
7 መጋቢት 2025, 14:06 EAT
በኢትዮጵያ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለሚያነሷቸው የማንነት ጥያቄዎች “በሳይንሳዊ መንገድ” ምላሽ የሚሰጥ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ማንነት መገለጫ ጥናት ሊያካሄድ ነው።
ጥናቱ ለማካሄድ የሚያስችለው ስምምነት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የካቲት 19/2017 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ተፈራርመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የሚካሄደው ጥናት አምስት ዓመት እንደሚፈጅ በስምምነት ፊርማው ወቅት ተገልጿል። ሂደቱን የሚያስፈጽም የፕሮጀክት ጽህፈት ቤትም እንደሚቋቋም ተጠቁሟል።
የፌደሬሽን ምክር ቤትን ወክለው በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያሰፈሩት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር “ለሁላችንም ማጣቀሻ ሊሆን የሚችል ነገር እንደ አገር አልተሠራም” ሲሉ ተናግረረዋል።
አቶ አገኘሁ አክለውም “ይሄ ጥናት ከተጠና በኋላ እውቅና መስጠት አለበት” ሲሉ ከጥናቱ መጠናቀቅ በኋላ በተደጋጋሚ የሚነሱ የማነነት ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚያገኙ ፍንጭ ሰጥተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በዳዳም የአፈ ጉባኤውን ሃሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ለቢቢሲ ሰጥተዋል።
አቶ ተረፈ “እዚያም እዚሀም የሚነሱ ደግሞ ‘ማንነት ይታወቅልን’ የሚሉ ሳይንሱን ያልተከተሉ ጥያቄዎች አሉ። በዚህ ጥናት ሳይንሱን በተከተለ መንገድ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ይቀረፋሉ የሚል እምነት ተይዟል” ሲሉ ከጥናቱ በኋላ የሚጠበቀውን ውጤት አስረድተዋል።
የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አክለውም፤ “በዚህ ጥናት ውስጥ በትክክል ማንነት ያላቸው የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው የራሳቸው ብሔረሰብ የሚያስብል ማንነት የሚያሰጥ መስፈርት ካሟሉ እውቅና ይሰጣቸዋል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ማለት “ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው” መሆናቸውን ያትታል።
ከዚህ በተጨማሪ “የጋራ ወይም ተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸው እና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ” መሆናቸውንም ይገልጻል።
- “‘ቁርጭምጭሚት’ የሚለው ቃል ያስቀኛል” ለ23 ዓመታት ለፈረንጆች አማርኛን ያስተማረችው ፖላንዳዊት፣ ዶ/ር ኤቫ ቮልክ-ሶሬ7 መጋቢት 2025
- https://www.bbc.com/amharic/extra/diyd5gtsh3/demolished_heritages_amharic
- ኦብነግ ቀጣይ የትግል ስልቱን ለመወሰን “ሕዝባዊ ውይይት” እንደሚያደርግ አስታወቀ3 መጋቢት 2025
የጥናቱ አንዱ ባለቤት የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ለሆኑት ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ዕውቅና የመስጠት ኃላፊነት አለበት።
በምክር ቤት ዕውቅና የተሰጣቸው አሁን ብሔር ብሔረሰቦች ቁጥር 76 ነው።
አቶ ተረፈ በዳዳ “ዛሬም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ማንነታችን ይታወቅልን [የሚል] ጥያቄ የሚያቀርቡ አካላት አሉ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ የጥናቱ ፋይዳ ለማንነት ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ያለፈ መሆኑን ይገልጻሉ።
“ኢትዮጵያ እንደ አገር ልሳነ ብዙ፣ ባህለ ብዙ እና ኅብረ ብሔራዊ ናት” የሚሉት ዶ/ር ዮሐንስ፤ “በተለያዩ ፀሐሀፊዎች ዘንድ እንደሚገለጸው በምሁራኑ በሕግ አውጪው በሕገ አስፈጻሚው ጭምር የኢትጵያ ብሔሮች ስንት ናቸው የሚለውን በትክክል ማወቅ አልተቻለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአካዳሚው ዳይሬክተር አክለውም የፌዴሬሽን ምክር ቤት እውቅና የሰጣቸው 76 ብሔር ብሔረሰቦች ቢኖሩም “ከዚህ አንጻር ቋንቋዎችን ስናይ ከ80 በላይ እየተባለ ነው የሚገለጸው እንጂ ይሄን ያህል ቋንቋዎች ኢትዮጵያ አሏት፣ ብሔር ብሔረሰቦቿ ይህን ያህል ናቸው የሚል እና ብሔሩ ከቋንቋው ጋር ያለው መስተጋብር አልተጠናም” ይላሉ።
“ቁጥሩን አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ሥርጭታቸው መጠናቸው ዝምድናቸው ልዩነታቸው በአጠቃላይ ብሔር ብሔረሰቦች ደግሞ የማኅበራዊ እና የአኗኗር ዘዴያቸው አይታወቅም” ሲሉ ዶ/ር ዮሐንስ ያስረዳሉ።
አክለውም ከጥናቱ ዓላማዎች አንዱን ሲያብራሩ “የዚህ የብሔር ብሔረሰቦች የኢትኖግራፊ እና የሥነ ልሳን አትላስ ወይም ፕሮፋይል መገለጫ መዘጋጀት [ዓላማ] ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች ምን ታክላለች ብሎ ጥርት ያለ መልስ በመስጠት ገጽታዋን ማሳየት ነው” ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ “የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ባሕል፣ ማንነት፣ የማንነት መገለጫ የሆኑ የቋንቋ እና የባሕል የአኗኗር ሁኔታዎችን መግለጽ፣ መሰነድ እና ካርታ ማዘጋጀት” ሌላኛው የጥናቱ ዋና ዓላማ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ለዘመናት የሚንከራተቱ ሰዎች አሉ እንደ ቡድን። በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና ይሰጠን የሚሉ አሉ፤ አልተሰጣቸውም። በቂ የሆነ ሳይንሳዊ መልስ ስለሌለው ጥያቄያቸውም አልተመለሰላቸውም” የሚሉት ዶ/ር ዮሐንስ ጥናቱ የማንነት ጥያቄዎችን እንደሚመልስ ይገልጻሉ።
“ጥናቱ ከተዘጋጀ በኋላ በትክክል በቋንቋዎቹ እና በዘዬዎቹ መካከል ያለው ልዩነት ከታወቀ፤ በቋንቋዎቹ እና በብሔር ብሔረሰቦቹ መካከል ያለው መስተጋብር ከተለየ በየጊዜው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚቀርቡ የማንነት እውቅና ይሰጠን የሚሉ ጥያቄዎች መልስ ያገኛሉ” ሲሉም አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ጥናቱ የቋንቋዎቹ እና የባሕሎቹ መገኛ ቦታ ብቻ ሳይሆን፣ህልውናቸው ምን ላይ እንዳለ” እንደሚለይ ዶ/ር ዮሐንስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ጥናቱ ለአደጋ የተጋለጡት የትኞቹ ናቸው፣ ቶሎ የስነዳ ሥራ የሚያስፈልጋቸው ብሔር ብሔረሰቦች የትኞቹ ናቸው የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው ድንበር ተሻጋዊ ባሕሎች እና ቋንቋዎቹ እነማን ናቸው፣ ለእነሱ ምን አይነት ምላሽ ያስፈልጋል የሚለውን ለመከታተል በጣም ጠቃሚ ግብዓት ይሆናል” ሲሉም አብራርተዋል።