የጋቦን እግር ኳስ በርካታ ዓመታት በጾታዊ ጥቃት ሲታመስ ቆይቷል

ከ 5 ሰአት በፊት

የቀድሞ የጋቦን ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በተጫዋቾች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽሟል በሚል ፊፋ የዕድሜ ልክ እገዳ ማስተላለፉ “አዎንታዊ እርምጃ” ቢሆንም “ብዙ ወንጀለኞች መኖራቸውን” የዓለም አቀፍ የተጫዋቾች ማኅበር (ፊፍፕሮ) ለቢቢሲ ገለጸ።

የጋቦን የታዳጊ ቡድኖች ዋና አሰልጣኝ የነበሩት ፓትሪክ አሱሙ ኢዪ ኃላፊነት ላይ እያለ በርካታ ታዳጊ ወንዶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽሟል ሲል ፊፋ ማክሰኞ ዕለት ውሳኔውን አስተላለፏል።

በጋቦን እግር ኳስ ላይ እየተንሰራፋ ያለውን የመብት ረገጣ በተመለከተ ቢቢሲ አፍሪካ አይ እአአ በ2023 በሠራው የምርመራ ዘገባ ላይ አዪ ስሙ ተጠቅሷል።

በምርመራው ላይ አንድ የቀድሞ የጋቦን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እንዳለው ከሆነ አዪ ለጋቦን ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ማን እንደሚጫወት የመወሰን ስልጣን ስለነበረው “እንደአምላክ” ይታያል ብለዋል።

ከፔሎ በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው አዪ “ብቸኛው የተቀጣው ሰው ነው።” በጋቦን እግር ኳስ ውስጥ ግን “በርካታ አጥፊዎች” አሉ ሲሉ የፊፍፕሮ የህግ አማካሪ ሎይክ አልቬስ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ፕሮግራም ተናግረዋል።

“ይህ አዎንታዊ የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው” ነው ሲሉም አልቬስ አክለዋል።

ስለጉዳዩ እአአ በ2021 የእንግሊዙ ጋርዲያን ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዘገበው በኋላ ታዳጊ ተጫዋቾችን በመድፈር እና በመበዝበዝ የቀረበበትን ክስ አምኗል።

ገለልተኛው የፊፋ የሥነ ምግባር ኮሚቴ በአዪ ላይ ምርመራውን የጀመረው በተመሳሳይ ዓመት ነው።

ከዕድሜ ልክ እገዳው በተጨማሪ አዪ 1.1 ሚሊዮን ዶላር የተቀጣ ሲሆን አሁን በእስር ላይ ይገኛል።

“በአዪ ላይ የሚደረገው ምርመራ ከ2006 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው በገለጹ አራት በሚደርሱ ወንድ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ቅሬታ ላይ የተመሰረተ ነው። እነዚህ ክስተቶች የተፈጸሙት ተጫዋቾቹ ታዳጊዎች በነበሩበት ወቅት ነው” ሲል ፊፋ ገልጿል።

በአዪይ ጥቃት ከተሰነዘረባቸው እና ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ አንድ ግለሰብ እገዳው እንዳስደሰተው ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በሌላ በኩል ግን አልረካሁም። ምክንያቱም እኛ እዚህ ላይ እንድንቆም ስለማልፈልግ ነው። ሙሉ ለሙሉ መበተን ያለበት መረብ ነው። አብዛኛዎቹ ጥቃት አድራሾች በነጻነት እየተንቀሳቀሱ ነው” ብሏል።

ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል የጋቦን እግር ኳስን በሁሉም ደረጃ በሚባል ስላመሰው የወሲብ ጥቃት መረብን በተመለከተ እአአ በ2023 ቢቢሲ አፍሪካ 30 ምስክሮችን አነጋግሯል።

አንድ ተጎጂ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ ጥቃት እንደደረሰበት አስታውቋል። ለጋቦን ብሔራዊ ቡድን ለበርካታ አመታት የተጫወተው ሌላ ተጫዋች ደግሞ ከ14 ዓመቱ ጀምሮ ጥቃት እንደደረሰበት ገልጿል።

ጥቃቱን ከፈጸሙት አካላት ጋር በመሆን እንደ ፊፋ እና የጋቦን ብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፌጋፉት ያሉ ተቋማት ታዳጊዎችን ከጥቃት መከላከል አልቻሉም የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሁለቱም አካላት የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።