የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

ከ 4 ሰአት በፊት

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አውሮፓ “የታሪክ እጥፋት ላይ” እንደምትገኝ በብራሰልስ ለመከላከያ ልዩ ምክር ቤት ለተሰበሰቡት የአውሮፓ መሪዎች ተናገሩ።

ስለ ዩክሬን ጉዳይ ለመምከር የተገናኙት አውሮፓ መሪዎች አገሪቱን ከማስታጠቅ ባሻገር፤ ከአሜሪካ ታገኝ የነበረው እርዳታ እንደሚቋረጥ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተገለጸላትን ኪዬቭ በምን ዓይነት መንገድ ይበልጥ መደገፍ እንደሚችሉ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚ ዜሌንስኪም በስብሰባው ላይ እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በነጩ ቤተመንግሥት ካደረጉት ንትርክ ወዲህ በአውሮፓ ያለው የመረበሽ ስሜት እና ስጋት ጨምሯል።

የትራምፕ አስተዳደር ለሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያሳዩት አቀራረብ፤ አውሮፓ ለደህንነቷ አሜሪካ ላይ መተማመን እንደማትችል በማሳየቱ ብዙዎቹ የአውሮፓ መሪዎች ላይ ስጋት ፈጥሯል።

ዋሽንግተን ለዩክሬን ስታጋራ የነበረውን የደህንነት መረጃ ለማቆም መወሰኗም ስጋቱን ይበልጥ ጨምሮታል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን ለሕዝብ ባደረጉት ንግግር አገራቸው ያላትን የኒውክሌር መሳሪያ በመጠቀም ለአውሮፓ አጋራት የምትሰጠውን ጥበቃ ማራዘምን በተመለከተ ንግግር ለማድርግ ክፍት መሆኗን አስታውቀዋል።

ቀጣዩ የጀርመን ቻንስለር ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁት ፍሬድሪክ ሜርዝ በበኩላቸው የኔኩሌር ክፍፍል እንዲጨምር ጥሪ አቅርበዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሳላ ቮን ዴር ሌይን ደግሞ፤ “በአዋቂነት እድሜያችን አይተን በማናውቀው መጠን አውሮፓ ግልጽ እና ድርስ አደጋ” ተጋርጦባታል ብለዋል።

የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ “ለዩክሬን እና አውሮፓ ደህንነት ወሳኝ ጊዜ” መሆኑን ገልጸዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ኃላፊው ኡርሳላ ቮን ዴር ሌይን ለአውሮፓ መሪዎች በላኩት ደብዳቤ አህጉሪቱ “ጊዜውን መዋጀት” እንዲሁም ያላትን “ኢንዱስትሪያል እና ምርታማ ኃይል በማቀናጀት ወደ የጸጥታ ግቦች መምራት” እንደሚገባት አሳስበዋል።

ኃላፊው፤ ‘ሪአርም ኢውሮፕ’ (ReArm Europe ) የተሰኘ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ የመከላከያ ድጋፍ ይፋ አድርገዋል።

አውሮፓ የመከላከያ በጀቷን “በግዙፉ” እና “በአስፈላጊው ፍጥነት እና ፍላጎት” ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

ቮን ዴር ሌይን፤ በሪአርም ኢውሮፕ እቅድ ውስጥ የተካተቱት ሦስት ውጥኖች ዩክሬንን ለመደገፍ እንዲሁም ለአውሮፓ ደህንነት “በረጅም ጊዜ ሊመጣ ለሚችል ፍላጎት የበለጠ ኃላፊነት ለመውሰድ” እንደሚረዳ አስረድተዋል።

ይህ ገለጻቸው አህጉሪቱ ከአሁን በኋላ የአሜሪካን እርዳታ ላይ መተማመን እንደማትችል በብዙዎች ላይ የተፈጠረውን ስጋት የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።

ይህ ሪአርም ኢውሮፕ እቅድ የአውሮፓ አገራት የመከላከያ ወጪያቸውን ለመሳደግ እንዲችሉ ለማድረግ ሲባል የበጀት ጉድለታቸውን እንዲጨምር ይፈቅዳል።

አውሮፓን በሙሉ ሊጠቅም በሚችል የመከላከያ ኢንቨስትመንት ላይ የሚፈጠር ጉድለትን ለመሙላትም 125 ቢሊዮን ፓውንድ ብድርንም ያካትታል።

አገራት በተለያዩ ግዛቶች ያለውን የእድገት ልዩነት ለማጥበብ የመደቡትን ገንዘብ ወደ መከላከያ ወጪዎች ማዞር እንዲችሉም ይፈቅዳል።

አውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክም ወታደራዊ ፕሮጀክቶችን እንዲደግፍ ይፈቀድለታል።

እንደ ቮን ዴር ሌይን ገለጻ ይህ እቅድ ለመከላከያ ወጪዎች ሊውል የሚችል እስከ 860 ቢሊዮን ዶላር ሊያስገኝ ይችላል።

ብዙዎቹ አውሮፓ መሪዎችም የአገሪቱን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚወሰድን ፈጣን እና ወሳኝ እርምጃ እንደሚደግፉ ጠቁመዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ አሜሪካ ከአሁን በኋላ ከጎናቸው የማትሆን ከሆነ ፈረንሳይ እና አውሮፓ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

“ራሳችንን ለመጠበቅ አንድ እና ቁርጠኛ መሆን አለብን” ያሉት ማክሮን፤ የአውሮፓ እጣ ፋንታ ከዋሽንግተን እና ሞስኮ ጋር መታሰር እንደሌለበት ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ “አሜሪካ ከእኛ ጎን እንደምትቆም ማመን ብፈልግም፤ ይህ የማይሆን ከሆነ ለእርሱ መዘጋጀት አለብን” ብለዋል።