የባርባዶስ ፕሬዝዳነት ሳንዳራ ማሶን (በስተግራ) እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞትሊ
የምስሉ መግለጫ,የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝዳንት ሴቶች ናቸው፤ ፕሬዝዳነት ሳንዳራ ማሰን (ከግራ) እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞትሊ (ከቀኝ)

ከ 6 ሰአት በፊት

ባለፈው ምዕተ ዓመት ሴቶች በአገራቸው ፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከፍተኛ መሻሻሎችን አሳይቷል።

በዓለማችን በሁሉም አገራት ለማለት በሚያስደፍር መልኩ የመምረጥ መብትን እንዲሁም የፓርላማ መቀመጫዎችን ማግኘት ችለዋል።

ይኹን አንጂ አሁንም በተለይ በከፍተኛ የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያላቸው ውክልና ዝቅተኛ እንደሆነ ይገኛል።

ነገር ግን በአንዳንድ አገራት ሴቶች በፖለቲካው ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እና ሚና እየጠነከረ ከፍተኛው ቦታ ላይ ደርሷል። ሴቶች በመሪነት፣ በከፍተኛ የውሳኔ ሰጪነት ሥልጣን እንዲሁም በሕግ አውጪ ምክር ቤቶች ውስጥ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ የሚገኙባቸው አገራት ቁጥር እየጨመረ ነው።

በአሁኑ ወቅት ባርቤዶስ፣ ቦሲኒያ እና ሄርዜጎቢና እና አይስላንድ ከሌሎች አገራት በተለየ በሥልጣን ላይ የሚገኙት ርዕሰ ብሔር (ፕሬዝዳንት) እና ርዕሰ መንግሥት (ጠቅላይ ሚኒስትር) ሁለቱም ሴቶች ናቸው።

በተጨማሪም በታንዛኒያ፣ በሜክሲኮ፣ በፔሩ እና በማርሻል ደሴቶች ደግሞ ሁለቱንም ከፍተኛ የሥልጣን ኃላፊነቶች ይዘው የሚገኙት ሴቶች ናቸው።

በፖለቲካ ውስጥ ስላሉ ሴቶች አራት እውነታዎች እነሆ።

1. የመምረጥ መብት መከበር

እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ጥቂት ሴቶች ብቻ ነበሩ የመምረጥ መብት የነበራቸው። ነገር ግን በክፍለ ዘመኑ ማብቂያ ላይ ይህ ሁኔታ ተቀይሯል።

አንዳንድ አገሮች በዚህ ምዕተ ዓመት ውስጥ በአፋጣኝ የተለያዩ ማሻሻያዎችን አድርገዋል።

ለምሳሌ ሳዑዲ አረቢያ በአውሮፓውያኑ 2015 ሴቶች በአካባቢ ምርጫ ላይ ለመምረጥ የሚችሉበትን መብት አክብራለች።

ነገር ግን አገሪቱ ብሔራዊ ምርጫ አታካሂድም።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም አገር ያሉ ሴቶች የመምረጥ ሕጋዊ መብት አላቸው።

ይኹን እንጂ በታሊባን አገዛዝ ሥር የምትገኘው አፍጋኒስታን የሴቶችን የፖለቲካ መብት ገፍፋለች።

“የአፍጋኒስታን ሴቶች የመምረጥ መብት ያገኙት ከመቶ ዓመት በፊት ቢሆንም፣ ዛሬ ግን በታሊባን አስተዳደር ከአደባባይ ሕይወት ሙሉ በሙሉ ተገልለዋል” ሲል በሴቶች እኩልነት ላይ የሚሰራው የመንግሥታቱ ድርጅት የሴቶች ተቋም አመልክቷል።

“በአሁኑ ወቅት በአፍጋኒስታን በብሔራዊም ሆነ በክልል ደረጃ አንዲትም ሴት ምንም ዓይነት ጉልህ የሆነ የፖለቲካ ሥልጣን አልያዘችም።”

በእርግጥ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ለወንዶችም ቢሆን ሁለን አቀፍ ምርጫ ብርቅ ነበር።

ነገር ግን ወንዶች በአንዳንድ አገሮች የመምረጥ መብትን እያገኙ ሲመጡ፣ ሴቶች ተገልለው ቀርተዋል።

በአውሮፓውያኑ 1893 በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሴቶች ሙሉ በሙሉ የመምረጥ መብት የሰጠችው አገር ኒው ዚላንድ ናት።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ ላይ ወንዶች በአንድ ሦስተኛ የዓለም አገራት ውስጥ የመምረጥ መብት የነበራቸው ሲሆን፣ ሴቶች ግን የመምረጥ መብት የነበራቸው አንድ ስድስተኛ በሆነው የዓለም ክፍል ውስጥ ብቻ ነበር።

ግሎባል ቼንጅ ዳታ ላብ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ባስቲያን ሄሬ “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ባሉት አሥርት ዓመታት ውስጥ ክፍተቱ በፍጥነት ጠብቧል፤ በሴቶች ላይ የሚደረገው የመምረጥ መብት አድልዎ በብዙ አገራት ሲያበቃ፣ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች በርካታ አገራት ውስጥ የመምረጥ መብት አግኝተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

በብዙ የአፍሪካ አገራት የሴቶች የመምረጥ መብት ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከቅኝ ግዛት ማብቃት በኋላ ነው።

በሌሎች አገራት ግን በአስገራሚ ሁኔታ እገዳዎች ለረዥም ጊዜ ቆይተዋል።

በአሜሪካ እስከ 1965 ድረስ ብዙ ጥቁር ሴቶች (እንዲሁም ወንዶች) ድምጽ እንዳይሰጡ ተከልክለዋል።

በስዊትዘርላንድ ደግሞ እስከ 1971 ድረስ በተደረጉ የፌደራል ምርጫዎች ሴቶች እንዲመርጡ አይፈቀድላቸውም ነበር።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ጥቁር ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲመርጡ የተፈቀደላቸው በ1993 ነው።

የመምረጥ መብት በወረቀት ላይ መኖሩ እና እነዚህን መብቶች መጠቀም መቻል የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

እንደ ወርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው መረጃ፤ “በአንዳንድ አገራት ወይም ክፍለ አህጉራት ሴቶች የመምረጥ ሕጋዊ መብት ቢኖራቸውም በሕብረተሰቡ አመለካከት፣ በምርጫ ወቅት በሚደርስባቸው ትንኮሳ እና ጥቃት ወይም በባሎቻቸው በሚደርስባቸው ጫና የተነሳ የተከለከለ ነበር።”

ግብፅ መራጮች መታወቂያቸውን እንዲያሳዩ የሚጠይቅ “የተለመደ የሚመስል” አሠራር ነበራት።

ነገር ግን ሴቶች ከወንዶች በተለየ፣ ሕጋዊ መታወቂያ የማግኘት ዕድላቸው አነስተኛ ነው።

መታወቂያ ቢኖራቸውም እንኳ ባለቤታቸው እጅ ስለሚቀመጥ፣ ድምጽ እንዲሰጡ ወይም እንዳይሰጡ የመቆጣጠር ሚና ነበራቸው።

ግብጻዊት ሴት ድምጽ ከሰጠች በኋላ ቀለም የተቀባውን ጣቷን ስታሳይ

2. ሴቶች የበላይነት የየዙባቸው ፓርላማዎች

መቀመጫውን በስዊድን ያደረገው ቫራይቲስ ኦፍ ዲሞክራሲ ፕሮጀክት (V-Dem) እንዳለው ከሆነ ሴቶች እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ከብሔራዊ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሙሉ በሙሉ የተገለሉ ነበሩ።

ፊንላንድ በ1907 ሴት የፓርላማ አባላትን የመረጠች የመጀመሪያዋ አገር ነች።

ከዚያ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ቀስ በቀስ ጨምሯል።

የእድገት መጠኑ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።

በአውረሮፓውያኑ 2008 በሩዋንዳ ፓርላማ ሴቶች አብላጫ ወንበር በማግኘት ከዓለም ቀዳሚ ለመሆን ችለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል በሩዋንዳ፣ በኩባ እና በኒካራጓ ፓርላማዎች ውስጥ ሴቶች ከ50 በመቶ በላይ መቀመጫ አላቸው።

ሌሎች ሦስት አገራት ደግሞ ሜክሲኮ፣ አንዶራ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በሕግ አውጪዎች ምክር ቤቶቻቸው ውስጥ ሴቶች እና ወንዶች እኩል ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ችለዋል።

ዊሜንስ ፓወር ኢንዴክስ (CFR) ውስጥ የምትሠራው ኖኤል ጄምስ “ከእነዚህ ቀዳሚ ስድስት አገራት አምስቱ በታችኛው ምክር ቤቶቻቸው ውስጥ የሴቶችን ከፍተኛ ተሳትፎ ለማሳደግ በሕግ የተቀመጠ ኮታ ተግብረዋል” ትላለች።

እንደ ጄምስ ገለፃ የሩዋንዳ የፆታ እኩልነት መሳካት ምሥጢር፤ በአውሮፓውያኑ 1994 ከተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ማግስት ሴቶችን አገሪቱን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለማካተት በመቻሉ ነው።

ለሴቶች የመማር ዕድልን ማስፋት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ትላለች ጄምስ።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፓርላማ 50 በመቶ ሴቶችን ያቀፈ መሆን እንደሚገባው በሕግ የተደነገገ ሲሆን፣ ግማሹ በምርጫ ግማሹ በሹመት ቦታውን ያገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት በበርካታ አገራት ምርጫ ላይ የሚሳተፉ ሴቶች ፈተናዎች እንደሚገጥሟቸው አመልክቷል።

“ጎጂ የሆኑ ደንቦች እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የሴቶችን የፖለቲካ መብት ያደናቅፋሉ።”

አክሎም የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙውን ጊዜ ሴቶችን በዕጩነት ለመምረጥ ወኔ ያጥራቸዋል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በማደግ ላይ ባሉ አገራት ሴቶች ብዙውን ጊዜ “የገንዘብ ምንጭ እና የፖለቲካ ድጋፍን” ማግኘት ስለሚቸግራቸው ከፖለቲካ ተሳትፎ ተገልለው ይቆያሉ።

በአሁኑ ጊዜ በስምንት አገራት ሴቶች በብሔራዊ ሕግ አውጭ ምክር ቤት ውስጥ ምንም ተወካይ የላቸውም።

እነዚህም አፍጋኒስታን፣ አዘርባጃን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሃንጋሪ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ ቫኑዋቱ፣ የመን እና ቱቫሉ ናቸው።

የአፍጋኒስታን ሴቶች በእስላማዊ አለባበስ
የምስሉ መግለጫ,ታሊባን ወደሥልጣን ከተመለሰ በኋላ በአፍጋኒስታን በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጫና እየበረታ ነው

3. ከ15 በመቶ አገራት ሴት መሪዎች አሏቸው

እስከ ታኅሣሥ ወር ድረስ ከ193 አገራት ውስጥ 26ቱ ብቻ የሴት ርዕሰ ብሔር ነበራቸው።

ይህ ቁጥር ከዓለም አገራት ከ15 በመቶው በታች የሚሆኑት ብቻ ሴት ርዕሳነ ብሔራት እንዳሏቸው እንደሚያመለክት የዊሜንስ ፓወር ኢንዴክስ መረጃ ያሳያል።

ከዚህ በተጨማሪም ሴቶች በመንግሥት ኃላፊነት ውስጥ ግማሽ ወይም ከዚያ በላይ የኃላፊነት ቦታ የያዙት በ15 አገራት ውስጥ ብቻ መሆኑን አስቀምጧል።

4. ከ1946 ጀምሮ 80 ሴት ርዕሳነ ብሔራት

ዊሜንስ ፓወር ኢንዴክስ ከአውሮፓውያኑ 1946 ጀምሮ 80 አገራት (በግምት 40 በመቶ የሚሆኑት) ሴት ርዕሳነ ብሔራት እንደነበሯቸው ይናገራል።

የሲሪ ላንካው ሲሪማቮ ባንዳራናይኬ በ1960 በዓለም የመጀመሪያዋ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር እስኪሆኑ ድረስ ከዚያ በፊት የነበሩት ሥልጣናቸውን ያገኙት በውርስ ነበር።

“ከዚያ ወዲህ ብዙ አገራት ሴት ርዕሳነ ብሔራት ነበሯቸው፤ ይህ አዝማሚያ በአብዛኛው በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚመራ ነው” ሲሉ ሄሬ ተናግረዋል።

ነገር ግን አሁንም በከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎች ላይ የወንዶች ቁጥር ከሴቶች በእጅጉ ይበልጣል።

ሄሬ አክለውም “ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ፣ የፖለቲካ ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች አሁንም ወንዶች ናቸው” ይላሉ።

የሴቶች ውክልና ለምን ግድ ይላል?

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ብዙ ሴቶች የፖለቲካ ሥልጣን መያዛቸው አዎንታዊ ለውጦችን ያመጣል።

በአውሮፓውያኑ 2021 የኮሎራዶ ቦልደር ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው ሴቶች በብሔራዊ ሕግ አውጪዎች ውስጥ የበለጠ ተጽዕኖ ሲኖራቸው፣ አገራት በትምህርት እና በጤና ላይ የበለጠ መዋዕለ ነዋይ ያፈስሳሉ።

በተመሳሳይ በ2020 የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ካሉ ሕግ አውጪዎች ውስጥ የሴቶች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ፣ የጤና አጠባበቅ ወጪ መሻሻል እንዲሁም የጨቅላ ሕጻናት እና የታዳጊዎች ሞት መቀነስ አሳይቷል።

በ2019፣ በአውስትራሊያ የኩርቲን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ብዙ ሴቶች ያሏቸው ፓርላማዎች ጠንካራ የአየር ንብረት ፖሊሲዎችን እንደሚያወጡ አስተውለዋል።

ሆኖም የዊሜንስ ፓወር ኢንዴክስ ባልደረባዋ ጄምስ ሴቶችን መምረጥ ብቻ ለእነዚህ ውጤቶች ዋስትና እንደማይሰጥ ታስጠነቅቃለች።

ሴቶች አንድ ዓይነት አለመሆናቸውን በመግለጽ፤ ሁሉም የፆታ እኩልነትን፣ ሰላምን ወይም ትብብርን አያበረታቱም በማለት ትናገራለች።