
ከ 3 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍልስጤም የድጋፍ ሰልፍ ጋር ተያይዞ የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ከፌደራሉ መንግሥት የሚያገኘውን የ400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማቋረጣቸውን አስታወቁ።
የትራምፕ አስተዳደር እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ዩኒቨርስቲው በግቢው ውስጥ ፀረ-ሴማዊነትን መግታት አልቻለም በሚል ነው።
አራት የፌደራል መንግሥት ኤጀንሲዎች በበኩላቸው የገንዘብ ድጋፉ የተቋረጠው ዩኒቨርስቲው “በአይሁድ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ተደጋጋሚ ትንኮሳ ለማስቆም እርምጃ” ባለመውሰዱ እንደሆነ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።
በኒው ዮርክ የሚገኘው የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ በጋዛ በሚካሄደው ጦርነት አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ በመቃወም ለፍልስጤም የሚደረጉ ድጋፎች ከተቀጣጠሉባቸው አንዱ ነው።
ትራምፕ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ “ሕገወጥ” ሲሉ የጠሯቸው ተቃውሞዎችን ለሚፈቅዱ ዩኒቨርስቲዎች የሚሰጥን የገንዘብ ድጋፍ አቋርጣለሁ ሲሉ አስፈራርተው ነበር።
የትምህርት ሚኒስቴር ፀሐፊ ሊንዳን ማክ ማሆን በዩኒቨርስቲው ውስጥ ያሉ አይሁድ ተማሪዎች “በግቢው ውስጥ የማያቋርጡ ትንኮሳዎች፣ ጥቃቶች፣ ማስፈራራት እና ፀረ ሴማዊ ትንኮሳዎች ሲደርሱባቸው የዩኒቨርስቲው ባለሥልጣናት ችላ ብለዋል” ሲሉ ወቅሰዋል።
“ዛሬ፣ ለኮሎምቢያ እና ለሌሎች ዩኒቨርስቲዎች እንዲህ ዓይነት አስጸያፊ ተግባራቸውን ከአሁን በኋላ እንደማንታገስ አሳይተናል” ብለዋል።
ኮሎምቢያ በአሜሪካ ውስጥ ስመ ጥር ዪኒቨርስቲዎች አንዱ ሲሆን፣ ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች አሉት።
ኮሎምቢያን ጨምሮ በመላው አሜሪካ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች የፍልስጤም ድጋፎች እየተቀጣጠሉ እና በግቢዎቻቸው ውስጥ ድንኳኖች ተክለው እያደሩ ሌት ተቀን የሚቃወሙ ተማሪዎች ታይተዋል።
የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደውን የዘር ጭፍጨፋ በጦር መሳሪያ እና በሌሎች ነገሮች እያገዙ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክናቸውን ዩኒቨርስቲዎች እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው የሚለውን አትቀበለውም።
- በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የነበሩባቸው ጀልባዎች ተገልብጠው 180ዎቹ ደብዛቸው ጠፋከ 6 ሰአት በፊት
- ከቤት ሠራተኝነት እስከ ሆቴል ባለቤትነት – የአዲሲኒያ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትከ 6 ሰአት በፊት
- በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ሄሊኮፕተር ላይ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉከ 5 ሰአት በፊት
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ካትሪና አርምስትሮንግ “ለዩኒቨርስቲያችን ከፍተኛ ስጋት የተጋረጠበት ወቅት” በማለት አርብ ዕለት ለካምፓሱ ተማሪዎች እና ሠራተኞች ኢሚይል መላካቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ አስነብቧል።
አክለውም “የዚህ ፈንድ መቋረጥ በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በሠራተኞች፣ በምርምር እና በዩኒቨርስቲው ሌሎች ወሳኝ ተግባራት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል።
ባለፈው የበጀት ዓመት ዩኒቨርስቲው 1.3 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ዓመታዊ የሥራ ማስኬጃ ገቢውን ከፌደራል መንግሥት ማግኘቱን ኮሎምቢያ ደይሊ ስፔክታተር የተሰኘው የተማሪዎች ጋዜጣ ዘግቧል።
የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የፌደራል እገዛ መቋረጥን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው ኒው ዮርክ ሲቪል ሊበርቲስ ኅብረት ዳይሬክተር ሕገወጥ እርምጃ ሲሉ ተችተውታል።
“ይህ ኮሌጆችን እና ዩኒቨርስቲዎች በአስተዳደሩ ተቀባይነት የሌላቸው እስራኤልን መተቸት፣ የፍልስጤም መብቶችን መደገፍ የመሳሰሉ የተማሪዎችን ንግግሮች እና ቅስቀሳዎችን ሳንሱር እንዲያደርጉ ለማስገደድ የሚደረግ ነው” ብለውታል።
ባለፈው ሚያዝያ የፍልስጤም ደጋፊዎች በእስራኤል ጦር ለተገደለችው የአምስት ዓመቷ ሕጻን ሂንድ ራጃብ መታሰቢያ በሚል የዩኒቨርስቲውን ሃሚልተን አዳራሽ በመቆጣጠር ሂንዲ ሲሉ ሰይመውት ነበር።
እነዚህ ተቃውሞዎች የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ሚኑቼ ሻፊክ ከሥልጣን እንዲለቁም ምክንያት ሆኗል።
ከጋዛ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ሰልፎችን መቆጣጠር ባለመቻላቸው ሦስት ፕሬዚዳንቶች ከስመ ጥር ዩኒቨርስቲዎች ኃላፊነት ለቀዋል።
የአይሁድ ተማሪዎች ቡድን አባል ተማሪ ኮሎምቢያን ለመቅጣት የተወሰደውን እርምጃ በደስታ እንደሚቀበል ለአሶሺየትድ ፕሬስ ተናግሯል።
“የኮሎምቢያ አስተዳደር ፀረ ሴማዊነትን፣ የአይሁድ ተማሪዎችን እና መምህራንን ትንኮሳ በቁም ነገር እንዲወስዱ የማንቂያ ደወል ነው” ሲል ተማሪው ተናግሯል።
ሐማስ ባለፈው ዓመት መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት ከ48 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።