የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ህንጻ

7 መጋቢት 2025, 14:06 EAT

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት “ክልሉን ዳግም ወደ ግጭት ለማስገባት እንቅስቃሴ ጀምረዋል” ያላቸውን “አንዳንድ” የተቃዋሚው ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) አመራር እና አባሎችን አስጠነቀቀ።

ቦዴፓ በበኩሉ ማስጠንቀቂያው፤ የፓርቲው አመራሮች በቅርቡ የተሻሻለው የክልሉ ሕገ መንግሥት “ተፈጻሚ እንዳይሆን” በዚህ ሳምንት ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ካቀረቡት አቤቱታ ጋር የተያያዘ ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ “በወቅታዊ ጉዳይ” የተሰጠውን ይህንን መግለጫ የያወጣው ትናንት ሐሙስ የካቲት 27/2017 ዓ.ም. ነው። በክልሉ ያሉ ሕዝቦች “በዘመናት አብሮነት የጋራ ማንነቶች ማዳበራቸውን” የገለጸው መግለጫው፤ “ከሀገራዊ ለውጡ ማግሥት አንስቶ” ተከናውነዋል ያላቸውን ተግባራትንም ዘርዝሯል።

“የክልሉን ሠላም በመመለስ፣ የተቋረጡ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲሶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ” የሚደረገው ጥረትም ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከል ናቸው። የክልሉ መንግሥት “የፖለቲካ ምኅዳሩን የበለጠ በማስፋት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ በመሥራት እና የኃላፊነት ቦታዎችንም ጭምር በማጋራት” እየሠራ መሆኑም ተጠቅሷል።

ይሁን እንጂ “እነዚህ ጥረቶች የበለጠ ተጠናክረው እየቀጠሉ” ባሉበት በዚህ ወቅት “ክልሉን ዳግም ወደ ግጭት” ለማስገባት የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውን መግለጫው አንስቷል። የክልሉ መንግሥት፤ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ እየተሳተፉ ነው በሚል የከሰሰው “የውጭ ቅጥረኛ እና ተላላኪ” በማለት የጠቀሳቸውን የተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ “አንዳንድ አመራሮች፣ አባሎች እና ደጋፊዎችን” ነው።

እነዚህ የቦዴፓ አባላት፤ “ክልሉን ዳግም ወደ ግጭት በማስገባት የተሰጣቸውን አጀንዳ ለማስፈፀም እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረዋል” ሲልም በመግለጫው ወንጅሏል። የክልሉ መንግሥት፤ “የሕዝቦች አብሮነት እና ሕብረት የማይመቻቸው፤ ሠላም እና መረጋጋት ሠላም የሚነሳቸው” ሲል በዚህ ውስጥ ተሳትፈዋል ያላቸውን የፓርቲው አመራር፣ አባል እና ደጋፊዎችን ወቅሷል።

እነዚህ ግለሰቦች “አዳዲስ አጀንዳዎችን በመፈብረክ እና በተዛባ መንገድ ሕዝብ ውስጥ በመበተን ለድብቅ አጀንዳቸው ሕጋዊ ሽፋን የመስጠት ሙከራ” ማድረጋቸውንም ጠቀሰው መግለጫው “ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን ለዚሁ ተግባራቸው መቀስቀሻነት እና ሽፋን መስጫነት” እየተጠቀሙ መሆኑንም አንስቷል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ ስብሰባ ላይ
የምስሉ መግለጫ,የክልሉ መንግስት “በማህበራዊም ሆነ በሌሎች የሚዲያ አማራጮች በሚደረግ የሞቅታ ዘመቻ የሚቀየር አንድም ውሳኔ እንደማይኖር” አስገንዝቧል

“በመሠረቱ በማኅበራዊም ሆነ በሌሎች የሚዲያ አማራጮች በሚደረግ የሞቅታ ዘመቻ የሚቀየር አንድም ውሳኔ እንደማይኖር ከልብ መገንዘብ ያስፈልጋል” ሲልም በመግለጫው አጽንዖት ሰጥቷል።

የክልሉ መንግሥት፤ በዚህ ዓይነቱ ጊዜ “ሕግን እና ሥርዓትን የማስከበር ሙሉ ሥልጣን እና ኃላፊነትም ጭምር” ያለው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮው፤ ይህንን መግለጫ ያወጣው “ለተጀመረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጎልበት ሲባል” እንደሆነ ገልጿል።

“የክልሉ መንግሥት ሕግን እና ሥርዓትን ለማስከበር ሲባል ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ እንደማይል ለማረጋገጥ ይወዳል” ሲል በድርጊቱ ውስጥ ተሳትፈዋል ያላቸውን የቦዴፓ አባላት አስጠንቅቋል።

“ከሌሎች ፓርቲዎች እጅግ በተለየ ሁኔታ አጀንዳዎችን በመፍጠር እና በተዛባ ሁኔታ ለሕዝብ በማድረስ” የተጠመዱ የፓርቲው አመራሮች፣ አባሎች እና ደጋፊዎችም “በአስቸኳይ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ” አሳስቧል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ይህንን መግለጫ ያወጣው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን የወከሉ ሦስት የክልሉ ምክር ቤት አባላት በቅርቡ የጸደቁ ሁለት አዋጆችን የተመለከተ አቤቱታ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ካቀረቡ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

አቤቱታውን ካቀረቡት የምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት የቦዴፓ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ፤ የክልሉ መንግሥት መግለጫ ከዚሁ አቤቱታ ጋር የተያያዘ ነው ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መግለጫው፤ የምክር ቤቱ አባላት ያቀረቡትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ “እንደ ጦርነት ቅስቀሳ አድርጎ ነው የወሰደ” ሲሉ ተችተዋል።

በምክር ቤቱ አባላቶች አቤቱታ የቀረበባቸው የክልሉን ሕገ መንግሥት ያሻሻሉ እና የክልሉን ምክር ቤት መቀመጫ ወንበሮች ብዛት ያሳደጉ ሁለት አዋጆች የጸደቁት፤ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በተካሄደው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነበር።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ ከተካተቱ ሦስት ለውጦች ውስጥ አንዱ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ ብዛትን የሚመለከት ነው። የክልሉ ሕገ መንግሥት የምክር ቤቱ የመቀመጫ ወንበር ብዛት ከ100 እንደማይበልጥ ደንግጎ የነበረ ሲሆን፣ አዲሱ ማሻሻያ ይህንን ቁጥር ወደ 165 አሳድጎታል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባላት
የምስሉ መግለጫ,”እያንዳንዱ ወረዳ ያለውን የሕዝብ ብዛት ወደ ወንበር መቀየር ሲገባ አነስተኛ ቁጥር ላለው ወረዳ በርካታ መቀመጫ፤ በርካታ የሕዝብ ቁጥር ላላቸው ወረዳዎች ደግሞ አነስተኛ መቀመጫ ተሰጥቷል” – የተወካዮቹ አቤቱታ

“የየእርከኑ ምክር ቤት ተወካዮች ብዛት መወሰኛ” የተሰኘው ሁለተኛው አዋጅ ደግሞ በ65 ያደገውን የክልሉን ምክር ቤት የመቀመጫ ወንበሮች ብዛት ለምርጫ ክልሎች ደልድሏል። አዋጁ መቀመጫዎቹን የደለደለው ከዚህ ቀደም ከነበሩ 23 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ሦስቱን አፍርሶ እና አምስት አዳዲስ የምርጫ ክልሎችን አዋቅሮ ነው።

ከዚህ በፊት በነበረው አዋጅ የምርጫ ክልሎች የነበራቸው ተወካይ ብዛት ከ4 እስከ 7 የነበረ ሲሆን በአዲሱ አዋጅ ምርጫ ክልሎች ከ5 እስከ 11 ተወካይ እንዲኖራቸው ተደርጓል።

ቦዴፓን የወከሉት ሦስቱ የምክር ቤት አባላት በክልሉ ሕገ መንግሥት ማሻሻያው ላይ ተሳተፉ የወረዳ ምክር ቤቶች “ሕጋዊነት” ላይ ጥያቄ በማንሳት ሂደቱን ተቃውመዋል። ወደ 165 ያደገው የተወካዮች ብዛት የተከፋፈለበት መንገድ “የሕዝብ ብዛትን ያማከለ አለመሆኑንም” ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ አንስተዋል።

“ነባር የምርጫ ክልሎች የፈረሱበት እና አዳዲስ የምርጫ ክልሎች የተቋቋሙበት ሂደት ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ” እንደሆነ ገልጸዋል። በመሆኑም ሁለቱ አዋጆች “ያልነበሩ፣ ያልተደነገጉ እንዲባሉ” እና “ተፈጻሚ እንዳይሆኑ” ጥያቄ አቅርበዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት መግለጫ ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሚያምኑት የምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሐንስ፤ በመግለጫው ላይ የተጠቀሱት ክሶችን “መሠረተ ቢስ” እና “ተቀባይነት የሌላቸው” ሲሉ ጠርተዋል።

ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ የቀረበው አቤቱታ “ሠላማዊ፣ ሕጋዊ እና ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ” እንደሆነ የገለጹት የምክር ቤት አባሉ፤ ፓርቲያቸው “የጦርነት ታሪክ የሌለው” እና “ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሠላማዊ ትግል በማድረግ” የሚታወቅ መሆኑን አስረድተዋል

“አቤቱታችንን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ያቀረብነው ሕገ መንግሥቱ፣ ሕጉ፣ አሠራሩ የሚፈቅደውን ሥርዓት ተከትለን ነው። አንድን ጉዳይ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መውሰድ ግጭት እና ጦርነት ሊቀሰቅስ የሚችለው በምን መመዘኛ ነው?” ሲሉ በምላሹ ጠይቀዋል።

አቶ ዮሐንስ አክለውም “የጠየቅነው የሕገ መንግሥት ትርጉም በሂደት ላይ ነው ያለው። እርሱን እየጠበቅን ነው። ምንም ወደ ኋላ የሚመልሰን ነገር የለም” ብለዋል።

ቢቢሲ፤ በጉዳዩ ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ እና ከሌሎች ክልሉ አመራሮች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች አልተሳኩም።