በጋዜጣዉ ሪፓርተር

March 9, 2025

https://www.ethiopianreporter.com/139080

በሃይማኖት ደስታ

ለአርሶ አደሮች 129 በመቶ የገቢ ዕድገት ያስገኘላቸው ዘመናዊ የግብርና አሠራር  በታሰበው ልክ እንዳይተገበር፣ ከላይ እስከ ታች ያለው የመንግሥት መዋቅር ክፍተት መፍጠሩ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የግብርና ሚኒስቴር ከጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ጋር በመተባበር የካቲት 26 እና 27 ቀን 2017 ዓ.ም ‹‹የተለያዩ የሼፕ አሠራሮች ንቅናቄ›› በሚል መሪ ቃል፣ በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ባካሄደው 11ኛው ‹‹በአነስተኛ ይዞታ ሆልቲካልቸር አምራች አርሶ አደሮችን ገበያ ተኮር የግብርና ዘዴ በማስተዋወቅ የማብቃት ፕሮጄክት (ኢትዮ ሼፕ) ዓለም አቀፍ ዓውድ ጥናት ላይ ነው።

በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብደላ ነጋሽ፣ አሠራሩ አርሶ አደሮች ከ2,000 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ያገኙ የነበረውን ዓመታዊ ገቢ፣ ከ13,072 ብር ወደ 29,773 ብር ወይም 129 በመቶ ከፍ እንዲልላቸው አድርጓል ብለዋል፡፡

ሆኖም ከላይ እስከ ታች ያለው የመንግሥት መዋቅር ይህን አሠራር ተቀብሎ ከመተግበር አንፃር ክፍተት እንደሚስተዋልበት የገለጹት አቶ አብደላ፣ ትግበራ ላይ እንቅፋት የሆነውን ችግር ለመፍታት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ገበያ ተኮር የግብርና ዘዴ በማስተዋወቅ፣ የማብቃት ፕሮጀክት (ኢትዮ­ ሼፕ)ን ከአገሪቱ የግብርና ኤክስቴንሽን ስትራቴጂ ጋር ለማዋሀድ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

በዓውደ ጥናቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በሚኒስቴሩ የእርሻና ሆልቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር)፣ መንግሥት በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ (እ.ኤ.አ ከ2020 እስከ 2030) በሆርቲካልቸር ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ግብርናውን ለማሳደግ እየሠራ ነው ብለዋል። ሆርቲካልቸር ምርትን አምርቶ ወደ ውጭ የመላክ አቅምን በማጠናከር፣ ድህነትን ለመቀነስና የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚን የማሳደግ አቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡  

በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በግብርና መስክ ዕድገት እንዲመጣ በማድረግ ረገድ ጃይካ ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ አጋርነት እንዳለው አስታውሰዋል፡፡ መለስ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በጃይካ ትብብር ኢትዮጵያ በገበያ ተኮር የኤክስቴንሽን አገልግሎቶች የምግብና የተመጣጠነ ምግብ ዋስትና፣ የአየር ንብረት ለውጥ መላመድና የግብርና መድኅን ድጋፍ አግኝታለች። ጃይካ አነስተኛ መሬት ባላቸው አርሶ አደሮች የሚተገበር የገበያ መር ግብርናን በመደገፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ፣ የበርካታ አርሶ አደሮች የኑሮ ሁኔታን የሚያሳድግ አሠራር ዘርግቷል ብለዋል፡፡  

ጃይካ በአቅም ግንባታ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎችንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በማሠልጠን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል። ለአርሶ አደሩ ተግባራዊ መፍትሔዎችን በማቅረብ በፖሊሲና በአፈጻጸም መካከል ያለውን ልዩነት በማስተካከል፣ በአነስተኛ ይዞታ ሆልቲካልቸር አምራች አርሶ አደሮችን ገበያ ተኮር የግብርና ዘዴ በማስተዋወቅ የማብቃት ፕሮጀክት (ኢትዮ ሼፕ)  አካሄድ ለውጥ ማምጣቱን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጃይካ ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ስለገበያ ተኮር ግብርና ጠቀሜታ የግንዛቤ ማስጨበጫና የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት፣ ወደ ትልቅ ቢዝነስነት እንዲሸጋገሩ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። 

በኢትዮጵያ የመጀመርያው የሼፕ አሠራር ትግበራ ምዕራፍ ከጀመረበት እ.ኤ.አ. ከ2017 እስከ 2023 ዓ.ም ከጃይካ ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደሚገኙም መለስ (ዶ/ር) አክለዋል። ‹‹አሁን ሁለተኛውን ምዕራፍ የሼፕ አሠራርን በአምስት ክልሎች  ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንገኛለን፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ መንግሥት በራሱ ሀብት በአዳዲስ አካባቢዎች ለአብነት ያህል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አሠራሩን እንዲተገበር እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።  ጃይካ ከአጭር ጊዜ ድጋፍ ይልቅ ዘላቂነት ያለው ተጠቃሚነትን ላይ መሠረት ማድረጉ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር እንድናደርገው አስችሏል ሲሉም አክለዋል።

የጃይካ ምክትል ፕሬዚዳንት ሂሮዩኪ ያማጉቺ በበኩላቸው፣ ጃይካ ከሚሠራባቸው የትኩረት መስኮች ዋነኛው የሆነው የሼፕ አሠራር፣ በጃፓንና በኬንያ መንግሥታት መካከል በተደረገ ቴክኒካዊ ትብብር አማካይነት፣ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ለማጠናከር በሚል ዓላማ እ.ኤ.አ. በ2006 በኬንያ ተግባራዊ መደረግ እንደጀመረ አውስተዋል። ይህ አሠራር የአነስተኛ አርሶ አደሮችን ገቢ በእጥፍ ያሳደገው የ‹‹ማደግና መሸጥ›› አስተሳሰብን ወደ ‹‹መሸጥ ለማደግ›› በመቀየር ነው እንደሆነ ጠቁመዋል።

ጃይካ ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲመዘገብ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል። 

ጃይካ ከሚሠራባቸው የትኩረት መስኮች አንዱ የሆነው፣ ‹‹በአነስተኛ ይዞታ ሆልቲካልቸር አምራች አርሶ አደሮችን ገበያ ተኮር የግብርና ዘዴ በማስተዋወቅ የማብቃት ፕሮጄክት›› (ኢትዮ ሼፕ) አሁን በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በላቲን አሜሪካ በሚገኙ 60 አገሮች በትግበራ ላይ እንደሚገኝ ሂሮዩኪ ገልጸዋል።

የሼፕ አሠራርን የተመለከቱ ያለፉ ዘጠኝ ዓውደ ጥናቶች በደቡብ አፍሪካ፣ ያለፈው ዓመት ደግሞ በኬንያ መደረጉን ያወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ችሏል ብለዋል። የሼፕ አሠራር አነስተኛ ግብርናን በመደገፍና በማስተዋወቅ በአፍሪካ የግብርናው ዘርፍ እንዲያድግ እየሠራ እንደሚገኝ ያነሱት ሂሮዩኪ፣ አገሮች ከዓውደ ጥናቱ ያገኙትን ተሞክሮ በአገራቸው እንዲተገብሩ አሳስበዋል፡፡

የሼፕ አሠራር በአፍሪካ የግብርና ዕድገት እንዲመዘገብ የሚያስችል አንዱ ምሰሶ ነው ያሉት ደግሞ፣ ‹‹የሼፕ አሠራር ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የመስፋፋት ሒደት›› በሚል ጭብጥ ላይ ሪፖርት ያቀረቡት በጃይካ የኢኮኖሚና ልማት ዲፓርትመንት ከፍተኛ አማካሪ ሃሩይ ኪታጂማ ናቸው።

እ.ኤ.አ. በ2030 አንድ ሚሊየን ለሚሆኑ በአነስተኛ ይዞታ የግብርና ምርት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ማስቻልን ዓላማ በማድረግ ኬንያና ማላዊን ጨምሮ የሼፕ አሠራር የጋራ ስምምነት የፈረሙ ሌሎች አገሮች እየሠሩ ናቸው ብለዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብደላ ነጋሽ በበኩላቸው፣ ‹‹በኢትዮጵያ የሼፕ አሠራር ትግበራ አሰፍላጊነት›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንዱ የጀርባ አጥንት መሆኑን በመጥቀስ፣ በተለይ ከ90 እስከ 95 በመቶ የሚሆነው የሆልቲካልቸር ምርት ከአነስተኛ አምራች አርሶ አደሮች የተውጣጣ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሼፕ አሠራር በመጀመሪያ ምዕራፍ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ለተከታታይ ስድስት ዓመታት መተግበሩን ያወሱት አቶ አብደላ፣ አሠራሩ ውጤት እንደሚያመጣ በመረጋገጡ ሁለቱ ክልሎች እንዳሉ ሆኖ አሁን ላይ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ፣ ሲዳማና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በማስፋፋት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት (እ.ኤ.አ. ከ2023 እስከ 2028) ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል። 

‹‹አርሶ አደራችን ይህ አሠራር ከመተግበሩ በፊት ባልተጠና መንገድ ለብቻው አምርቶ መሸጥን ሲከተል ነበር፤›› ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፣ አሁን ግን ለመሸጥ ማምረትን እየተገበረ ነው ብለዋል። ይህ ማለት አርሶ አደሩ በመጀመሪያ ወደ ገበያ ሄዶ ገበያው ምንድን ነው የሚፈልገው ነገር? የሚለውን በራሱ አጥንቶ፣ በራሱ ያመርታል። መጨረሻ ላይ ደግሞ በጋራ ይሸጣል፣ በዚህ መንገድ እየተጠቀመ ይገኛል ብለዋል።

በሼፕ አሠራር የመጀመሪያው ምዕራፍ የታቀፉ አርሶ አደሮች ከ2,000 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ያገኙ የነበረውን ዓመታዊ ገቢ ከ13,072 ብር ወደ 29,773 ብር ከፍ እንዲልላቸው ማድረጉንም አመልክተዋል። ይህም አርሶ አደሮች የሼፕ አሠራርን መተግበራቸው የ129 በመቶ የገቢ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ አስችሏል ብለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 2024 አንስቶ መንግሥት ሀብት በመመደብ የራሱን ቁርጠኝነት ወስዶ አሠራሩን እንዲተገበር እያደረገ እንደሚገኝ አክለዋል። ከዚሁ በመነሳትም የግብርና ሚኒስቴር በተያዘው ዓመት በትግራይ ክልል አሠራሩን ለማስጀመር ማቀዱን አስረድተዋል።

አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች እየተተገበረ የሚገኘውን ገበያ መር የሆርቲካልቸር ልማት የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት (ኢትዮ ሼፕ)ን የኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን ስትራቴጂ ጋር ለማዋሀድ እየተሠራ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው በዚህ ወቅት ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ውይይቶችም እየተደረጉ እንደሆነ አመልክተዋል። ይህም የሁለተኛው ምዕራፍ ትግበራ ሲጠናቀቅ የሼፕ አሠራርን በአገሪቱ ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል።

የካቲት 26 እና 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ በተካሄደው 11ኛው በአነስተኛ ይዞታ ሆልቲካልቸር አምራች አርሶ አደሮችን ገበያ ተኮር የግብርና ዘዴ በማስተዋወቅ የማብቃት ፕሮጀክት (ኢትዮ ሼፕ)፣ ዓለም አቀፍ ዓውደ ጥናት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከታንዛኒያ፣ ከናይጄሪያ፣ ከማላዊና ከሲሪላንካ የመጡ ተሳታፊዎች በየአገራቸው እየተተገበረ ስላለው የሼፕ አሠራርና ስለተገኙ ውጤቶች እንዲሁም መሻሻል ስላለባቸው ጉዳዮች ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል። ተሳታፊ አገሮችም የፕሮጀክት ትግበራ ዕውቀትና ልምድ ልውውጥ ማድረጋቸው በዓውደ ጥናቱ ወቅት ተነግሯል፡፡