዳት ነው ይላሉ።

ይህ ደግሞ እንደ ቻይና እና ዛምቢያ ያሉ አገራት የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማቲክ ጫና በማድረግ የምርቱ አቅርቦት እንዲቀጥል ሊያደርጉ ይችላሉ።

በፖለቲካ ውጥረት ላይ የሚገኘው የኮንጎ መንግሥት ዕቀባውን እንዴት ሊያስፈጽም ይችላል የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው።

ዋናዎቹ ኮባልት ማውጫዎች የሚገኙት በሉዋላባና ሐውንት ካታንጋ አካባቢ ነው። እነዚህ አካባቢዎች ላይ ብዙም ግጭት የለም።

ሆኖም ቦታዎቹ ከዛምቢያ እና ከአንጎላ 1000 ኪሎ ሜትር ድንበር ይጋራሉ።

ይህ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ደካማ ማዕከላዊ መንግሥት ላላት ኮንጎ ማዕድኑ በኮንትሮባንድ እንዳይወጣ የመቆጣጠር አቅሟን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ሆኗል።