
ከ 3 ሰአት በፊት
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ “የነጮችን መሬት እየወረሰች ነው” የሚለውን ክሳቸውን በድጋሚ ካሰሙ በኋላ አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር “ጠቃሚ ባልሆነ የውዝግብ ዲፕሎማሲ” ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ አስታወቀች።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ለደኅንነታቸው በመስጋት ከደቡብ አፍሪካ ለቀው መውጣት ለሚፈልጉ” ነጭ አርሶ አደሮች ወደ አሜሪካ መጥተው እንዲኖሩ እንዲሁም ዜግነት በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚፈቅዱ ጥሪ አቅርበዋል።
ደቡብ አፍሪካ ቀደም ሲል ትራምፕ አዲሱን የአገሪቱን የመሬት ሕግ በአግባቡ አልተረዱትም ስትል አቋሟን ገልጻ የነበረ ቢሆንም፣ አሜሪካ አዲሱን ሕግ በመቃወም ለአገሪቱ ትሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ አቋርጣለች።
ፕሬዝዳንቱ በድጋሚ የሰነዘሩትን አስተያየት ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በሰጠው ምላሽ፣ አገሪቱ አሁንም ከትራምፕ አስተዳደር ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን ያለው የንግድ፣ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጿል።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ ጨምረውም በሁለቱ አገራት መካከል የሚኖረው ግንኙነት በጋራ መከባበር ላይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ባለፈው ጥር ወር የጸደቀው አዲሱ የደቡብ አፍሪካ የመሬት ሕግ በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ ካሳ ሳይከፈል መሬት እንዲወረስ የሚፈቅድ ነው።
- በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የነበሩባቸው ጀልባዎች ተገልብጠው 180ዎቹ ደብዛቸው ጠፋከ 6 ሰአት በፊት
- ከቤት ሠራተኝነት እስከ ሆቴል ባለቤትነት – የአዲሲኒያ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትከ 5 ሰአት በፊት
- በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ሄሊኮፕተር ላይ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉከ 4 ሰአት በፊት
ደቡብ አፍሪካ ከአሜሪካ የምታገኘውን እርዳታ ባስቆመው ትራምፕ ባለፈው ወር በፈረሙት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ላይ፣ የደች እና የፈረንሳይ ሰፋሪዎች ወራሾች የሆኑት ነጭ አፍሪካነር ደቡብ አፍሪካውያን ላይ መድልዎ ይፈጸማል ሲሉ ከሰዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጨምረውም የጥቂት ነጮቹ መሬት ካሳ ሳያገኙ እየተወረሰ ነው በማለት የከሰሱ ሲሆን፣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ግን ይህንን ያስተባብላል።
በተጨማሪም ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱበት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ ስደተኞችን ለማባረር እና ወደ አገራቸው እንዳይገቡ እንደሚያደርጉ እየተናገሩ ቢሆንም፣ ለነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ገበሬዎች ግን ጥገኝነት ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
አርብ ዕለት ፕሬዝዳንቱ እንደተናገሩት አፍሪካነር ገበሬዎች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም የደቡብ አፍሪካ ገበሬ ወደ አሜሪካ በመምጣት መኖር እንደሚችል አሳውቀዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ገበሬዎች ጉዳይ በአሜሪካ የቀኝ ዘመም እና የአክራሪ ቀኝ ዘመም ፖለቲካ ውስጥ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ጉዳይ ሆኖ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል።
አብዛኞቹ የግል የእርሻ መሬቶች በነጭ ገበሬዎች እጅ በሚገኝባት ደቡብ አፍሪካ ዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት ካበቃ ከ30 ዓመታት በኋላ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ በአገሪቱ አሁንም አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል።
መንግሥት በዘር መድልዖ ሥርዓት የተፈጸሙ ኢፍትሃዊነቶችን እና የመሬት ይዞታን መፍትሄ እንዲሰጥ ለረጅም ጊዜ ግፊት ሲደረግበት ቆይቷል።
በቅርቡ የጸደቀው አዲሱ የመሬት ሕግ “ፍትሃዊ፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ለሕዝብ ጥቅም” አስፈላጊ ሲሆን ብቻ መሬት ያለ ካሳ እንዲወረስ ይፈቅዳል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደስተኛ ያልሆኑት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ለደቡብ አፍሪካ የምትሰጠው ድጋፍን ያቋረጡ ሲሆን፣ በተጨማሪም አሜሪካ በአገሪቱ ለሚካሄዱ የኤችአይቪ መረሃ ግብሮች የምትሰጠው የገንዘብ ድጋፏን ባለፈው ሳምንት አቋርጣለች።