
ማኅበራዊ የመሬት መንቀጥቀጥ ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ በተዘረጋው መንገድ ላይ አደጋ መደቀኑ ተገለጸ
ቀን: March 9, 2025
የኢትዮጵያ የገቢና የወጪ ንግድ የሚተላለፍበት ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋው መንገድ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ መተሃራ አካባቢ ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችልና አደጋ መደቀኑ ተነገረ፡፡
በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ተመራማሪ አቶ ናትናኤል አገኘሁ እንደተናገሩት፣ ፈንታሌ ተራራ ላይ በተደጋጋሚ እየተከሰተ በሚገኘው የመሬት መንቀጥቀጥ የማግማ ወይም ቅልጥ አለት ወደ ላይኛው የመሬት ክፍል እየተጠጋ መሆኑን ኢንሳር (INSAR) በተሰኘ የራዳር ቴክኖሎጂ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህ በመሆኑም የእሳተ ጎመራ ፍንዳታ ከተከሰተ ከጂቡቲ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ መተሃራ አካባቢ ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል ብለዋል፡፡
ማግማው ወይም ቅልጥ አለቱ ፈንድቶ በመንገዱ ላይም ሆነ በሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት፣ ሦስት ተለዋጭ መንገዶች እንዲገነቡ ለኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክረ ሐሳብ መቅረቡን ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ናትናኤል፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራውና የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋውን ለመከላከልና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ ጂኦሎጂካል ሰርቬይና የአደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በተገኙበት ምክረ ሐሳብ ከሁለት ወራት በፊት ቀርቧል፡፡
‹‹መተሃራ የመሬት መንቀጥቀጡ እየተከሰተ ለሚገኝበት ሥፍራ በጣም የቀረበ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚተላለፍበት የጂቡቲ አዲስ አበባ፣ እንዲሁም ከጅግጅጋ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ የሚገኝበት አካባቢ በመሆኑ እጅግ ጥንቃቄ ይፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
ተመራማሪው፣ ተለዋጭ መንገድ እንዲገነባ ከቀረበው ምክረ ሐሰብ በተጨማሪ፣ መንግሥት ትልልቅ የሚባሉ ኢንቨስትመንቶችንና መሠረተ ልማቶችን በሥፍራው እንዳያካሂድ፣ ግድብና ሌሎች በመከናወን ላይ የሚገኙ ግንባታዎች ለጊዜው እንዲቆሙ ሐሳብ መቅረቡንም አክለዋል፡፡
በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት አዲስ እንዲገነቡ ምክረ ሐሳብ በቀረበባቸው ሦስት የመንገድ ዲዛይኖች ላይ ሪፖርተር አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ሲስተም ማኔጅመንት ዳይሬክተር ዮሴፍ ታምሩ (ኢንጂነር)፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ተቋሙ ምላሽ መስጠት እንደማይችልና መረጃ ማግኘት የሚቻለው ከተዋቀረው ኮሚቴ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡