
ከ 5 ሰአት በፊት
በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላም ለማውረድ ከሩሲያ ይልቅ ከዩክሬን ጋር መግባባት “የበለጠ አስቸጋሪ ነው” ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የምታደርገው ግንኙነት “በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ከዩክሬን ይልቅ ከሩሲያ ጋር “ከስምምነት መድረስ ቀላል ሳይሆን አይቀርም” በማለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ነገር ግን ትራምፕ ይህንን ከማለታቸው ከሰዓታት ቀደም ብለው ከዩክሬን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በሩሲያ ላይ መጠነ ሰፊ ማዕቀቦች እና የታሪፍ ግዴታዎችን ለመጣል “እያሰቡ” መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሩሲያው መሪ ፑቲን ጦርነቱ እንዲያበቃ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ በየክሬን በኩል ተመሳሳይ ፍላጎት አለ ብለው ለመናገር እንደማይቸሉ ገልጸዋል።
ለዩክሬን የሚሰጠው ድጋፍ ለምን እንዲቋረጥ እንዳደረጉ ተጠይቀው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሰጡት ምላሽ “ዩክሬናውያን ከስምምነት ለመድረስ ፍላጎት እንዳለቸው ማወቅ እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን ይህ ፍላጎት እንዳለ የማውቀው ነገር የለም” ብለዋል።
አሜሪካ ከዩክሬን ውድ ማዕድናት ከፍተኛውን ድርሻ ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነትን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እንዲፈርሙ እና ከሩሲያ ጋር በፍጥነት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ትፈልጋለች።
ነገር ግን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት አስተማማኝ የደኅንነት ዋስትና ለአገራቸው እንዲሰጥ ከስምምነቱ ውስጥ እንዲካተት ይፈልጋሉ። ትራምፕ በበኩላቸው ዋስትናውን መስጠት “ቀላል ነገር” መሆኑን እና ከስምምነቱ በኋላ ለውይይት የሚቀርብ መሆኑን አመልክተዋል።
- የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ አለባበስ ከሌሎች መሪዎች ለምን የተለየ ሆነ?4 መጋቢት 2025
- ስለ አሜሪካ እና ዩክሬን የማዕድን ድርድር እስካሁን ምን እናውቃለን?5 መጋቢት 2025
- ምዕራባውያንን ያሳሰበው የፑቲን ምሥጢራዊ የጥቃት መሳሪያ24 የካቲት 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ እና የመረጃ ድጋፍ ማቋረጧን ተከትሎ አሁን ደግሞ ማክሳር ከሚባለው የህዋ ቴክኖሎጂ ተቋም የሚቀርቡላት ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የሳተላይት ምሥሎችን እንዳታገኝ መደረጉን ቢቢሲ አረጋግጧል።
የሳተላይት ምሥሎች በጦርነት ወቅት የተቀናቃኝ ወገን መረጃን በቀላሉ ለማግኘት የጦር ኃይሎች የሚጠቀሙበት የመረጃ ምንጮች ሲሆኑ፣ የአሜሪካ ተቋም የሆነው ማክሳር የተለያዩ ምሥሎችን ለመንግሥታት እና ለተቋማት የሚያቀርብ ነው።
ማክሳር ለቢቢሲ እንደገለጸው “የአሜሪካ መንግሥት ዩክሬናውያን የሳተላይት ምሥሎችን የሚያገኙበት አካውንት በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ አዟል” በማለት ውሳኔውን አሳውቋል።
በሚቀጥለው ሳምንት የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከዩክሬን ልዑካን ጋር ለመወያየት ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በዚህ ንግግር ውጤት ይገኛል ብለው ተስፋ እንዳላቸው አመልክተው፤ አገራቸው “በፍጥነት ሰላም እንዲወርድ ዝግጁ መሆኗን” እና ለዚህም መሳካት “ለተጨባጭ እርምጃዎች” የሚያግዙ ሃሳቦችን ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ሳምንት ውስጥ በሩሲያ ከባድ ጥቃት የተከፈተባቸው ዜሌንስኪ “በየዕለቱ አዳዲስ ጥቃቶች እና ሁኔታዎችን እየፈጠረች ያለችው ሩሲያ ለሰላም ዝግጁ መሆኗን ማሳየት ይጠበቅባታል” ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ዋሽንግተን ውስጥ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ከምክትላቸው ጋር በሕዝብ ፊት እሰጣገባ ውስጥ ገብተው የነበሩት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከአሜሪካ ጋር ያላቸው ጠንካራ ግንኙነትን ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊኮፍ ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቁት ትራምፕ ከዜሌንስኪ የተጻፈ “የይቅርታ እና የምስጋና” ደብዳቤ ደርሷቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት በአውሮፓ መሪዎች አማካኝነት የተዋቀረውን “የፈቃደኞች ስብስብን” 20 የሚሆኑ አገራት መቀላቀላቸውን የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ዩክሬን ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ የዩክሬን ባለሥልጣናት እንዳሉት አርብ ዕለት በዶኔትስክ አካባቢ አምስት ሰዎች በሩሲያ ወታደሮች ተገድለዋል።