
ከ 6 ሰአት በፊት
የኬንያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሆኖ የተሾመው ደቡብ አፍሪካዊው ቤኒ ማካርቲ “ኬንያ ለቀጣዩ 2026 የዓለም ዋንጫ በማለፍ ብዙዎችን ልታስደንቅ እንደምትችል” ተናገረ።
በአንድ ወቅት ከአገሩ አልፎ የአህጉሪቱ ኮከብ ተጫዋች የነበረው ቤኒ ማካርቲ የኬንያውን ሐራምቤ ቡድንን ለቀጣዩ ሁለት ዓመት እንዲያሠለጥን ስምምነት ላይ ደርሷል።
የኬንያ ቡድንን በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ከማሳተፍ ባለፈው በአውሮፓውያኑ 2027 የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫንም አዲሱ አሠልጣኝ እያለመ ነው።
ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ በኬንያ፣ በታንዛኒያ እና በኡጋንዳ በጋራ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።
የ47 ዓመቱ ቤኒ ማካርቲ ቡድኑን ከጊዜያዊ አሠልጣኙ ፍራንሲስ ኪማንዚ ይረከባል።
ቱርካዊው አሠልጣኝ ኢንጂን ፍራት ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት መገባደጃ ላይ ኃላፊነቱን መልቀቁን ተከትሎ ነው ቡድኑ በጊዜያዊ አሠልጣኝ ሲሰለጥን የነበረው።
ማካርቲ ቡድኑን ከተረከበ በኋላ የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ በጋምቢያ ያደርጋል። ከዚያም በሜዳው ኬንያ ከጋቦን ጋር ቀጣዩን ጨዋታ ያደርጋል።
“በዓለም ዋንጫ ላይ መሳተፍ በዓለም ላይ ለየት ካሉ ልዩ ስሜቶች አንዱ ነው። እሱንም ዕድል ልሰጣቸው እፈልጋለሁ” ሲል ማካርቲ ከቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።
“ተጫዎቾቹ ቁርጠኝነት ካላቸው፣ ለመመማር እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ለጨዋታው ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑ ለዓለም ዋንጫ ብቁ በመሆን ብዙ ሰዎችን የምናስደንቅ ይመስለኛል” ብሏል።
ኬንያ በምድብ ኤፍ ከተደለደሉት ስድስት ቡድኖች በአራተኛ ደረጃ ተቀምጣለች።
በአራት ጨዋታዎች አምስት ነጥብ አስመዝግባ ከቡድኑ መሪ አይቮሪ ኮስት በአምስት ነጥብ ርቃለች።
ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና አሜሪካ በጥምረት ለሚያዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ብቁ የሚሆኑት የምድቦቹ አሸናፊዎች ናቸው።
ከዘጠኙ ቡድኖች በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጡ አራት ምርጦች በውድድር ሁለተኛ ዕድል ይኖራቸዋል።
በደቡብ አፍሪካ ታሪክ ግብ በማስቆጠር የምንጊዜም ክብረወሰንን የጨበጠው ማካርቲ፤ አገሩን በአውሮፓውያኑ 1998 እና 2002 በዓለም ዋንጫ ወክሎ ተጫውቷል።
ሆኖም አሁን አዲስ አሠልጣኝ የሆነባት ኬንያ ለዓለም ዋንጫ ውድድር ብቁ ሆና አታውቅም።
- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር መቻል እና ሲዳማ ቡናን በድምሩ 39 ሚሊዮን ብር ቀጣ25 የካቲት 2025
- አዲሱ የበረኞች የ8 ሰከንድ ሕግ ምን ምን ጉዳዮችን ይዟል? የትኞቹ ግብ ጠባቂዎችስ ሰዓት ያባክናሉ?4 መጋቢት 2025
- “‘ወንድ ነሽ ተብዬ’ ከሴቶች እግር ኳስ ተገለልኩ” መሳይ ተመስገን1 መጋቢት 2025

ከሞሪንሆ እና ቴን ሃግ ጋር መሥራት
ቤኒ ማካርቲ በአፍሪካ እግር ኳስ ስመ ጥር ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ ነው። ከአህጉሪቷም ዘልቆ በአውሮፓ የተሳካ የእግር ኳስን ሕይወት አሳልፏል።
ከሆላንድ ቡድኑ አያክስ ጋር የሆላንድ ሊግ እንዲሁም የክለቡን ዋንጫ አንስቷል።
በፖርቹጋል በፖርቶ ክለብ በጆዜ ሞሪንሆ አሠልጣኝነት የአውሮፓውያኑ 2004 የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ሆኗል።
የቀድሞው አጥቂ ከብላክበርን ሮቨርስ እንዲሁም ከዌስትሃም ጋር በፕሪሚየር ሊጉ አምስት ዓመታትን አሳልፏል።
ከዚያም ወደ አገሩ ደቡብ አፍሪካ ተመልሶ ለኦርላንዶ ፓይሬትስ በመጫወት ጫማውን ሰቅሏል።
የአሠልጣኝ ሕይወቱንም የጀመረው በቤልጂየሙ ክለብ ሲንት ትሩይደን በረዳትነት ነው።
በመቀጠልም ወደ አገሩ አቅንቶ የኬፕታውን ከተማን እንዲሁም አማዙሉ የተሰኙትን ቡድኖች አሠልጥኗል።
በቅርብ ጊዜም በማንችስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ተመርጦ የአሠልጣኝ ቡድኑ ውስጥ እንዲካተት ተደርጎ ነበር።
“በዓለም ላይ ካሉት ታላቅ እና ምርጥ ከሆነው ክለብ ጋር ለመሥራት ድንቅ ዕድል አግኝቼ ነበር” ሲል ማካርቲ በኦልድ ትራፎርድ ስለነበረው ቆይታ ተናግሯል።
“በጣም የምወደውን ለማድረግ ጊዜው አሁን እንደሆነ ተሰማኝ፤ ይህም አሠልጣኝ መሆን እና ተጫዋቾች እንዲያድጉ መርዳት።”
“ይህ ዕድል [የኬንያ አሠልጣኝነት] ሲመጣ ሁሉንም ነገር ለሰጠኝ አህጉር ከማገልገል በላይ የተሻለ የት ይኖራል አልኩኝ” ብሏል።

መሸነፍ የሚጠላው ማካርቲ
ኬንያ እስከ አውሮፓውያኑ 2022 ድረስ ከዓለም አቀፍ እግር ኳስ ታግዳ ነበር።
ለዚህም የአገሪቱ ስፖርት ሚኒስቴር ብሔራዊ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ገንዘብ አላግባብ መዝብሯል በሚል መበተኑን ተከትሎ ነው።
ነገር ግን በቅርብ የተደረጉ ምርጫዎችን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ አዲስ አስተዳደር አዋቅሯል።
የቀድሞው የኢንተር ሚላን አማካኝ ተጫዋች ማክዶናልድ ማሪጋ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኗል።
የማካርቲ ሹመት የቀጣዩ አፍሪካ የዓለም ዋንጫን በጋራ ለማዘጋጀት ሽር ጉድ እያለ ላለው ፌዴሬሽን ጠንክሮ እየሠራ መሆኑ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
የኬንያን ቡድን የሚመራው ማካርቲ ራሱን ሲገልጽ “መሸነፍን የሚጠላ ልዩ አሸናፊ” በማለት በታታሪነት ፍልስፍናውም የአሸናፊነትን መንፈስ ለኬንያውያን ቃለ እየገባላቸው ነው።
“ለእኔ፤ ለደጋፊዎች፣ ለእውነተኛ ኬንያውያን ማንነታቸውን መስጠት ነው” ሲል ያብራራል።
“የኬንያ ሕዝብ በታታሪ ሠራተኝነት፣ በታማኝነታቸው ይታወቃሉ። እናም እኔም ልሰጣቸው የምፈልገው ይህንኑ የሚያንጸባርቅ ብሔራዊ ቡድን ነው” በማለት ያስረዳል።
“ስለዚህ በእኔ ስር ያሉ ተጫዋቾች ያንኑ ጽኑ ፍላጎት፣ ያን ዓይነት ስሜት ሊኖራቸው ይገባል፤ ልክ የኬንያ ማሊያ ለብሰህ እንደምትሞት ዓይነት።”
የሚለው ማካርቲ “ምክንያቱም ከዚያ ሜዳ ስትወጡ ሰዎች ሊኮሩብህ ይገባል” ሲል አጠቃሏል።
