
6 መጋቢት 2025
የደቡብ ሱዳን ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ወታደራዊ ክንፍ የጦር አዛዥ ጄነራል መታሰር ለአምስት ዓመታት የዘለቀውን የእርስ በርስ ጦርነት የቋጨውን የሰላም ስምምነት “የጣሰ ነው” ሲሉ የተቃዋሚው ቃለ አቀባይ ተናገሩ።
ጄኔራል ጋብርኤል ዲዮፕ ላም እንዲሁም በተቃውሞ ላይ ያለው የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ (ኤስፒኤልኤም-አይኦ) ከፍተኛ ባለስልጣናት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለእስር ተዳርገዋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት የጦር ጄነራል እና ከፍተኛ ባለስልጣናቱ በአውሮፓውያኑ 2013 ከፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ጋር ከፍተኛ ሽኩቻ ውስጥ የገቡት የምክትል ፕሬዚዳንቱ ሪክ ማቻር አጋር ናቸው። በሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው የተነሳው የስልጣን ውጥረት አገሪቷን ደም አፋሳሽ ወደሆነ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መክተቱ ይታወሳል።
ሐሙስ ጥዋት የማቻር ቃል አቀባይ ፓርቲያቸው ባለስልጣኖቻቸው የት እንዳሉ ወይም የት እንደታሰሩ አያውቅም ብለዋል።
“ሁኔታዎች የበለጠ እንዳይባባሱ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፤ ነገር ግን ይህች አገር ዳግም ወደ ጦርነት እንዳትመለስ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን ማሳየት ያላባቸው የሰላም አጋሮቻችን ናቸው ሲሉ ፑዎክ ቦዝ ባሉዋንግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ደቡብ ሱዳን ተመልሳ ወደ ጦርነት አትገባም ሲሉ መናገራቸውን የመንግሥት ቃል አቀባይ ማኩዩ ረቡዕ ዕለት በመዲናዋ ጁባ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የተቃዋሚዎቹ ባለስልጣናት የታሰሩት “ከህግ ጋር በመጋጨታቸው” እንደሆነ ቃል አቀባዩ አክለዋል።
- ኢሉሚናቲዎች መነሻቸው ከየት ነው? ዓለምንስ በምሥጢር ‘ይቆጣጠራሉ’?6 መጋቢት 2025
- ቻይና ከአሜሪካ ጋር ለሚደረግ ‘ማንኛውም ጦርነት’ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች6 መጋቢት 2025
- አውሮፓ “የታሪክ እጥፋት ላይ ትገኛለች” ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት አስጠነቀቁ6 መጋቢት 2025

በአውሮፓውያኑ 2011 ከሱዳን የተገነጠለችው ደቡብ ሱዳን የአለማችን አዲሲቷ አገር ናት። ነጻነቷን ከተቀዳጀች ከሁለት ዓመት በኋላ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ሙሉ ካቢኔያቸውን በማባረር እንዲሁም ምክትላቸውን ማቻርን ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት አነሳስተዋል ሲሉ ወነጀሉ።
በዚህም የተነሳ አገሪቱ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገባች።
400 ሺህ ሰዎች ህይወታቸውን ካጡ እንዲሁም 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ ከአምስት ዓመታት በኋላ፣ በአውሮፓውያኑ 2018 የሰላም ስምምነት ላይ ተደረሰ።
ሆኖም እስካሁን ድረስ የሰላም ስምምነቱ በጸና መሰረት ላይ አልቆመም።
ጄነራል ላም የተቃዋሚ ፓርቲው ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ ሲሆን ከሱዳን ጦር ጋርም መዋሃድ ነበረባቸው።
ሆኖም ማክሰኞ ዕለት በቁጥጥር ስር ውለው ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።
ሌላኛው የማቻር አጋር የሆኑት የነዳጅ ሚኒስትሩ ፑዎት ካንግ ቾል በጸጥታ ኃይሎች ሌሊት ላይ ተወስደዋል።
በመዲናዋ ጁባ የሚገኘው የማቻር ቤት በደቡብ ሱዳን ጦር ለአንድ ሌሊት ከተከበበ በኋላ ስፍራውን ለቀው ወጥተዋል።
የማቻር አጋር የሆኑ ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት በሙሉ በቁም እስር ላይ መሆናቸውን ቢቢሲ ተረድቷል።
ባለስልጣናቱ በቁጥጥር ስር የዋሉት ዋይት አርሚ የተሰኘው ጦር በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የላይኛው የናይል ተፋሰስ አካባቢ የምትገኝ ስትራቴጂካዊ ከተማን ከመንግሥት ወታደሮች ጋር ተዋግተው ከተቆጣጠሩ በኋላ ነው።
በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት ዋይት አርሚ ከማቻር ጦር ጋር ወግኖ ተፋልሟል።
ለፕሬዚዳንቱ ታማኝ የሆኑ የሰራዊቱ አባላት የማቻር አጋሮች አማጺያኑን ይደግፋሉ ሲሉ ከሰዋል።
የማቻር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት በዋይት አርሚ እና በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት የብሄራዊ ጦር አመራሮች የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ አድርገውት ቢሆን ኖር “ይቀር ነበር” ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት በዚህ አካባቢ የተነሳው ግጭት ሊዛመት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
መቀመጫውን ጁባ ያደረገው የሰላም እና አድቮኬሲ ማእከል ኃላፊ ቴር ማንያንግ በበኩላቸው እየተካሄደ ያለው ውጊያ የሰላም ስምምነቱን አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ እና አገሪቱንም ድጋሜ ወደ ጦርነት ሊከት እንደሚችል ለሮይተርስ ገልጸዋል።
ደቡብ ሱዳን እስካሁን ድረስ ምርጫ አድርጋ የማታውቅ ሲሆን ከረጅም ጊዜ መዘግየት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2026 ሊደረግ ዕቅድ ተይዟል።