
ከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃማስ በጋዛ ያገታቸውን ሰዎች እንዲለቅቅ “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” ሰጡ።
ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ረዥም ጽሑፍ “እስራኤል የጀመረችውን ለመጨረስ እንዲያስችላት የሚያስፈልጋትን ሁሉ እየላኩ ነው። እኔ ያልኳችሁን የማታደርጉ ከሆነ አንድም የሃማስ አባል አይተርፍም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ይህ የተሰማው ዋይት ሐውስ ታጋቾችን በተመለከተ ከሃማስ ጋር ቀጥተኛ ውይይት እያደረገ መሆኑን ካረጋገጠ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።
ዋሽንግተን እስካሁን ድረስ ከቡድኑ ጋር ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ግንኙነትን ሳታደርግ ቆይታለች።
አሜሪካ በአሸባሪነት ከዘረዘረቻቸው ቡድኖች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳትፈጥር የሚከለክል ፖሊሲ አለ።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ ታጋቾቹ ካልተለቀቁ “የምትከፍሉት ዋጋ ከባድ ነው” ሲሉ ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ ወደ እስራኤል እየላኩ ያለውን ድጋፍ ምንነት ግን ይፋ ሳያደርጉ ቀርተዋል።
አክለውም “ሁሉንም ታጋቾች አሁኑኑ ልቀቁ፤ በኋላ አይሆንም፤ የገደላችኋቸውን ሰዎች አስከሬን ሁሉ በአስቸኳይ መልሱ፤ አለበለዚያ ግን የእናንተ ነገር ማብቂያው ይሆናል” ሲል አክለዋል።
“ለአመራሩ ጋዛን ለቅቆ ለመሄድ ያላችሁ እድል አሁን ነው።”
ትራምፕ፤ በጋዛ ለሚኖሩ ንፁኃን ዜጎችም ማስፈራሪያ ጽፈዋል “መፃዒው ጊዜ ብሩህ ነው። ይህ የሚሆነው ግን ታጋቾችን ደብቃችሁ እስካላቆያችሁ ድረስ ነው። ይህንን የምታደርጉ ከሆነ የሚጠብቃችሁ ሞት ነው” ብለዋል።
ትራምፕ ሃማስን ሲያስፈራሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። በታኅሣሥ ወር፣ የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸውን በተረከቡበት ወቅት ታጋቾች ካልተለቀቁ ሀማስ “የሚከፍለው ዋጋ የከፋ ይሆናል” ብለው ነበር ።
ትራምፕ አዲሱን ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉት በቅርቡ ተኩስ አቁም ከተፈቱ ታጋቾች ጋር በዋይት ሐውስ ከተገናኙ በኋላ ነው።
- የአረብ መሪዎች ጋዛን መልሶ ለመገንባት 53 ቢሊዮን ዶላር አማራጭ እቅድ አፀደቁ5 መጋቢት 2025
- እጣ ፈንታቸው በዓለም አቀፍ መድረክ እያከራከረ የሚገኘው የጋዛ ነዋሪዎች የገጠማቸው አጣብቂኝ4 መጋቢት 2025
- እስራኤል ማንኛውም እርዳታ ወደ ጋዛ እንዳይገባ መከልከሏን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አወገዘ3 መጋቢት 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዋይት ሀውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት አሜሪካ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ከሃማስ ጋር በቀጥታ እየተደራደረች መሆኑን አረጋግጠዋል።
እስራኤል ከንግግሩ በፊት በጉዳዩ ላይ ሀሳቧን መጠየቋን አክለው ተናግረዋል።
ሌቪት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካን ሕዝብ ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ነገር በማድረግ እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
የታጋቾች ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አዳም ቦህለር “ለአሜሪካ ሕዝብ ትክክል የሆነውን ለማድረግ በማሰብ የተጀመረ” ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሃማስ እና አሜሪካ “ሁለት ቀጥተኛ ስብሰባዎችን” ከማድረጋቸው በፊት “በርካታ የመረጃ ልውውጦች” መካሄዳቸውን የቢቢሲ የፍልስጤም ምንጭ ተናግሯል።
እስራኤል፤ አሁንም በጋዛ 59 ታጋቾች እንደሚገኙና እስከ 24 የሚደርሱት ታጋቾች በሕይወት እንደሚገኙ ተናግራለች።ከታጋቾቹ መካከል የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው እንደሚገኙበት ተገልጿል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ንግግር መጀመሩ በቅድሚያ የተሰማው አክስዮስ በተሰኘው የመገናኛ ብዙኃን በኩል ነበር።
የመረጃ ምንጩ፤ አሜሪካ ከሃማስ ጋር በኳታር ታጋቾች በሚለቀቁበት እና ጦርነቱ በሚቆምበት ሁኔታ ላይ እየተነጋገረች መሆኑን ዘግቦ ነበር።
የቀድሞ የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ የመከላከያ ምክትል ረዳት ሚኒስትር እንዳሉት ዩናይትድ ስቴትስ ዜጎቿን ለመመለስ “የበለጠ ንቁ” መሆን አለባት።
የቀድሞ የሲአይኤ ፓራሚሊተሪ ኦፊሰር የሆኑት ሚክ ሙልሮይ “በጥብቅ ካልተቀናጀ በስተቀር እስራኤላውያን ዜጎቻቸውን ለማስመለስ ያላቸውን እድል ያወሳስበዋል” ብለዋል።
የእስራኤል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመግለጫው ቀጥታ ውይይቱን አስመልክቶ “አቋሙን መግለጹን” አስታውቋል። ከዚህ ውጪ በመግለጫው ላይ ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ቦህለር ባለፉት ሳምንታት በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ከሃማስ ተወካዮች ጋር ተገናኝተዋል።
እኤአ ከ2012 ጀምሮ ሃማስ በኦባማ አስተዳደር ጥያቄ መሰረት በዶሃ መቀመጫ ቢሮ አለው።
ከአሜሪካ እና ግብፅ ጎን ለጎን በእስራኤል እና በጋዛ ሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ኳታር ትልቅ ሚና ተጫውታለች።
ትንሿ ነገር ግን ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነችው የባህረ ሰላጤው መንግሥት፣ በአካባቢው ቁልፍ የአሜሪካ አጋር ናት። ዋና የአሜሪካ አየር ኃይል ማረፊያን ያዘች ሲሆን ከኢራን፣ ከታሊባን እና ከሩሲያ ጋር እና ከሌሎች ጋር የተደረጉ ወሳኝ የፖለቲካ ድርድሮችን አስተናግዳለች።