በአዲስ አበባ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ተሰጥቶ የነበረው ቦታ

ዜና ለጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ተሰጥቶ የነበረው ቦታ ለኦሮሚያ ባህል ማዕከል…

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: March 9, 2025

በአዲስ አበባ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ከአንድ ዓመት በፊት ተሰጥቶ የነበረው 12 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ፣ ለኦሮሚያ ባህል ማዕከል ማስፋፊያ ፕሮጀክት እንዲውል መተላለፉ ታወቀ።

በክፍለ ከተማው ወረዳ 10 ቀበሌ 01 በተለምዶ መሿለኪያ ተብሎ የሚጠራው 92 መኖሪያ ቤቶች የሚገኙበት የመኖሪያ አካባቢ በኅዳር ወር 2016 ዓ.ም. ለኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ መሰጠቱን፣ የገንዘብ ሚኒስቴርም ለሚገነባው ሕንፃ ዲዛይን ሥራ የሚውል 60 ሚሊዮን ብር መመደቡን በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል።

ከተጠቀሰው አካባቢ ፊት ለፊት በሚገኘው ሥፍራ ባለ 15 ወለል ሕንፃ በዓመት 67 ሚሊዮን ብር የኪራይ ክፍያ የሚፈጽመው ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ለሕንፃ ግንባታ የሚሆነው መሬት እንዲሰጠው ከጠየቀ ረዥም ጊዜያት ማስቆጠሩን የተቋማዊ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አዱኛው አንዷለም በወቅቱ ለሪፖርተር መግለጻቸው አይዘነጋም።

ክፍለ ከተማው ለኮሚሽኑ መሬቱን እንደሚሰጥ ከተረጋገጠ በኋላ፣ በኅዳር ወር 2016 ዓ.ም. ጉዳዩ የሚመለከተው የቀበሌ አስተዳደር ቢሮ ለነዋሪዎች ይፋ ባደረገው ማስታወቂያ፣ የልማት ተነሺ በሚል የነዋሪዎቹን መረጃ በመሰብሰብ ከአካባቢው እንደሚነሱ አሳውቆም ነበር።

ይሁንና የቀበሌው አስተዳደር በጥር ወር 2017 ዓ.ም. ለነዋሪዎች በድጋሚ ይፋ ባደረገው አዲስ ማስታወቂያ፣ ከዚህ በፊት ‹‹ለኮሚሽን ቢሮ ግንባታ ልማት ተነሺ›› በሚል የነዋሪዎች መረጃ መሰብሰቡን በማስታወስ፣ ሆኖም ፕሮጀክቱ አሁን ተቀይሮ በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ማስፋፊያ የተካለለ በመሆኑ ነዋሪዎች መረጃቸውን በድጋሚ አደራጅተው ለወረዳው መሬት ልማት አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንዲያሳውቁ አሳስቧል።

ጉዳዮን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ሠራተኛ፣ ለነዋሪዎቹ የደረሰው መረጃ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

‹‹ውሳኔው የተላለፈው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው። በትክክልም ባለፈው ዓመት መሬቱ ለጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ እንዲውል በመወሰኑ፣ ነዋሪዎች ከአካባቢው ለልማት እንደሚነሱ ዓላማውንም አሳውቀን እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። አሁን ግን የከተማ አስተዳደሩ መሬቱ ለኦሮሚያ ባህል ማዕከል ማስፋፊያ ፕሮጀክት እንደሚፈለግና እንደገና መረጃ እንድናደራጅ ስላሳወቀን ይህንኑ እያደረግን ነው፤›› ሲሉ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ለልማት እንደሚነሱ ቀበሌው ያሳወቃቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ወር የመኖሪያ ሥፍራው ለልማት እንደሚፈለግና እንደሚነሱ ከተነገራቸው በኋላ፣ ከቀበሌ ቤት እስከ የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚንየም) ባለሁለት መኝታ ቤት ድረስ ፍላጎታቸውን የሚያሳውቅ ፎርም ጭምር ሞልተው እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በወቅቱ ለልማት ተነሺነትና ለትራንስፖርት ካሳ የሚውል 85,000 ብር ካሳ እንደሚከፈላቸው ተገልጾ የነበረ መሆኑን፣ አሁን ግን ባለፈው ዓመት ያስገቡትን ማስረጃ ቀርቶ እንደ አዲስ መረጃቸውን አደራጅተው ማስገባታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአስተዳደሩ በዋናነት የተጠየቁት ማስረጃም ለቀበሌ ቤት ነዋሪዎች የታደሰ ውል፣ የኪራይ ደረሰኝ፣ የታደሰ መታወቂያ፣ እንዲሁም ቤቱ በጋራ የተያዘ ከሆነ የጋራ መሆኑን ማረጋገጫና ውክልና ያላቸው ነዋሪዎችም ውክልናቸውን እንዲያቀርቡ ነው። የግል ይዞታ ያላቸው ነዋሪዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታና የግብር ደረሰኝ ማስረጃዎችንም እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል።

ስለጉዳዩ ሪፖርተር ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እናት፣ በአካባቢው ከእነዚህ በሁለት ጎራ ከተጠቀሱት ነዋሪዎች በተጨማሪ በጥገኝነት የሚኖሩ ብዙ መሆናቸውን በመጠቆም፣ በሁለቱ ጎራ ለተካተቱት ቤትና ካሳ በሚሰጥበት ወቅት ሜዳ ላይ እንዳይወድቁ በመሥጋት የኑሮ ሁኔታቸውን በመግለጽ ወረዳው የእነሱንም መውደቂያ ታሳቢ እንዲያደርግላቸው የሚጠይቅ ማመልከቻ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡