
ከ 2 ሰአት በፊት
እሑድ ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው አርሰናልን ያስተናግዳል።
“ከታሪክ አንጻር ይህ ጨዋታ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው” ይላል የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን።
“ጨዋታው ለዩናይትዱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። ከኤፍኤ ዋንጫ ውጭ ሆነዋል። ቡድኑ በውጤት ቀውስ ውስጥ መገኘቱም ሌላኛው ምክንያት ነው።”
ሱተን ይህንን ተጠባቂ ጨዋታ ጨምሮ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት መርሃ ግብሮችን እንደሚከተለው ተንብይዋል።
ቅዳሜ
ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ማንቸስተር ሲቲ
የቻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለማግኘት የሚደረግ ከባድ ፉክክር ብቻ ሳይሆን ለመገመትም የሚከብድ ጭምር ነው።
ፎረስት በሜዳው እየተከላከለ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክር ተደጋግሞ ታይቷል።
ቡድኑ በኤፍኤ ካፕ እየተፎካከረ ሲሆን በሊጉም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ አሸናፊ ለመሆን ችሏል።
ይህ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ቢደረግበትም ሲቲ በጠባብ ውጤት ያሸንፋል።
ግምት፡ 1 – 2
ብራይተን ከ ፉልሃም
ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ ሲሆን ጨዋታውን የሚያሸንፈው ቡድን እስከ አምስት ያለው ደረጃ ይዞ የማጠናቀቅ ዕድል አለው
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ብራይተን አምስቱንም ሲያሸንፍ ፉልሃም ደግሞ አራቱን አሸንፏል።
በመጀመሪያው ዙር ብራይተን ቢሸነፍም በዚህ ጨዋታ ላይ የትኛውም ዓይነት ውጤት ሊመዘገብ ይችላል።
ግምት፡ 2 – 1
ክሪስታል ፓላስ ከ ኢፕስዊች ታወን
ፓላስ በጉዳት ከሜዳ ከሚርቀው ጂን-ፊሊፔ ማቴታ ውጭ ምን ሊመስል ይችላል የሚለው የሁሉም ጥያቄ ነው።
አጥቂውን በመተካት ኤዲ ኒኪታህ ሊሰለፍ ይችላል። ራሱን የሚያሳይበት ትልቅ አጋጣሚም ይሆናል።
ኢፕስዊች በኖቲንግሃም ፎረስት በመለያ ምት ተሸንፎ ከኤፍኤ ዋንጫ ውጭ መሆኑን ተከትሎ አሁን ትኩረቱ ከሊጉ ላለመውረድ ይሆናል።
ቡድኑ ያለፉትን ስምንት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
ግምት፡ 1 – 1

ሊቨርፑል ከ ሳውዝሃምፐተን
ሊቨርፑል በሊጉ በሰፊ ልዩነት እየመራ ሲሆን በቀጣይ ሳምንት ለሚኖረው የሻምፒዮንስ ሊግ ወሳኝ ጨዋታ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ሊያሳርፍ ይችላል።
አሰልጣኝ አርን ስሎት ሦስተኛ ቡድን ቢኖራቸው ለዚህ ጨዋታ ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም።
ሳውዝሃምፕተን ከዚህ ጨዋታ ምንም ነጥብ አያገኝም።
ግምት፡ 2 – 0
ብሬንትፎርድ ከ አስቶን ቪላ
ይህ በአውሮፓ መድረክ ለመሳተፍ በሚፎካከሩ ቡድኖች መካከል የሚደረግ አጓጊ ጨዋታ ነው።
ቪላዎች ከሻምፒዮንስ ሊግ መልስ ነጠብ መጣላቸውን በዚህ ጨዋታ ይቀለብሱ ይሆን?
የቪላ ውድድር ዓመት የሚወሰንበት ሳምንት ነው። ሻምፒዮንስ ሊግ ከክለብ ብሩዥ ጋር በኤፍኤ ካፕ ደግሞ ፕሪስተንን በተከታታይ ይገጥማሉ።
ግምት፡ 2 – 1
ዎልቭስ ከ ኤቨርተን
ኤቨርተን ዴቪድ ሞዬስን ወደ ቡድኑ ከመለሰ በኋላ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ነው።
በመጀመሪያው ሞዬስ ጨዋታ ከተሸነፉ በኋላ፤ አራት አሸንፈው ሦስቱን አቻ ተለያይተዋል።
ኩኛ በኤፍኤ ካፕ ከበርመዝ ጋር በነበረ ጨዋታ ወቅት ራሱን መቆጣጠር አቅቶት በፈጸመው ጥፋት የሚተላለፍበት ቅጣት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ዎልቭስ ከወራጅ ቀጠና በአምስት ነጥብ ርቆ ይገኛል።
አምስት ነጥብ ብዙ ቢመስልም የኩኛ ቅጣት የሚኖረውን መዘዝ በቀጣይ ጨዋታዎች የምንመለከተው ይሆናል።
ግምት፡ 1 – 1

እሑድ
ቼልሲ ከ ሌስተር
ባለፈው ሳምንት ሳውዝሃምፕተን በዚህኛው ደግሞ ሌስተር።
ቼልሲ በቀላሉ ሦስት ነትቦችን የሚያሳካባቸው ጨዋታዎች ተከታትለው መጥተዋል።
ከቼልሲ በላይ የተቀመጡት ፎረስት እና ማንቸስተር ሲቲ እርስ በእርስ በሚገናኙበት ጨዋታ ሰማያዊዎቹ በቀላሉ የሚያሸንፉት መርሃ ግብር ሆኖላቸዋል።
የሌስተሩ አሰልጣኝ ሩድ ቫንኒስተልሮይ በብዙ ችግሮች የተተበተበውን ቡድንን ተረክቧል።
አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው የማንቸስትር ዩናይትድ ተጠባባቂ አሰልጣኝ በነበረበት ወቅት በተከታታይ ሁለት ጊዜ ስላሸነፋቸው ይመስላል።
ግምት፡ 3 – 0
ቶተንሃም ከ በርንመዝ
ቶተንሃም አሰልጣኝ አንጅ ፖስትኮግሉን ካባረረ የሚተኳቸው የበርንመዙ አንዶኒ አራዮላ እንደሚሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው።
የቶተንሃም የውድድር ዘመን የሚለካው በዩሮፓ ሊግ በሚያስመዘግቡት ውጤት ነው።
ዶምኪን ሶላንኬ፣ ሚኪ ቫን ደ ቬን እና ክርስቲያን ሮሜሮ ከጉዳት ቢመለሱም ምን ያህል ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው የሚለው ጥያቄ ያስነሳል።
በርንመዝ በዚህ ዓመት ቶተንሃምን አንድ ለምንም ማሸነፍ ችሏል።
በርንመዞች ወደፊት ሲሄዱ በፍጥነት ነው። በጨዋታው በርካታ ጎሎች ይቆጠራሉ ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 2 – 2
ማንቸስተር ዩናይትድ ከ አርሰናል
አርሰናል በሊጉ ጎሎችን ማስቆጠር ቢከብደውም በሻምፒዮንስ ሊጉ ፒኤስቪ ላይ ጎሎችን አዝንቧል።
ዩናይትድ ጥሩ ከሚባሉ ቡድኖች ጋር ሲጫወት መነሳሳቱ ይጨምራል።
ዩናይትድ ጨዋታውን ከባድ ሊያደርግባቸው ቢችልም አሸናፊነቱ የመድፈኞቹ ይሆናል።
ግምት፡ 0 – 1
ሰኞ
ዌስት ሃም ከ ኒውካስል
በግራሀም ፖተር ስር ዌስት ሃም ማንሰራራት እያሳየ ሲሆን ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ኒውካስሉ አሰልጣኝ ኤዲ ሃው ፈተና የሚጀምረው ደግሞ ማን ጤነኛ ሆኖ ይሰለፋል የሚለው ነው።
አሰልጣኙ ከሚቀጥለው ሳምንት ካራባኦ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በፊት ተቻዋቾችን ለማሳረፍ የሚመርጡ አይመስልም።
አሌክሳንደር ኢዛክ መሰለፉ የሚያጠራጥር ሲሆን ሌዊስ ሃል (በጉዳት) እና አንቶኒ ጎርደን (በቅጣት) አይሰለፉም።
ግምት፡ 1 – 1