የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጄይፒንግ

ከ 3 ሰአት በፊት

ቻይና በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተጣለውን አዲስ የንግድ ታሪፍ በመቃወም ከአሜሪካ ጋር ለሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ጦርነት ዝግጁ መሆኗን ገለጸች።

ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ከጣሉ በኋላ ሁለቱ የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች ወደ ንግድ ጦርነት ለመግባት ተፋጥጠዋል።

ቻይና በአሜሪካ የእርሻ ምርቶች ላይ ከ10-15 በመቶ ቀረጥ በመጣል ለዶናልድ ትራምፕ እርምጃ ምላሽ ሰጥታለች።

የቻይና ኤምባሲ በኤክስ ገጹ ላይ “አሜሪካ የምትፈልገው ጦርነት ከሆነ፤ የታሪፍ፣ የንግድ ወይም ሌላ ዓይነት ጦርነት እስከ መጨረሻው ለመዋጋት ዝግጁ ነን” ሲል ማክሰኞ ዕለት የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰጠውን መግለጫ በድጋሚ ጠቅሷል።

ይህ የቻይና መግለጫ ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ የተሰማው የመጀመርያው ጠንካራ አቋም ነው።

ረቡዕ ዕለት የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ የዚህ ዓመት የአገሪቱን የመከላከያ በጀት በ7.2 በመቶ እንደምታሳድግ ተናግረዋል።

አክለውም ” በዓለማችን በመቶ ዓመት ውስጥ ያልታዩ ለውጦች በፍጥነት እየተከሰቱ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የቤጂንግ መሪዎች፤ ከአሜሪካ ጋር የንግድ ጦርነት ስጋት እንኳ እያለ የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ሊመነደግ እንደሚችል እርግጠኛ መሆናቸውን ለዜጎቻቸው ማሳየት ይፈልጋሉ።

ቻይና፤ በመካከለኛው ምስራቅ እና በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ገብታለች በማለት ከምትከስሳት አሜሪካ በተቃራኒ የተረጋጋ እና ሰላማዊ አገር መሆኗን ለማሳየት ትፈልጋለች።

ቻይና በአሜሪካ በተጣለባት ተጨማሪ ታሪፍ የተነሳ አዳዲስ ዓለም አቀፍ አጋሮችን ማስደንበር አትፈልግም።

ረቡዕ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤጂንግ ባደረጉት ንግግር አገራቸው ተጨማሪ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በሯን ክፍት ማድረግ እንደምትቀጥል አፅንዖት ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደምም ቻይና ወደ ጦርነት ለመግባት ዝግጁ መሆኗን ተናግራ ታውቃለች።

በጥቅምት ወር ፕሬዚደንት ዢ በታይዋን ደሴት ዙሪያ ወታደራዊ ልምምድ ሲያካሂዱ ለነበሩ የአገሪቱ ወታደሮች ለጦርነት ዝግጁነታቸውን እንዲያጠናክሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ በእንግሊዘኛ ያወጣውን መግለጫ በመጥቀስ፣ አሜሪካ ፌንታኒል ለተባለው መድሀኒት መስፋፋት ቻይናን ተጠያቂ ማድረጓን ተችቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፤ “የፌንታኒል ጉዳይ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ ታሪፍ ለመጨመር ውሃ የማያነሳ ሰበብ ነው” ብለዋል።

“ማስፈራራት አያስፈራንም። ዘለፋ በእኛ ላይ አይሰራም። ጫና ማድረግ፣ ማስገደድ ወይም ማስፈራራት ከቻይና ጋር ለሚደረግ ግንኙነት ትክክለኛው መንገድ አይደለም” ሲሉም አክለዋል።

የአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት ሁልጊዜ በውጥረት የታጀበ ነው።

የቤጂንግ ባለስልጣናት ዶናልድ ትራምፕ የቻይናውን አቻቸውን ለበዓለ ሲመታቸው መጋበዛቸውን ተከትሎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተሻለ ሁኔታ ላይ ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋ ነበራቸው።

ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከመግባታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ጋር “በጣም ጥሩ የስልክ ውይይት” አድርገናል ብለው ነበር።

ባለፈው ወር እንዲሁ ሁለቱ መሪዎች ሌላ የስልክ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ቢይዙም ሳይሳካ መቅረቱን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።

ቻይና ለወታደራዊ በጀት ብቻ 245 ቢሊዮን ዶላር ብትመድብም ከአሜሪካ የመከላከያ በጀት ጋር ሲነጻጸር በጣም ያነሰ ነው።

የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት እንዳለው ቻይና ምንም እንኳ ከአሜሪካ እና ሩሲያ በጣም ያነሰ ቢሆንም 1.6 በመቶ የሚሆነውን የአገር ውስጥ ምርቷን ለወታደራዊ አገልግሎት ታወጣለች።

ይኹን እንጂ ተንታኞች ቻይና ለመከላከያ የምታወጣውን ገንዘብ ዝቅ አድርጋ ታቀርባለች ብለው ያምናሉ።