
ከ 4 ሰአት በፊት
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር በመጪው ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ ልታደርገው ያቀደችው ውይይት “ትርጉም ያለው” እንደሚሆን ተስፋቸውን ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ በሳዑዲ አረቢያ ቢገኙም በውይይቱ የማይሳተፉ ሲሆን አገራቸው “አስቸኳይ እና ዘላቂ” ሰላምን ለማምጣት እየሰራች ነው ብለዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በበኩላቸው የአሜሪካ ቡድን የሩስያ እና የዩክሬን ጦርነት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት የሚያስችለውን “ማዕቀፍ” መወያየት ይፈልጋል ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት የዩክሬኑ መሪ ዜሌንስኪ እና ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዋይት ሃውስ ሊያደርጉት የነበረው ውይይት ወደ ግጭት እንዲሁም ዘለፋ ተቀይሯል።
በዚህም ወቅት ትራምፕ አቻቸውን ዜሌንስኪን ጦርነቱን ለመቋጨት ዝግጁ አይደሉም ሲሉ ወቅሰዋቸው ነበር።
በመሪዎቹ መካከል የተፈጠረውን የዲፕሎማሲ ቀውስ ተከትሎ አሜሪካ ከዚህ ቀደም ታደርገው የነበረውን ወታደራዊ ዕርዳታ እንዲሁም የመረጃ ልውውጥን አቁማለች።
ዜሌንስኪ ውይይቱ ወደዚህ ማምራቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸው ከአገራቸው ከፍተኛ የጦር መሳሪያ አቅራቢ ከሆነችው አሜሪካም ጋር ግንኙነታቸውን ለመጠገን እየሞከሩ ይገኛሉ።
ሐሙስ ዕለት ትራምፕ “የይቅርታ” እንዲሁም “የምስጋና” ደብዳቤ ከዜሌንስኪ እንደደረሳቸው ዊትኮፍ ተናግረዋል።
- “‘ቁርጭምጭሚት’ የሚለው ቃል ያስቀኛል” ለ23 ዓመታት ለፈረንጆች አማርኛን ያስተማረችው ፖላንዳዊት፣ ዶ/ር ኤቫ ቮልክ-ሶሬከ 6 ሰአት በፊት
- የደቡብ ኮሪያ ተዋጊ ጄቶች ስምንት ቦምቦች በስህተት በመጣላቸው በርካቶች ተጎዱከ 5 ሰአት በፊት
- “ኬንያ ለመጪው የዓለም ዋንጫ በማለፍ ብዙዎችን ማስደነቅ ትችላለች” አዲሱ አሠልጣኝ ቤኒ ማካርቲከ 6 ሰአት በፊት
“ከዩክሬናውያን ጋር ወደ ትክክለኛው መንገድ እንደምንመጣ እና ሁሉም ነገር እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ዊትኮፍ አክለዋል።
ዜሌንስኪ ከማንኛውም የሰላም ድርድር በፊት ስምምነት ውስጥ እንዲገቡ አሜሪካ ከፍተኛ ጫና ስታደርግባቸው የቆየች ሲሆን እሳቸው በበኩላቸው ለአገራቸው ጥብቅ የጸጥታ ዋስትና እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያነሱት ነው።
ሩሲያ ከሶስት ዓመታት በፊት የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ የዩክሬንን 20 በመቶ ግዛት ተቆጣጥራ ትገኛለች።
ዜሌንስኪ የመከላከያ ወጪን የመጨመር ዕቅዶች ባጸደቁበት የአውሮፓ ህብረት መሪዎች የብራስልስ ቀውስ ጉባኤ ላይ ከተገኙ በኋላ በሳዑዲ አረቢያ ስለሚደረገው የአሜሪካ እና ዩክሬን ውይይት በማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ ተከታታይ ጽሁፎችን አስፍረዋል።
“የዩክሬን እና የአሜሪካ ቡድኖች ስራቸውን ቀጥለዋል፤ እናም በሚቀጥለው ሳምንት ትርጉም ያለው ውይይት እንደሚኖረን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
“ዩክሬን ከጦርነቱ ጅማሮ ጀምሮ ሰላምን መሻቷን ቀጥላለች። ጦርነቱ እየቀጠለ ያለው በሩሲያ ምክንያት ብቻ ነው” ብለዋል። ዜሌንስኪ ሞስኮ ጦርነቱን እንድታቆም የዓለም ማህበረሰብ የበለጠ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል።
በተጨማሪም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአየር እና በባህር ላይ የሚደረግ የተኩስ አቁም፣ በሃይል እና በሌሎች የሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም ያቀረቡትን የእርቅ ዕቅድም ጠቅሰዋል።
ሩሲያ፣ ፈረንሳይ ባቀረበችው የሰላም ዕቅድ ላይ አስተያየቷን አልሰጠችም።
ሐሙስ ዕለት፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው የምትፈልገው ሰላም “በዘላቂነት መረጋጋትን የሚሰጣትን ነው” ብለዋል።
“የሌሎች የሆነ ምንም ነገር አንፈልግም ነገር ግን የእኛ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አሳልፈን አንሰጥም” ብለዋል ፑቲን
ሩሲያ የዩክሬን ደቡባዊ ክሪሚያ ግዛት በአውሮፓውያኑ 2014 የጠቀለለች ሲሆን ሌሎች ሙሉ በሙሉ የማትቆጣጠራቸው አራት የዩክሬን ግዛቶችም የራሴ ግዛቶች ናቸው የሚል ጥያቄን ታነሳለች።