ባሕር ዳርቻ ላይ የተጣሉ ጀልባዎች
የምስሉ መግለጫ,በጀልባዎቹ በደረሰው አደጋ ከ180 በላይ የሚሆኑት ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተሰግቷል

ከ 6 ሰአት በፊት

ከጂቡቲ የተነሱ ስደተኞችን ያሳፈሩ ጀልባዎች ከየመን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ተገልብጠው የደረሱበት ያልታወቀ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባቸው ከ180 በላይ ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀረ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ።

አደጋው የደረሰባቸው ጀልባዎች ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ተነስተው የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም የባሕረ ሰላጤው አገራት በሕገወጥ እና በአደገኛ መንገድ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን ያሳፈሩ ነበሩ።

በጀልባዎቹ ላይ ተሳፍረው የነበሩት እና ደብዛቸው የጠፈው ስደተኞች የየትኞቹ አገራት ዜጎች እንደሆኑ ድርጅቱ የገለጸው ነገር ባይኖርም፤ አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ግን አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ዘግቧል።

ከየመን የባሕር ዳርቻ ከመድረሳቸው በፊት ከተገለበጡት ጀልባዎች መካከል አንዷ 31 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እና ሦስት የመናውያን የጀልባው ሠራተኞችን አሳፍራ እንደነበር ኤፒ ጨምሮ አመልክቷል።

በዚህ አደገኛ ባሕር በኩል በተደጋጋሚ ለመሻገር የሚሞክሩት እና ቀደም ሲል በደረሱ አደጋዎች ሰለባ ከሆኑት መካከል በአብዛኞቹ ኢትዮጵያውን እና ሶማሊያውያን መሆናቸው ይታወቃል።

የአይኦኤም ቃል አቀባይ ታሚም ኤላይን ለኤፒ እንደረናገሩት ሐሙስ ዕለት የመን ባሕር ዳርቻ ከመድረሳቸው በፊት ከተገለበጡት ጀልባዎች ከተረፉት ሁለት ሰዎች ውጪ 181 ስደተኞች እና አምስት የመናውያን የጀልባዎቹ ሠራተኞች የደረሱበት አልታወቅም።

የዜና ወኪሉ ጨምሮም በተመሳሳይ ጊዜ ሌሎች ሁለት ጀልባዎች ከጂቡቲ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ተገልብጠው ሁለት ሰዎች ሲሞቱ ሌሎቹ ግን በነፍስ አድን ሠራተኞች በሕይወት መትረፋቸውን ዘግቧል።

በጀልባዎቹ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት መካከል ቢያንስ 124ቱ ወንዶች እንዲሁም 57 ሴቶች መሆናቸው ተነግሯል።

አደጋው ከደረሰባቸው ጀልባዎች ሁለት የመናውያን የጀልባ ሠራተኞች በሕይወት ሲተርፉ፣ ቀሪዎቹ ሰዎች እና የጀልባዎቹ ሠራተኞች ሳይሞቱ አይቀርም የሚል ስጋት አለ።

ነገር ግን እስካሁን በአደጋው ሕይወታቸው ሳያልፍ አይቀርም ከተባሉት ሰዎች መካከል አንድም አስከሬን አልተገኘም።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

አይኦኤም አደጋውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የሰዎች አዘዋዋሪዎች የየመን ባለሥልጣናት ወቅቱ ከባድ ንፋስ እና ከፍተኛ ማዕበል የሚከሰትበት በመሆኑ በጀልባ ባሕሩን ማቋረጥ አደገኛ መሆኑን የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለው በመጓዛቸው አደጋው ደርሷል።

ከጂቡቲ ተነስተው በአደገኛ የጀልባ ጉዞ የመን ወደሚገኘው የአይኦኤም ማዕከል መድረስ የቻሉ ስደተኞች እንዳመለከቱት፤ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የአየሩ ሁኔታ አደገኛ እንደሆነ እያወቁ የባሕር ላይ ተቆጣጣሪዎችን ለማምለጥ ሲሉ በግድየለሽነት ጀልባዎች ባሕሩን እንዲያቋርጡ ያደርጋሉ።

“ግልጽ የአየር ሁኔታ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም አዘዋዋሪዎች በሰው ሕይወት ላይ ቁማር እየተጫዋቱ ነው። የስደተኞችን ሕይወት ለመታደግ አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ ተጨማሪ የሰው ሕይወት መጥፋቱ ይቀጥላል” ሲሉ በየመን የአይኦኤም ኃላፊ አብዱሳተር ኢሶኤቭ ተናግረዋል።

በአካባቢው ከዚህ ቀደም በደረሱት አደጋዎች በርካታ ኢትዮጵያውን እና ሶማሊያውን መሞታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ሐሙስ ዕለት በደረሰው አደጋ ደብዛቸው የጠፋው ስደተኞች አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ ወይም ከሶማሊያ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

ኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት እንዲሁም ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናት በተለያዩ መስኮች ላይ ተሰማርተው የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ሕይወት መቀየርን ዓላማ አድርገው አደገኛውን ባሕር ለማቋረጥ ይሞክራሉ።

ነገር ግን ጥቂት የማይባሉት ከመነሻው በአደገኛው ባሕር ጉዞ ላይ በሚገጥማቸው አደጋ ለሞት እና ለጉዳት የሚዳረጉ ሲሆን፣ ተሳክቶላቸው ባሕሩን የተሻገሩት ደግሞ በሚያቋርጧቸው አገራት ውስጥ ለእስር፣ ለጥቃት፣ ለግዳጅ የጉልበት ሥራ እና ሌሎች ዓይነት ብዝበዛዎች ይዳረጋሉ።

በተጨማሪም በርካቶች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እና በታጣቂ ቡድኖች አማካኝነት ለእገታ እና በግዳጅ ገንዘብ እንዲከፍሉ ይደረጋሉ።

በባሕር እና በየብስ ላይ ሞት እና ስቃይ በተደጋጋሚ በሚያጋጥምበት በዚህ የፍልሰት መስመር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚገዕዙ ሲሆን፣ አይኦኤም እንደሚለው ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ከ60 ሺህ በላይ ስደተኞች የመን ደርሰዋል።

እንዲሁም 580 ሴቶች እና 100 ሕጻናትን ጨምሮ ከ3,400 በላይ ሰዎች ሞተዋል ወይም የደረሱበት አልታወቀም።