
ከ 6 ሰአት በፊት
“ኢሉሚናቲዎች በምሥጢር ዓለምን ተቆጣጥረው አዲስ ሥርዓት ሊዘረጉ ነው” የሚለው መላ ምት ለዓመታት ሲሰማ ቆይቷል።
የዚህ ሃሳብ መነሻ በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ የነበረ ልብ ወለዳዊ ክስተት ነው።
ጀርመን የነበረው ‘ኢንላይትመንት ኢራ’ ወይም የዕውቀት ብርሃን ዘመን ከኢሉሚናቲ መነሻ ጋር ይተሳሰራል።
ባቫሪያን የሚባል ምሥጢራዊ ስብስብ ነበር።ይህም እአአ በ1776 ነበር የተጀመረው።
የተማሩ ሰዎች ተሰባስበው ሃይማኖታዊ ሥርዓት እና መዋቅርን ይነቅፉ ነበር።
ፍሪሜሰን እንደተባለው ሌላ ምሥጢራዊ ቡድን ሁሉ ኢሉሚናቲም ተራማጅ ተደርገው ይወሰዳሉ።
ወግ አጥባቂ እና ክርስቲያን ተቺዎች ግን አልተቀበሏቸውም።
ለተወሰነ ጊዜ ጠፍተው በ1960ዎቹ ዳግመኛ አንሰራሩ።

አሁን ያለው ኢሉሚናቲ ከባቫሪያን ምሥጢራዊ ቡድን እንደሚለይ በኢሉሚናቲ ላይ ጥናት የሠራው ዴቪድ ብራምዌል ይናገራል።
በምሥራቃዊው ፍልስፍና የሚመራ ከተለመደው ባህላዊ አካሄድ የሚጻረር ንቅናቄ በምዕራቡ ዓለም የተስፋፋበት ወቅት ነበር።
በወቅቱ ‘Principia Discordia’ የሚል መጽሐፍ ታተመ። መንግሥት አልባ ሥርዓት የሚያቀነቅኑ ሰዎች ኢሪስ የምትባል የቀውስ አምላክን እንደሚያመልኩ ልብ ወለዱ ያትታል።
ማኅበራዊ ነውጥ ማስነሳት የሚፈልግ ቡድንን ሕይወት ያስቃኛል።
መጽሐፉን ካዘጋጁት መካከል አንዱ ሮበርት አንቶን ዊልሰን ነው።
“ዓለም አምባገነን ሆናለች። ቁጥጥር ጠንክሯል” ብሎ ስለሚያስብ ማኅበራዊ ነውጥ በማስነሳት ለውጥ እንዲመጣ ይሻል።
“መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም፣ ታዋቂ ባህልን በመገዳደር፣ ሐሰተኛ መረጃ በማሠራጨት ለውጥ እንደሚመጣ ያምን ነበር” ሲል በኢሉሚናቲ ላይ ጥናት የሠራው ዴቪድ ብራምዌል ይናገራል።
- ባልተጨበጡ የሤራ ትንተና ፅንሰ-ሐሳቦች ያምናሉ?14 ነሐሴ 2019
- በዓለም ላይ በርካታ ሰዎች በሽብር ጥቃት የሚገደሉበት የአፍሪካ የሳህል አካባቢ5 መጋቢት 2025
- አዲሱ የበረኞች የ8 ሰከንድ ሕግ ምን ምን ጉዳዮችን ይዟል? የትኞቹ ግብ ጠባቂዎችስ ሰዓት ያባክናሉ?4 መጋቢት 2025
ፀሐፊው ከሌላ ወዳጁ ጋር በመሆን ‘ፕሌይቦይ’ መጽሔት ላይ ከአንባብያን የተላኩ ናቸው ያሏቸውን ሐሰተኛ ደብዳቤዎች ያትሙ ነበር።
ደብዳቤዎቹ ኢሉሚናቲ ስለተባለ ምሥጢራዊ ቡድን መኖር ይገልጻሉ።
ሰዎች የሚያነቡት እና የሚሰሙት ምን ያህል እውነት እንደሆነ እንዲጠራጠሩ የማድረግ መንገድ ነበር።
ብዙዎች ስለ ኢሉሚናቲዎች መኖር ማመን ጀመሩ።
ጆን ኤፍ ኬኔዲን ማን ገደላቸው? የሚለውን ጨምሮ በይፋ ከማይታወቁ ነገሮች ጀርባ ያሉት ኢሉሚናቲዎች ናቸው ተባለ።
ወሬው እንዲሠራጭ ምክንያት የሆነው መጽሐፍ ተቀባይነት በማግኘቱ ዩናይትድ ኪንግደም ሊቨርፑል ውስጥ ቴአትር ሆነ።
በ1975 ኢሉሚናቲ ሆኖ ጌም ለመጫወት የሚሆን ካርድ ሲታተም ከቡድኑ ጋር በተለምዶ የሚተሳሰሩ ምሥሎች ታዋቂ ሆኑ።
አሁን ላይ ጄ ዚ እና ቢዮንሴን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ሰዎች ኢሉሚናቲ ናቸው ተብሎ ይታመናል።
ሦስት ማዕዘን ያለው ቅርጽ በመሥራት መድረክ ላይ ሲያሳዩ ይስተዋላል።
ነገሩ እውነት እንዳልሆነ ቢታወቅም አሁንም ድረስ ከ1960ዎቹ የተነሳው የሴራ ትንታኔ ዘልቋል።

4ቻን በተባለውና በሬዲት ድረ ገጾች የሴራ ትንታኔው በስፋት ይሠራጫል።
በ2015 በአሜሪካ በተሠራ ጥናት ግማሽ የአገሪቱ ሕዝብ ቢያንስ በአንድ የሴራ ትንታኔ ያምናል።
በአንግላ ሩስኪን ዩኒቨርስቲ የምትሠራው ቪረን ስዋሚ እንደምትለው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች በሴራ ትንታኔ ሊያምኑ ይችላሉ።
አንዳች ዓይነት የሥነ ልቦና ጤና መዛባት እንዳለባቸው መላ ምት የሚያስቀምጡ ባለሙያዎች አሉ።
ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ በራስ መተማመንን የሚሸረሽር እውነታን ከመቀበል ይልቅ ቀላል ምላሽ ወይም ማብራሪያ የሴራ ትንታኔን ሰዎች ሊመርጡ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
የተማሩ ሰዎች በሴራ ትንታኔ እንደማያምኑ በቅርቡ የተሠራ ጥናት ይጠቁማል።
ባለሙያዋ እንደምትለው በደቡብ እስያ አገራት የሴራ ትንታኔ ሕዝብን ለመቆጣጠር በመንግሥታት ጥቅም ላይ ይውላል።
በተቃራኒው በምዕራቡ ዓለም ሰዎች አድማጭ እንዳጡ ወይም እንዳልተወከሉ ሲሰማቸው ፊታቸውን ወደ ሴራ ትንታኔ ያዞራሉ።

እንደ ዶናልድ ትራምፕ ያሉ መሪዎችም የሴራ ትንታኔን ሲያቀነቅኑ ይሰማል።
ባራክ ኦባማ አሜሪካ አልተወለዱም የሚለው እና ጆ ባይደን ያሸነፉበት ምርጫ ተጭበርብሯል የሚለውን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።
በሴራ ትንታኔ የሚያምኑ ሰዎች መደበኛ መገናኛ ብዙኃንን የማመን ዕድላቸው ውስን ነው።
“ለዘረኛ፣ ለመጤ ጠል እና ለአክራሪ ዕሳቤዎች ይጋለጣሉ” ስትል ባለሙያዋ ታስረዳለች።
ትራምፕ በልሂቃል ‘የተገፉ’ ሰዎች ውክልና እንደሚሰጡ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
በኢሉሚናቲ ላይ ጥናት የሠራው ዴቪድ ብራምዌል እንደሚለው በ1960ዎቹ በጻፈው መጽሐፍ ኢሉሚናቲን ዳግመኛ የቀሰቀሰው ሰው አሁን የሴራ ትንታኔው እጅግ መስፋፋቱን ሲያይ “ሊደነቅ እና ሊደሰትም ይችላል።”
ሐሰተኛ መረጃን የመዋጋት ዘመቻ መስፋፋት እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያ የሚገፋው መረጃ ሁሌም እውነት እንዳልሆነ የማሳቅ ንቅናቄ ማደግ እንደ ኢሉሚናቲ ያሉ የሴራ ትንታኔዎችን ያከስሙ ይሆናል ብለው ባለሙያዎች ይገምታሉ።
የኢሉሚናቲ መነሻ
መነሻ ሐሳቡ ከ200 ዓመት በላይ አስቆጥሯል።
ሲስተር አና የምትሠራው ከጎቲክ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ነው። ወደ አካባቢው ከፈረንሳይ፣ ከዩናይትድ ኪንግደም እና ከሌሎች አገራት ሰዎች “ለስብሰባ” እንደሚሄዱ ብታውቅም የት እንደሚካሄድ በግልጽ መረጃ የላትም።
በቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ መደብር ውስጥ የምትሠራው ሲስተር አና በባቫሪያን የኢሉሚናቲ ስብሰባ እንደሚደረግ ሰምታለች።
ኢንጎስልታድ ከተማ የኢሉሚናቲ መነሻ ቢሆንም ምሥጢራው ስብሰባ የመደረጉ ነገር ከእውነት የራቀ ይመስላል።
በአውሮፓውያኑ 1776 በኢንጎስልታድ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህሩ አዳም ዌስሻፑት ኢሉሚናቲን ፈጠረ።
የንግግር ነጻነት ያለበት የልሂቃን ስብስብ እንዲሆን ነበር ሐሳቡ። ከፍሪሜሰንስ ምሥጢራዊ ቡድን በተጨማሪ የፈረንሳይ ፈላስፎችም ተጽዕኖ አሳድረውበታል።
ሃይማኖታዊ ቡድን ሳይሆን ነጻ አስተሳሰብ የሚስተጋባበት ቡደን መፍጠርን ዓላማው አድርጎ ተነሳ።
ሃይማኖታዊ ዕሳቤ ዋነኛ በሆነበት ከተማ ነጻ አስተሳሰብ ማራመድ ቀላል አልነበረም።

መጀመሪያ ለቡድኑ አባልነት የመረጠው አምስት ጎበዝ የሕግ ተማሪዎቹን ነበር። ከዚያም ቡድኑ በፍጥነት ተስፋፋ።
የዕውቀት ብርሃንን አባላቱ ለማሠራጭ ሲሞክሩ፣ የመንግሥት እና የሃይማኖት ተቋማትን እንቅስቃሴ ተከታትሎ መረጃ የሚያቀብላቸውም ነበራቸው።
ሃብት በማከማቸት አስተምሮውን ለማስፋፋት ሞክረዋል።
ታዋቂው የጀርመን ዲፕሎማት ባሮን አዶልፍ ሐሳቡን ካስተዋወቁት መካከል ናቸው።
በባቫሪያ፣ በፈረንሳይ፣ በሃንጋሪ፣ በጣልያን እና በፖላንድ ያሉት አባላቱ ብዛት ሁለት ሺህ ደረሰ።
ጋዜጠኛው ማይክል ክሌነር እንደሚለው የኢሉሚናቲ ፈጣሪን “አብዮተኛ” ማለት ይቻላል።
“ሰዎች የተሻሉ እንዲሆኑ ያስተምራል። ማኅበረሰብን መለወጥ ይፈልግ ነበር። የተሻለ ዓለም እና አስተዳደር ማየት ይመኝ ነበር” ይላል።
በሚያስተምርበት ዩኒቨርስቲ ከሚፈቀደው በተቃራኒው የሰው ልጅ ዕውቀቶች ሁሉ በትምህርት መሰጥ አለባቸው ብሎ ያምን ነበር።
ቡድኑ በተመሠረተ በአሥረኛው ዓመት ፀረ መንግሥት ንቅናቄ ሲያደርግ ተደርሶበት ተበትኖ፣ መሥራቹ ወደ ጎተ ከተማ ተሰደደ።

ሆኖም ግን ምሥጢራዊ ቡድኑ አልታገደም ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሁንም ድረስ እንዳሉ የታሪክ ምሁራን ይገልጻሉ።
በዊንቸስተር ዩኒቨርስቲ የሚሠራው ዶክተር ማይክል ዉድ እንደሚለው ኢሉሚናቲ ብዙ ንዑስ የሴራ ትንታኔዎች ያሉት ጥቅል የሴራ ትንታኔ ነው።
ኢንጎስልታድ ከተማ የኢሉሚናቲ መነሻ ትባላለች። በከተማው ሙዝየም የምትሠራው ማርያ ኢፕለሽመር እንደምትለው በሙዝየሙ ካሉ አስገራሚ የታሪክ አጋጣሚዎች ጋር የሚተሳሰሩ የኢሉሚናቲ መጽሐፎች አሏቸው።

ከተማውን የሚያስጎበኘው ክላርነር እንደሚለው፣ በታሪክ ጉልህ ሥፍራ ያላቸውን ቦታዎች ሲያስጎበኝ በሴራ ትንታኔው የሚያምኑ ጎብኚዎች ያጋጥሙታል።
“ኢሉሚናቲ አሁን የሚታይበት መንገድ አስገራሚ ነው። ከእውነተኛው ኢሉሚናቲ በጣም በተለየ መንገድ ነው አሁን የሚታየው” ትላለች።
ሲስተር አና እንደምትለው አሁንም ድረስ የኢሉሚናቲ ስብሰባ በከተማው እንደሚካሄድ የሚያምኑ ሰዎች እውነት ባይሆንም እንኳን ቦታውን ይጠይቋታል።
ከፈረንሳይ አብዮት፣ አሜሪካ ላይ ከተፈጸመው የመስከረም 11 ጥቃት እንዲሁም ከሌሎች ጉልህ ክስተቶች ጀርባ ኢሉሚናቲዎች እንዳሉ የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም።