
ከ 3 ሰአት በፊት
ሱዳን በአገሯ የርስ በርስ ጦርነት ‘በዘር ማጥፋት ወንጀል ተባባሪ ናት’ ያለቻትን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን በአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ልታቆማት ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በዘር ማጥፋት ለሚወነጀለው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድጋፍ እየሰጠች ነው ስትል ሱዳን ከሳለች።
ኤምሬትስ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በምታደርገው ወታደራዊ፣ የገንዘብ እና የፖለቲካ ድጋፍ በምዕራብ ዳርፉር በሚገኘው የማሳሊት ማህበረሰብ ‘የዘር ማጥፋት ወንጀል’ ተባባሪ ናት ሲል የሱዳን መንግሥት ከሷል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በበኩሏ የሱዳንን ውንጀላ ውድቅ በማድረግ “ቀልብ ለመሳብ የሚደረግ ትርዒት” በሚልም በአፋጣኝ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ እሰራለሁ ብላለች።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተፋላሚ ወገኖቹ፣ የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጥሰቶችን በመፈጸም ተወንጅለዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉር አረብ ባልሆኑ ነዋሪዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል በሚል ክስ ቀርቦበታል።
ሱዳን ለአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ባቀረበችው ክስ ላይ “የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ግጭቱን በማቀጣጠል እንዲሁም በምዕራብ ዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸመውን ሚሊሻ ትደግፋለች” ሲል የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
- “‘ቁርጭምጭሚት’ የሚለው ቃል ያስቀኛል” ለ23 ዓመታት ለፈረንጆች አማርኛን ያስተማረችው ፖላንዳዊት፣ ዶ/ር ኤቫ ቮልክ-ሶሬከ 6 ሰአት በፊት
- ዜሌንስኪ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ልታደርገው ያቀደችው ውይይት “ፍሬያማ” እንደሚሆን ተስፋቸውን ገለጹከ 5 ሰአት በፊት
- የደቡብ ኮሪያ ተዋጊ ጄቶች ስምንት ቦምቦች በስህተት በመጣላቸው በርካቶች ተጎዱከ 5 ሰአት በፊት
“የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አለማቀፋዊ የሆነ ጥሰቷ ላስከተለው ጉዳት ሙሉ ካሳን ጨምሮ በጦርነቱ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች ክፍያዎችን ልትፈጽም ይገባል” ብሏል።
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለስልጣን በበኩላቸው ” በሱዳን ጦር ተወካይ በኩል በአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ ምንም አይነት ህጋዊ ሆነ ተጨባጭ መሰረት የሌለው ነው። ከዚህ አስከፊ ጦርነት ለማዘናጋት የተደረገ ሌላ ሙከራ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።
በዳርፉር ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የሚከታተሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሙያዎች ቀደም ሲል የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በቻድ በኩል ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የጦር መሳሪያ ታዘዋውራለች የሚለውን ታማኝነት ያለው እንደሆነ ገልጸው ነበር።
የአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ በህጋዊ መንገድ አስገዳጅ ባይሆንም ጉልህ የሆነ ፖለቲካዊ ተጽእኖ አለው።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የሱዳን ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሲገደሉ፣ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል እንዲሁም አገሪቱን ለከፋ ውድመት ዳርጓታል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሰሜን ዳፉር በተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ ጣቢያ ላይ በደረሰ ከባድ ጥቃት በርካታ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ተገልጿል።
ከኤል ፋሸር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው በአቡ ሹክ የተጨናነቀ ገበያ ማክሰኞ ማምሻውን ለሁለት ሰዓታት ያህል ከፍተኛ ጥቃት እንደተፈጸመበት የአካባቢው ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።