
ከ 6 ሰአት በፊት
ፓላንዳዊት ናት። አማርኛን ከ40 ዓመት በፊት ነው የተማረችው።
እሷ አማርኛ ስትማር ጓድ መንግሥቱ ምናልባት የእድገት በኅብረት ዘመቻን እያሰናዱ ነበር። እንደው የጊዜውን ርዝማኔ ለማስታወስ ነው እንጂ ነገሩ ምንም ግንኙነት የለውም።
እና ያኔ ድሮ አማርኛን በዲግሪ ተመርቃ እስከዛሬ ታስተምራለች።
ላለፉት 23 ዓመታት በርካታ ፈረንጅ በአማርኛ ቋንቋ ዲግሪ አስይዛለች።
ዶ/ር ኤቫን ‘አንቺ’ እንበላት እንጂ በሥራዋ አንቱታን የተጎናጸፈች ሴት ናት። የአማርኛ የቁልምጫ ስሟ ሔዋን ይባላል።
ብታምኑም ባታምኑም፣እሷ የምታስተምርበት ዋርሶ ዩኒቨርስቲ አማርኛን ማስተማር ከጀመረ 75 ዓመት አልፎታል።
ለነገሩ ይሄ ምኑ ይደንቃል?
በምኒልክ ጊዜ አማርኛ በአውሮፓ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ይሰጥ ነበር

ኔፕልስ፣ ፓሪስ እና ሐምቡርግ ዩኒቨርስቲዎች አማርኛ ማስተማር ከጀመሩ 100 ዓመት አልፏቸዋል።
ይህ ለብዙ ሰው ዜና ነው።
በኔፕልስ አማርኛን ማስተማር የጀመሩት አፈወርቅ ገብረየሱስ ናቸው። ይህ ማለት በ1890ዎቹ መሆኑ ነው። ጥንት በዓድዋ ዘመን።
አማርኛ በጀርመን፣ ሐምቡርግም ዩኒቨርስቲም ይሰጣል። እዚያም ድሮ ነው የተጀመረው። ዛሬም ድረስ አለ፤ ለዚያውም ሳይቋረጥ።
ይቆጠር ከተባለ 105 ዓመት ሆኖታል፣ ዘንድሮ።
የመጀመሪያው መምህር ወልደማሪያም ደስታ የሚባሉ ሰው ናቸው። በ1909 ከአንኮበር-ሐምቡርግ ሄደው አምስት ዓመት አስተምረዋል።
በዶክተር ኤቫ አገር፣ ፖላንድ አማርኛን ማስተማር የጀመሩት ፕሮፌሰር ስቴፋን ስትሬልሲን ናቸው።የዛሬ 75 ዓመት ገደማ።
እሳቸው አማርኛን ያጠኑት በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ነው። ቋንቋውን የተማሩት ደግሞ በፈረንሳይ ነው። እኚህ ሰው ከባድ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነበሩ ይባላል።
በዚህም ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የወርቅ ኒሻን ተበርክቶላቸዋል።
1950ዎቹ የአፍሪካ ጥናትን ከመሠረቱ ወዲህ ብዙ ለፉ። አማርኛን በአውሮፓ አስፋፉ።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ1981 ሕይወታቸው አለፈ።
እርሳቸው የመሠረቱት ተቋም ሰፍቶ፣ አድጎ እና ተመንድጎ በ1977 የአፍሪካ ቋንቋዎች እና ባሕል ትምህርት ክፍል ተባለ።
ከአማርኛ እና ከግዕዝ ሌላ ሐውሳ እና ስዋሂሊ ቋንቋዎችን ማስተማር ጀመረ።
ዶ/ር ኤቫ በዚህ ዘመን ባስቆጠረ ተቋም ነው አማርኛን የምታስተምረው።
እሷ ፕሮፌሰር ስቴፈንን አልደረሰችባቸውም። በዝና ነው የምታውቃቸው።
የዋርሶ ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ትምህርት ክፍል ብዙ ተማሪ አይቀበልም።
አንዱ ምክንያት ብዙ ተማሪዎች አማርኛ ከባድ ነው ብለው ስለሚፈሩ ነው። ከጀመሩት ውስጥ ሲሶዎቹ አይጨርሱትም።
በየዓመቱ በአማካይ 10 ተማሪዎችን ይቀበላል። ግዕዝን ደግሞ እንደ ኮርስ ለማንኛውም ለፈለገ ተማሪ ይሰጣል።
በ75 ዓመታት ውስጥ ቁጥራቸው ከመቶ ትንሽ ከፍ ያሉ ተማሪዎች በማስተርስ አስመርቋል። 12 የሚሆኑት ፒኤችዲ ይዘዋል።
የሆነስ ሆኖ፣ የዛሬ 40 ዓመት ኤቫ አማርኛ ለመማር እንዴት ወሰነች?
- በቻይና ቤይጂንግ ዩኒቨርሲቲ አማርኛ ቋንቋ የምታስተምረው ቻይናዊት26 ነሐሴ 2021
- በአስር ወራት አማርኛ የቻለው ጀርመናዊ5 ነሐሴ 2019
- በኢትዮጵያ አምስት ሰዎች ብቻ የሚናገሩት ቋንቋ15 የካቲት 2023


“አማርኛን በአጋጣሚ ነው የተማርኩት”

“አጋጣሚ ነው” ትላለች።
“ሒሳብ፣ ሕግ፣ ፊዚክስ እንደዚህ ዓይነት ትምህርት ብዙም አይማርከኝም ነበር። ከዚያ ይልቅ ሥነ ጥበብ፣ ኪነ ጥበብ፣ ቋንቋ እና የሩቅ አገር ባሕል ይማርከኝ ነበር።”
ዋርሶ ዩኒቨርስቲ ያኔ ድሮ የኦሪየንታል ጥናት ክፍል ነበረው። ዶ/ር ኤቫ እዚያ ስለሚሰጠው የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ሰማች። ተሳበች። ተመዘገበች፣ ተማረች። ተመረቀች።
ታሪኳ በአጭሩ ይኸው ነው።
አማርኛን ለአምስት ዓመታት ነው የተማረችው። አራት ዓመት በፖላንድ ከተማረች በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስኮላርሺፕ አግኝታ 1 ዓመት ወደ ኢትዮጵያ አቅንታ ከአገሬው ጋር ተምራለች።
ኢትዮጵያ የመሄድ አጋጣሚን መጀመሪያ ስታገኝ እንዴት እንደፈነደቀች።
“እኔ ወጣት በነበርኩበት በዚያ ዘመን እኛ ስለ ኢትዮጵያ ምንም አናውቅም፤ ፖላንድ ውስጥ በትምህርት ቤት ጭራሽ ስለ ኢትዮጵያ ምንም ተምረን አናውቅም. . .” ትላለች።
“አማርኛ ቋንቋ ሲሰሙት እንደ ፏፏቴ ያለ ነው”

አምስት ቋንቋዎችን አቀላጥፋ የምትናገረው ዶክተር ኤቫ ‘ከቋንቋዎች ሁሉ አማርኛ ለምን ማረከሽ?’ ስትባል ‘ድምጹ ነዋ!’ ትላለች።
ብዙዎች ጀርመንኛ ኮስተር ያለ ነው። ፈረንሳይኛ ፍቅር ነው። አረብኛ ሉስሉስ ነው ይላሉ። ለመሆኑ አማርኛ ለባዕድ ጆሮ እንዴት ያለ ነው?
“የፏፏቴ ድምጽ ነው ያለው. . .” ትላለች ዶክተር ኤቫ።
“ሰዎች ሲያወሩት መስማት በቃ ፏፏቴ ሲፈስ እንደመስማት ያለ ነው።”
ጥበብ ስለምትወድ አማርኛ ድምጹ ብቻ ሳይሆን አጻጻፉ ማረካት። ፊደል ትወዳለች። እያንዳንዱ ቅርጽ ውብ የጥለት ጥልፍ ሆኖ ነው የሚታያት።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሄድ ደግሞ የምግቡን ዓይነት እና ብዛት የባሕሉን ጉራማሌነት ወደደችው። ያልወደደችው ግን አንድ ነገር ብቻ ነበር።
ጉርሻን።
“ጉርሻ አስጨናቂ ነገር ነው”

“ባሌ ጉራጌ ነው” የምትለው ዶ/ር ኤቫ ክትፎ ግን የምትሞትለት ምግብ አይደለም።
“ያሳዝናል፣ ክትፎ ለኔ ጨጓራ አልተሠራም” ትላለች።
ለእርሷ አንደኛ ምግብ “ጎመን በሥጋ” ነው።
ቢሆንም ራሷ ስትበላው ነው እንጂ ሲያጎርሷት አትወድም።
ዶክተር ኤቫ እናት አገሯን ፖላንድን እና ኢትዮጵያን አነጻጽሪ ስትባል ሁለቱን ሕዝቦች እንግዳ ተቀባይነት ብቻ ያመሳስላቸዋል ትላለች። ከዚያ በተረፈ የጋራ ነገር አላገኘችም።
በፖላንድ “እንጀራችን ድንች ነው” የምትለው ኤቫ ከኢትዮጵያ ባሕል ጉርሻ እጅግ ያስገርማታል።
“. . . ጉርሻ ለእኔ በጣም የሚያስፈራ ነገር ነው። አንደኛ ትልቅ ነው፤ ለመዋጥ ያስቸግራል። ሁለተኛ በአንድ አያበቃም” ትላለች።
‘የእናት ጡት ሁለት ነው’ ተብሎ ጉርሻ የሚደገመው ነገር ይስቃታል። የሚወዱትን ሰው ሁለት ጊዜ ለማጉረስ የተፈጠረ አባባል ሆኖ ነው የሚሰማት።

‘ፍቅር እስከ መቃብርን’ ወደ ፖላንድ ቋንቋ
በአፍሪቃ ቋንቋዎች እና ባሕሎች ተቋም በሥነ-ልሳን ክፍል አማርኛ የሚያስተምሩት እሷ እና ባልደረባዋ ፕሮፌሰር ማርቲን ናቸው።
ፕሮፌሰር ማርቲን ከአማርኛ በተጨማሪ ግዕዝም ያስተምራሉ።
ዶ/ር ኤቫ ድሮ አማርኛ ስትማር 7 ፈረንጆች አብረዋት ነበሩ፤ የክፍሏ ልጆች። አሁን በተለያየ ዓለም በተለያየ ዘርፍ ይሠራሉ።
አንዳንዶቹ በኤምባሲ፣ አንዳንዶቹ ምናልባትም አማርኛውን ጨርሶ ረስተውት ይሆናል።
እርሷ ግን ያኔ በዲግሪ እንደተመረቀች ወዲያውኑ ለእረፍት ለንደን ሄደች።
በዚያው በለንደን ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል እና የአፍሪካ ጥናት ገባች። እዚያው ደግሞ የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ወሰደች።
ፍቅር እስከ መቃብር እና ሌሎች የአማርኛ ልቦለድ ታሪኮችን መተርጎም የጀመረችው ያኔ ነው። እስከዛሬ ግን አልጨረሰችውም።
‘ፍቅር እስከ መቃብር’ ወደ ፈረንሳይኛ እና ወደ ኖርዌይ ቋንቋ ተመልሷል። የእሷ ህልም ወደ ፖሊሽ መተርጎም ነው።
አሁን ስለእሱ ብዙ ማውራት አትፈልግም። “ህልሜን ካሳካሁት በኋላ ብናወራ አይሻልም?” ትላለች።
በሥነ ጽሑፍ ባለሙያ ሆና ከለንዶን ወደ ፖላንድ ከተመለሰች በኋላ ዶክትሬቷን ሠራች።
ከዚያ የበቃች የነቃች የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪ ሆነች።
እርሷ ግን አሁንም “የአማርኛ ቋንቋ ተማሪ ነኝ” ትላለች። ከጎኗ መዝገበ ቃላት አይለያትም።
የሚገርመው በ23 ዓመታት ውስጥ አንድም ሐበሻ ተማሪ ገጥሟት አያውቅም።
በፖላንድ የተወለዱ ሁለተኛ ትውልድ ሐበሾችን ግን አስተምራለች።
ዶክተር ኤቫ ከማስተማሩ ሌላ የአማርኛ አስተርጓሚ ናት።
ለምሳሌ በስደት ወደ ፖላንድ የመጡ አማርኛ ተናጋሪዎች ለጥገኝነት ቃለ መጠይቅ ሲደረጉ ‘ዶክተር ኤቫን ጥሩ’ ነው የሚባለው። እሷ ትጠራለች፤ ታስተረጉማለች።
በፖላንድ ፍርድ ቤትም እንዲሁ የአማርኛ አስተርጓሚ ናት።

“አዲስ አበባ ሲያሙኝ ሰማኋቸው”
የቆዳዋ ቅላት አሳስቷቸው ፈረንጅ ሲያሙ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ሐበሾች አሉ፤ በዶክተር ኤቫ።
አማርኛ የማትችል መስሏቸው ሰዎች በአዲስ አበባ ከአንዴም፣ ሁለት ሦስቴ ሲያሟት ይዛቸዋለች፤ ታዝባቸዋለች። ከመሳቅ ሌላ ግን ልታስደነግጣቸው አልፈለገችም።
ዶ/ር ኤቫ ቀጭን ናት። ‘ቀጮ’ የምትባል ዓይነት ቀጭን።
አንድ ጊዜ ካፌ ቁጭ ብላ ሳለ ከጎን የተቀመጡ ጎረምሶች ‘ሲቦጭቋት’ ሰማቻቸው።
ምን ብለው?
“ሹፋትማ ይቺን የጫት እንጨት የመሰለች ፈረንጅ” ብለው።
ሲያሙኝ ‘ከጆሮዬ ዘለቀ’። ቀጭን ስለሆንኩ እኮ ነው” ብላ ያን ዘለግ ያለ ሳቋን ትስቃለች።

አማርኛ ግን ከባድ ቋንቋ ነው እንዴ?
ዶ/ር ኤቫ “አዎ አማርኛ ከባድ ነው። ቀላል ቋንቋ አይደለም። ቢሆንም ግን ከማንደሪን [የቻይና ቋንቋ] ይሻላል” ትላለች።
ከአፍ መፍቻ ቋንቋዋ ፖሊሽኛ ሌላ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ሩሲያኛ አቀላጥፋ ትናገራለች።
“አማርኛ ከባድ ብቻ ሳይሆን አያልቅም፤ አሁንም እየተማርኩ ነው፣ ገና አያልቅም።”

“‘ቁርጭምጭሚት’ የሚለው ቃል በጣም ያስቀኛል”
ዶክተር ኤቫ የአማርኛ አንዳንድ ቃላት የኮረኮሯት ያህል ያስቋታል።
ለምሳሌ “ቁርጭምጭሚት” የሚለው ቃል።
እግር ላይ ያለች ትንሽ ነገር ለምን ‘ቁርጭምጭሚት’ ተባለች? እያለች ዝም ብሎ ግርም ይላታል። በዚህ ነገር ቁርጭምጭሚቷን ወለም እስኪላት ድረስ ነው የምትስቀው።
“አያስቅም ግን? እስኪ በለውማ ‘ቁ-ር-ጭ-ም-ጭ-ሚ-ት” (ሌላ ረዥም ሳቅ). . .