
ከ 5 ሰአት በፊት
በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ባለፈው ሳምንት ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የተተመነለትን የጆሮ ጌጥ ሰርቋል የተባለው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት ጉትቻዎቹን መዋጡን ፖሊስ ገለፀ።
የኦርላንዶ ፖሊስ የ32 ዓመቱ ጄይታን ጊልደርን በፍሎሪዳ የውድ ጌጣ ጌጦች መሸጫ መደብር ለሆነው ቲፋኒ እና ኩባንያ ሠራተኞች፤ “ፕሮፌሽናል አትሌቶችን” እንደሚወክል በመግለጽ ከዋሸ በኋላ “በርካታ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ጌጣጌጦች” እንዲያሳዩት አድርጓል።
ከዚያም ጊልደር የጆሮ ጌጦቹን ሰርቆ ከመደብሩ ሮጦ መውጣቱን የፖሊስ መረጃ ያስረዳል።
በዚያው ዕለት ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ያዋለው ሲሆን “የተሰረቁት የጆሮ ጌጦች ናቸው ተብሎ የታመኑ በርካታ ነገሮችን መዋጡን” ፖሊስ አረጋግጧል።
ሚስተር ጊልደር 769,500 ዶላር የሚያወጡ ሁለት ጉትቻዎችን እንዲሁም ከሱቁ ሮጦ ሲወጣ ጥሎታል የተባለውን የአልማዝ ቀለበት ሰርቋል ተብሏል።
- አሜሪካ የታገቱ ሰዎችን በተመለከተ ከሐማስ ጋር ቀጥተኛ ድርድር ማድረጓን ገለፀችከ 5 ሰአት በፊት
- የዲሞክራቲክ ኮንጎ ማዕቀብ በሞባይል እና በመኪኖች ዋጋ ላይ ጭማሪ ያስከትላል ተባለከ 6 ሰአት በፊት
- ኢሉሚናቲዎች መነሻቸው ከየት ነው? ዓለምንስ በምሥጢር ‘ይቆጣጠራሉ’?ከ 6 ሰአት በፊት
ፖሊስ የግለሰቡን የሆድ ዕቃ የሚያሳይ የራጅ ውጤት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ግለሰቡ ሆድ ውስጥም ባዕድ ነገር ተቀምጦ ይታያል።
ቢቢሲ የኦርላንዶ ፖሊስ ጌጣጌጦቹን ከግለሰቡ ሆድ ውስጥ ማውጣት ችሎ መሆኑን ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።
ፖሊስ በተጨማሪም ጊልደር እኤአ በ2022 ከቲፋኒ እና ኩባንያ የቴክሳስ መደብር መዝረፉን ገልጿል።
ደጋጋሚ ወንጀለኛ ነው የተባለው ጊልደር በኮሎራዶ 48 የተለያዩ ክሶች እንዳሉበት ተገልጿል።
ፖሊስ ጊልደርን ጭምብል ለብሶ ከ100,000 ዶላር በላይ ዋጋ የተተመነላቸውን እቃዎች በመስረቅ ወንጀል ከስሶታል።