ሄሊኮፕተር

ከ 5 ሰአት በፊት

ደቡብ ሱዳን ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሄሊኮፕተር ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሱዳን ጦር ጄኔራልን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ድርጅቱ አስታወቀ።

ሄሊኮፕተሯ በቅርቡ ግጭት በተፋፈመበት የላይኛው ናይል ተፋሰስ ግዛት የአገሪቱን ጦር አባላት ልታስወጣ በምትሞክርበት ወቅት እንደተኮሰባት ተገልጿል።

በጥቃቱም አንድ የሄሊኮፕተሯ ሠራተኛ፣ ቆስለው የነበሩ ጄኔራል እና በርካታ የደቡብ ሱዳን ወታደሮች መገደላቸውን በደቡብ ሱዳን የመንግሥታቱ ድርጅት ተልዕኮ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ወታደሮቹን ውጊያ ከተፋፋመበት የላይኛው ናይል ተፋሰስ ግዛት ለማስወጣት በሚሞከርበት ወቅት የተፈጸመው ጥቃት በጦር ወንጀልነት ሊፈረጅ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።

ከጥቃቱ በኋላ ሌላ ሁለተኛ ሄሊኮፕተር ቢነሳም ተጋጭቶ እንዲያርፍ በመደረጉ ተሳፋሪዎች በሙሉ መሞታቸውን የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ በበኩሉ ሁለቱም ሄሊኮፕተሮች በሰላም ማላካል በሚባል ስፍራ ማረፋቸውን ገልጿል።

በዚህ ጥቃት 27 የደቡብ ሱዳን ወታደሮች መገደላቸውን የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ማይክር ማኩዪን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል።

በላይኛው የናይል ተፋሰስ ግዛት ለሳምንታት የዘለቀው ጦርነት በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ሬይክ ማቻር መካከል ከአምስት ዓመታት በፊት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ስጋት ላይ ጥሎታል።

በአውሮፓውያኑ 2011 ከሱዳን የተገነጠለችው ደቡብ ሱዳን የዓለማችን አዲሲቷ አገር ናት።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ነጻነቷን ከተቀዳጀች ከሁለት ዓመት በኋላ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ሙሉ ካቢኔያቸውን በማባረር እንዲሁም ምክትላቸውን ማቻርን ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት አነሳስተዋል ሲሉ ወነጀሉ።

በዚህም የተነሳ አገሪቱ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገባች።

400 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን ካጡ እንዲሁም 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ ከአምስት ዓመታት በኋላ፣ በአውሮፓውያኑ 2018 የሰላም ስምምነት ላይ ተደረሰ።

ሆኖም እስካሁን ድረስ የሰላም ስምምነቱ በጸና መሠረት ላይ አልቆመም።

በአሁኑ ወቅት በላይኛው የናይል ተፋሰስ ግዛት እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአገሪቱ ጦር እና በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት ከማቻር ጋር በአጋርነት ተሰልፎ በነበረው ዋይት አርሚ በተሰኘው ሚሊሻ መካከል ነው።

ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ጋር በተደረሰ ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት የቆሰሉ ወታደሮችን ከግጭቱ ቀጣና እያስወጣ ይገኛል።

በተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ሠራተኞች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ኃላፊው ኒኮላስ ሃይሶም “እጅግ አጸያፊ እና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንደ ጦር ወንጀል የሚቆጠር ነው። በባልደረባችን ላይ በደረሰው አሰቃቂ ሞት ከልባችን አዝነን ለወዳጅ ዘመዶቹም መጽናናትን እንመኛለን” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ኪር በጥቃቱ የተገደሉት በላይኛው ናይል ተፋሰስ ናስር የሰፈረውን ጦር ሲመሩ የነበሩት ጄኔራል ማጁር ዳክ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በቅርቡ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በርካቶች ደቡብ ሱዳን ሰፋ ወዳለ የእርስ በርስ ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚሉ ስጋቶችን እያነሱ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ኅብረት በዚህ አካባቢ የተነሳው ግጭት ሊዛመት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በቅርቡ የደቡብ ሱዳን ዋነኛ ተቃዋሚ የሆነው የሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ (ኤስፒኤልኤም-አይኦ) ወታደራዊ ክንፍ የጦር አዛዥ እንዲሁም የነዳጅ ሚኒስትሩን ጨምሮ የማቻር አጋር የሆኑ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ለእስር ተዳርገዋል።

ሆኖም ከአርቡ ጥቃት በኋላ ፕሬዚዳንት ኪር ሕዝቡ “እንዲረጋጋ” ጥሪ አድርገዋል።

“አገራችን ወደ ጦርነት እንደማትመለስ ደጋግሜ ተናግሬአለሁ። ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም ። እኔ የምመራው መንግሥት ይህንን ቀውስ ይፈታዋል” ብለዋል።