
ከ 6 ሰአት በፊት
አዲስ ገብረማርያም የልጅነት ሕይወቷ፣ እጅግ ከባድ እና ውስብስብ ነበር። በኢኮኖሚ ችግር፣ በስደት እና በጦርነት ምክንያት በፈተና የተሞላ ሕይወት ማሳለፏን ታስታውሳለች።
ቤተሰቦቿ መሠረታዊ ነገሮች ለሟሟላት ይቸገሩ ነበር።
የበኩር ልጅ በመሆኗ ደግሞ ሁሉም ዓይነት ኃላፊነቶች ጫንቃዋ ላይ የወደቀው በእርሷ ላይ ነው።
“እንደ ታላቅ እህት፣ ቤተሰቤን የመጠበቅ ኃላፊነት በልጅነቴ ለመሸከም ወሰንኩ። ነገር ግን እጄ ላይ ምንም ነገር አልነበረም” ትላለች።
በ1957 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ማይበራዝዮ ተብሎ በሚጠራው የአክሱም ገጠራማ አካባቢ ነው ተወልዳ ያደገችው።
አባቷ አቶ ገብረማርያም በአክሱም እና አካባቢው የጨው ነጋዴ ነበሩ፤ ኑሯቸውን ለመደገፍ ሁለት ልጆቻቸውን እና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ ምዕራብ ትግራይ ሁመራ ከተማ በመሄድ በእርሻ ሥራ ላይ ተሰማሩ።
ሆኖም በወቅቱ በደርግ እና በህወሓት መካከል ጦርነት ስለነበረ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ሱዳን ተሰደዱ።
በዚህ ምክንያት አዲስ ትምህርቷን አቋርጠች። የስደት ሕይወት እጅግ ከባድ ሆነ። ታናሽ ወንድሟም ጤንነት አጣ።
“ሱዳን ውስጥ በጣም ዝቅተኛ የሚባለውን ሥራ ሳይቀር፤ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቻለሁ። ያገኘሁትን ሁሉ ነበር የምሠራው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
አዲስ ቤተሰቦቿን ለመርዳት ካላት ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ፣ ከትናንሽ የንግድ ሥራዎች ባሻገር የቤት ሠራተኛ በመሆን ጭምር በመሥራት ጥረት አድርጋለች።
“እናቴ በአስተሳሰቧ ብልህ ነች፤ ችግር ውስጥ መሆናችንን ስትመለከት እንጀራ መሸጥ ጀመረች። የምትጋግረውን እንጀራ ለመሸጥ፣ ሱዳን ውስጥ ፉል ዋጋው ረከስ ስለሚል እኛን ‘ፉል’ ብሉ ትለን ነበር።”
በሱዳን ውስጥ ያሳለፈቻቸው ከባድ ቀናት ድህነትን በማሸነፍ፣ ለማደግ እና ለመለወጥ ጽኑ ፍላጎት እንዲያድርባት ምክንያት እንደሆናት ትናገራለች።
በዚህ ተነሳሽነት ወደ ተሻለ ቦታ ለመድረስ ከቤተሰቧ ጋር በመሆን ታገለች። ቤተሰቧን ስለመርዳት ስታስብ ግን ራሷን አልረሳችም።
በዚያን ጊዜ የ18 ዓመት ወጣት የነበረችው አዲስ “በወቅቱ የማልመው የተሻለ ቦታ መድረስ ብቻ ነበር” ትላለች።
“ሥራ ሳልመርጥ መሥራት ለእኔ ብርታት ነው የሆነኝ። ዝቅተኛ ሥራ በመሥራት ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚቻል አስተምሮኛል።”
- ሴቶች ከወንዶች ያላነሰ አቅም እንዳላቸው የሚያወሳው “ማክዳ” የሙዚቃ አልበም7 ሀምሌ 2024
- ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ ክብረ ወሰን በሰበረ ዋጋ ለቼልሲ ፈረመች27 ጥር 2025
- ከጀበና ቡና እስከ በርካታ ቅርንጫፎችን ማስተዳደር – የወርቃ ቡናዋ ቻቺ ተፈራ5 መስከረም 2024

ፈተና፣ ጥረት እና ስኬት
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
አዲስ ከ45 ዓመታት በፊት ‘በእኔ የትውልድ ዘመን’ በተለይ ለሴቶች ሁኔታዎች እጅግ አዳጋች እና ፈታኝ ነው የነበሩት ትላለች።
በወቅቱ ወጣት መሆኗ እንዲሁም ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው ጥረት የገንዘብ አቅም ባላቸው ወንዶች ዓይን ውስጥ እንድትገባ አደረጋት።
በመሆኑም፣ እሷ ሕይወትን ለማሸነፍ ስትሮጥ፣ ከፊቷ ብዙ መሰናክሎች ያጋጥሟት እንደነበረ ታስታውሳለች።
“ያኔ ሴት ልጅ በኢኮኖሚ ራሴን እችላለሁ፤ ሀብታም እሆናለሁ፤ ብላ ማሰቧ ያልተለመደ ነገር ተደርጎ ይቆጠር ነበር” ትላለች።
ከዚህ ይልቅ ብዙዎች አንዲት ሴት የባሏ ጥገኛ፣ ልጅ ለመውለድ ወይም የወንድን የፆታ ፍላጎት ለማርካት እንደተፈጠረች አድርገው ይመለከቱ ነበር የምትለው አዲስ ግን ትኩረቷ ሁሉ ዓላማዋ ላይ እንደነበር ትጠቅሳለች።
“ይሄንን ሁሉ ሰበርኩት፤ እማገባም ከሆነ መርጬ እንጂ እናንተ ስላላችሁ አይደለም አልኩ፤ አሁን ግን እሠራለሁ ብዬ ሥራዬን አስቀደምኩ።”
በተጨማሪም፣ “ይሄን አመለካከት ኢኮኖሚያዊ አቅም በመገንባት፣ ስኬታማ በመሆን፣ የምፈልገው ደረጃ ላይ በመድረስ ነበር መታገል የምፈልገው። የሴት ልጅ ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ማረጋገጥ ከብዙ ነገር ነው የሚያድነው። እረፍት ይሰጣታል፤ ህልሟን እንድትኖር ይረዳታል። ሰው መሆን ማለት ደግሞ እንደምንፈልገው መኖር ማለት ነው” ትላለች።
ደርግ ወድቆ ጦርነቱ ሲያበቃ እሷ እና አባቷ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ እናቷ ደግሞ ሌሎች ሦስት ሱዳን የተወለዱ ወንድሞቿን ይዘው ወደ አሜሪካ አቀኑ።
ከሱዳን ከተመለሰች በኋላ ንግድ ውስጥ የገባችው አዲስ፣ በኢትዮጵያ ትልቁ የበርበሬ ምርት ወደ ሚገኝበት ሀላባ እየተመላለሰች በርበሬ እና ሌሎች እቃዎች መነገድ ጀመረች።
እዚም ቢሆን ግን ከፈተና አላመለጠችም።
“ብዙ መሰናክሎች ገጠሙኝ፤ ነገር ግን የተሻልኩ እሆናለሁ። ጎበዝ ነኝ፤ ወንዶች የሚሠሩትንም ሆነ ጠንካራ ሴቶች የሠሩትን ሁሉ መሥራት እችላለሁ የሚል እምነት ስለነበረኝ ብዙ ቢዝነሶች ነው የሞከርኩት” ሴቶች የኢኮኖሚ ነጻነት እንዲኖራቸው እንዲጥሩ ትመክራለች።
“ጥገኛ መሆን አይጠበቅባቸውም፤ ነጻ ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸውንም መርዳት ይችላሉ። ነገር ግን አንዲት ሴት ጥገኛ ከሆነች ጫናው ከባድ ነው።”
ከእራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ
አዲስ ካሳለፈቻቸው በርካታ የውጣ ውረድ ዓመታት በኋላ አዲሲኒያ ቢዝነስ ግሩፕን በመመሥረት ውጤታማ ለመሆን በቃች።
ኩባንያው በተለያዩ ቢዝነሶች የተሰማራ ሲሆን፣ በተለየ መልኩ በሆቴል እና ቨቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ይንቀሳቀሳል።
ኩባንያው 110 ለሚጠጉ ሠራተኞች የሥራ ዕድልን ፈጥሯል፤ እርሷ እንደምትለው አብዛኞቹ ሠራተኞቿ ሴቶች ናቸው።
“ሥራ ለእኔ ገንዘብ ማግኘት ብቻ አይደለም፤ ሕይወቴ ነው። ካለ ሥራ መኖር አልችልም ማለት ነው፤ መኖር የምፈልግ ከሆነ መሥራት ነው ያለብኝ” የምትለው አዲስ “እረፍቴም ሥራዬ ነው፤ ሥራ ላይ ነው እረፍት የማገኘው።” ብላለች።
ይህ ከባለቤቷ ጋር በመተጋገዝ ያጸናችው ቢዝነስ 14 ዓመታትን አስቆጥሯል።

በአሁኑ ወቅት በመቀለ እና በአክሱም ከተሞች ትላልቅ የሆቴል ፕሮጀክቶችን እየሠራች ትገኛለች።
አዲስ የመረጠችው የሕይወት መንገድ፣ ድህነትን አሸንፋ ለታናናሽ ወንድሞቿ እና እህቶቿ የተሻለ ዕድል መፍጠር ነበር።
ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ በንግድ ለመሰማራት ስትወስን ወንድሞቿ ለተሻለ የትምህርት ዕድል ወደ አሜሪካ እንዲሄዱ ስትገፋፋቸው ተምረው የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ በማሰብ ነበር።
“በተለይ ታናሽ እህቴ በትምህርት፣ በሁሉም ነገር የተሳካላት ሆናልኛለች። በጣም ደስተኛ ነኝ” የምትለው አዲስ ገብረማርያም፤ ማንኛዋም ሴት ፍላጎቷን አጥብቃ ከያዘች ለስኬት እንደምትበቃ ታምናለች።
“በኢኮኖሚ ዝቅተኛ መሆን የለብኝም፤ ሀብታም መሆን አለብኝ ብዬ አስብ ነበር። እግዚአብሔር ይመስገን በአቅሜ ጥሩ እየሠራሁ ነው። አሁን ብዙ የቀረኝ ነገር የለም” በማለት አሁንም በሥራዋ ወደ በለጠ ደረጃ እንደምትሸጋገር ታምናለች።
አዎንታዊ አመለካከት እና ጥረት
አዲስ ለአዎንታዊ አመለካከቷ፣ መንፈሳዊ ጥንካሬዋ እና ጤናዋ ትልቅ ቦታ ትሰጣለች።
“አብዛኛው ነገር የአስተሳሰብ ውጤት ነው፤ ሀብት ደግሞ አስተሳሰብ ነው” የምትለው አዲስ፣ “ሰው የሚድነው እና የሚሞተው በአስተሳሰቡ ውስጥ ነው። እኔ ምንም ነገር ሳይኖረኝ ነው ትልቅ ቦታ መድረስ እንደምችል ያመንኩት” በማለት ሥራዋን ስላሳደገችበት ምሥጢር ትናገራለች።
ያሳለፈችው ውጣ ውረድ እና ኢኮኖሚ ችግር አዎንታዊ የሆነ አስተሳሰብ እንድታዳብር እንደረዳት፤ ይህም ከእናቷ የወረሰችው ጥንካሬዋ መሆኑን ታምናለች።
“በሥራ ዓለም ውስጥ ብዙ ጥሩ ሰዎች፣ አማካሪዎች፣ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ጋር ነው የምንገናኘው። በየዕለቱ እንማራለን፣ እናድጋለን” በማለት ጥረት እና ጥሩ ሥራ የስኬት ቁልፍ ነው ትላለች ባለትዳር እና የሦስት ልጆች እናት የሆነችው የ60 ዓመቷ አዲስ ገብረማርያም።