https://www.ethiopianreporter.com/139069/

ዜና በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የቀድሞ ተዋጊዎችን ማቋቋም ሰሞኑን እንደሚጀመር ተነገረ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: March 9, 2025

በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የቀድሞ ተዋጊዎችን የመልሶ ማቋቋምና ወደ ኅብረተሰብ የመቀላቀል ሥራ፣ በዚህ ሳምንት መጨረሻ እንደሚጀመር ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ከአንድ ወር ከ15 ቀናት በላይ በተለያዩ በቴክኒክ ጉዳዮች፣ በክልሉ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ፣ እንዲሁም ትጥቅ የመፍታትና የመሣሪያ አያያዝ ላይ ዝርዝር ነገሮች ቀድመው ባለመሠራታቸው፣ እስኪስተካከሉ ቆሞ እንደነበር የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይሁን አንጂ በተያዘው ሳምንት አጋማሽ ወይም መጨረሻ አካባቢ ሥራ እንደሚጀመር አረጋግጠዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የቀድሞው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የነበሩትን  ጃል ሰኚ ነጋሳን ጨምሮ፣ በርካታ የታጣቂ ቡደኑ አባላት መለስተኛ የተሃድሶ ሥልጠና በአዋሽ እንዲወስዱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል የርዕስ መስተዳድሩ የሰላምና ደኅንነት አማካሪ ሆነው የተሾሙትን ጃል ሰኚን ጨምሮ፣ በክልሉ ከ4,000 በላይ የታጣቂው ቡድን አባላት በዚያ መንገድ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን አክለው ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል የመልሶ መቋቋም ሥራ ቆሞ በነበረበት ወቅት በአፋር፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ተመሳሳይ ሥራ ሲከናወን መቆየቱን የገለጹት ኮሚሽነር ተመስገን፣ በአማራ ክልል የመንግሥትን ጥሪ ለተቀበሉ የፋኖ፣ የአገውና የቅማንት ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋምና የመቀላቀል ሥራ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ከመጋቢት እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም. ባሉት ወራት የትግራይ ክልል 67 ሺሕ የቀድሞ ታጣቂዎች ጨምሮ፣ በአምስት ክልሎች ወደ 75 ሺሕ ታጣቂዎችን ወደ ኅብረተሰቡ ለመቀላቀል ይሠራል ብለዋል፡፡ እስካሁን ድረስ 17 ሺሕ ታጣቂዎችን በማቋቋም ወደ ኅብረተሰቡ መቀላቀል መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል ካለው የፀጥታ ችግር አንፃር አስቻይ ሁኔታ አለ ብሎ ደፍሮ መናገር አይቻልም ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በዚሁ ክልል በርካታ ታጣቂዎች ለመንግሥት ምላሽ እየሰጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በስምንት ክልሎች ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የመልሶ ማቋቋምና የተሃድሶ ሥራ፣ መንግሥትን የተዋጉ ከ371,971 የቀድሞ ተዋጊዎችንና ከውጊያ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የነበራቸውን ግለሰቦች ብቻ እንደሚያካትት መገለጹ ይታወሳል፡፡ ለዚህም ከ760 ሚሊዮን በላይ ዶላር እንደሚያስፈልግ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡