ስብርባሪው በሃማስ ውስጥ እየዘነበ መሆኑ ታይቷል

ከ 3 ሰአት በፊት

ሐሙስ ዕለት ከቴክሳስ ወደ ህዋ ለመምጠቅ የተነሳው የስፔስኤክስ ሮኬት ፈንድቶ ስብርባሪዎቹ በረራዎችን አስተጓጎሉ።

የሮኬቱ ስብርባሪዎቹ አሁንም ከአየር ወደ ምድር መውደቃቸውን ተከትሎ ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡም እንደሚገኝ ተገልጿል።

ስፔስኤክስም ሰው ያልያዘው ሮኬት ወደ ህዋ በነበረው ጉዞ “ፈጣን ድንገተኛ ፍንዳታ” እንዳጋጠመው እና ከመሬት ጋር ያለው ግንኙነት መቆራጡን አረጋግጧል።

እስከዛሬ ከተገነቡት ትልቁ የሆነው የስፔስኤክስ ስታርሺፕ ሮኬት ከመጠቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከቁጥጥር ውጭ ወጥቷል።

ምንም ዓይነት ጉዳት ባይመዘገብም ግን ከካሪቢያን አገራት የተገኙ ምስሎች ከሰማይ የሚወርድ ስብርባሪዎችን አሳይተዋል።

ይህ ሮኬቱን ለመፈተሽ ስምንተኛው ሙከራ ሲሆን ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜም ፈንድቷል።

123 ሜትር ያለው ሮኬት ከአንድ ሰዓት ጉዞ በኋላ በህንድ ውቅያኖስ በኩል ወደ ምድር ምህዋር እንዲገባ ታስቦ ነበር።

መሬቱን ለቆ እንዲወጣ የሚረዳው የሮኬቱ ኃይል መስጫ ክፍል በተሳካ ሁኔታ ወደ ማስመንጠቂያው ለመመለስ ችሏል።

የቢሊየነር ኢሎን መስክ ንብረት የሆነው ስፔስኤክስ ባወጣው መግለጫ ከደህንነት ባለስልጣናት ጋር በመሆን “ቅድሚያ የሚሰጣቸው የአደጋ ጊዜ ምላሾችን” በፍጥነት ማስተባበር ጀምሯል።

መግለጫው አክሎም ስፔስኤክስ የአደጋውን “መንስኤ በተሻለ ለመረዳት” መረጃዎቹን እንደሚገመግም ገልጾ፤ ፍንዳታው የተከሰተው “በርካታ” ሞተሮች ከጠፋ በኋላ መሆኑን አስታውቋል።

“እንደተለመደው ስኬትን ምንማረው ከስሀተት ነው። የዛሬው ሙከራ የስታርሺፕ አስተማማኝነትን ለማሻሻል ተጨማሪ ትምህርቶችን ያስገኛል።” ብሏል።

መግለጫው አክሎም ፍርስራሹ አስቀድሞ በታቀደለት ቦታ ላይ መውደቅ እነደነበረበት እና ሮኬቱ ምንም አይነት መርዛማ ንጥረ ነገር አልያዘም ብሏል።

ኩባንያው ስብርባሪ አግኝተናል ብለው ለሚያምኑ ሰዎች ኢሜይል እና ስልክ ቁጥሩን ይፋ አድርጓል።

መስክ ስለሐሙሱ ፍንዳታ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

አደጋው እሳት ያላቸው ስብርባሪዎችን ሊፈጥር ይችላል በሚል ሚያሚ እና ኦርላንዶን ጨምሮ በተለያዩ የፍሎሪዳ አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚደረጉ በረራዎችን ለአጭር ጊዜ እንዲቆሙ አስገድዷል።

የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ባወጣው መግለጫ በአውሮፕላን ማረፊያዎች የሚያርፉ እና የሚነሱ በረራዎች የዘገዩት “በህዋ ላይ በተፈጠረ ችግር” ነው ብሏል።

የአሁኑ ክስተት በጥር ወር ቴክሳስ ከሚገኘው የስፔስኤክስ ተቋም የተመነጠቀ ሮኬት ከደቂቃዎች በኋላ መውደቁን ተከትሎ የተፈጠረ ነው።

በተመሳሳይ ስጋት ምክንያት ኤፍኤኤ ከሁለት ወራት በፊትም አየር ማረፊያዎችን ለአጭር ጊዜ ለመዝጋት ተገድዶ ነበር።

ከጥሩ ክስተት በኋላ በካሪቢያኖቹ የቱርክስ እና ካይኮስ ደሴቶች አካባቢዎች የንብረት ውድመት መድረሱን ኤፍኤኤ አስታውቋል።

የስፔስ ኤክስ የበረራ ተንታኝ ዳን ሁዎት ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ ባለፈው ጊዜም ተከስቷል። ስለዚህ የተወሰነ ልምድ አለን” ብለዋል።

የአሁኑ የስታርሺፕ ማስወንጨፍ የተካሄደው ኤፍኤኤ በጥር የደረሰውን ፍንዳታ ከማጠናቀቁ በፊት ነው ሲሉ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የቱርክስ እና የካይኮስ መንግስት ባወጣው መግለጫ ደግሞ ከአሜሪካ ባለስልጣናት እና ከስፔስኤክስ ጋር ግንኙነት እንዳለው እና “የደሴቶቻችንን ደህንነት ለማረጋገጥ በምንሰራበት ጊዜ ለህዝቡ መረጃ ማጋራታችንን እንቀጥላለን” ብሏል።

በኤክስ ላይ የተለጠፈው ምስል በካሪቢያን ባህር ላይ የሚወድቁ የሮኬት ፍርስራሾችን ያሳያል። ባሃማስ ያሉ ሰዎች ደግሞ ከፍርስራሹ ለመሸሸግ መጠለያ እየፈለጉ እንደሆነ ጽፈዋል።

ስታርሺፕ እስከ ዛሬ ከተሠሩት ትልቁ ሮኬት ሲሆን መስክ ማርስን ለመቆጣጠር ያለውን ምኞት የሚያሳካበት ቁልፍ መሣሪያ ነው።

የስፔስ ኤክስ ስታርሺፕ የጠፈር መንኮራኩር እና ሱፐር ሄቪ ሮኬት አንድ ላይ ስታርሺፕ እየተባለ የሚጠራ ሲሆን ሙሉ በሙሉ እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል ታስቦ መዘጋጀቱን ኩባንያው ገልጿል።