
https://www.ethiopianreporter.com/139059
March 9, 2025
በሃይማኖት ደስታ
በኢትዮጵያ የተለያዩ የሆርቲካልቸር ፓርኮች ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲቋቋሙ የሚያደርግ ስትራቴጂ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ተገለጸ፡፡
ረዥም ጊዜ ወስዶ የተከለሰው አገር አቀፍ የሆርቲካልቸር ስትራቴጂ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ በርካቶች ጥሩ አቅም የሚፈጥር መሆኑን፣ በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብደላ ነጋሽ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
አቶ አብደላ እንደተናገሩት፣ ስትራቴጂው በአነስተኛ ይዞታ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አርሶ አደሮችንና ሌሎች አካላትን የበለጠ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ነው። ‹‹ይህም ለአገራችን ትልቁ ማነቆ የሆነባት የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ችግርን ለመቅረፍ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚሁ ጋር ተያይዞ የባህር በር የለንም ብለን የምናስበውን ወደ ልማት ከቀየርንና ከሠራን፣ ያንን ታሪክ የሚቀይር አንዱ ንዑስ ዘርፍ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው አገር አቀፍ የሆርቲካልቸር ስትራቴጂ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀው፣ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን በመደገፍና የላቀ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደነበር ያወሱት አቶ አብደላ፣ በአሁኑ ጊዜ የግሉ ዘርፍ በስፋት ወደ ዘርፉ ገብቶ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በዘርፉ የተለያዩ የሥራ ዕድል ተነሳሽነቶች መምጣታቸው የበፊቱን ስትራቴጂ እንደገና እንዲከለስ ምክንያት ሆኗል ያሉት አቶ አብደላ፣ ሲተገበር የቆየው ስትራቴጂ በሆርቲካልቸር ዘርፍ የግል ዘርፉ ሲሳተፍ መንግሥት እንዴት ይደግፋል የሚለው አሠራር ግልጽ እንዳልነበረ አስረድተዋል። ‹‹የተሻሻለው ስትራቴጂ ይህን ጉድለት ሊቀርፍ የሚችል ነው ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በአንድ ማዕከል ላይ እነዚህ ጉዳዮች መምጣታቸው ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የዕውቀትና የክህሎት ሽግግር፣ እንዲሁም ጥራትን መሠረት ያደረገ የአመራረት ዘዬ ጋር ተያይዞ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል ብለን እንጠብቃለን፤›› ሲሉም መሪ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
በዘርፉ የዕውቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲመጣ ከተፈለገ የግል ሴክተሩን በሚገባ መደገፍና ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ አቶ አብደላ ተናግረዋል። በአነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች ብቻ በማምረት ከሌሎች አገሮች ጋር መወዳደር ስለማይቻል የሌሎች አካባቢ ዕውቀቶች፣ ክህሎቶችና ኢንቨስትመንቶች ወደ ክልላቸው በመሳብ ኢንቨስተሮችን መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል። ‹‹በተለይ ከመሬት ጋር ተያይዞ ኢንቨስተሮች ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ከተቻለ፣ እርግጠኛ ነኝ ሁሉም ክልሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለን እንጠብቃለን፤›› ሲሉ አቶ አብደላ ተናግረዋል። በተለይ ለግል ዘርፉ አስቻይ ሁኔታዎች ከመፍጠር አኳያ ስትራቴጂው ዕገዛ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
የግል ሴክተሩ በዘርፉ ከዕውቀትና ከህሎት ጋር ተይይዞ ያለውን ችግር የሚፈታበት ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ለማስቻል ለመጀመሪያ ጊዜ የተለያዩ የሆርቲ ፓርኮች ይቋቋማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። በአማራ ክልል ቁንዝላ ከተማ ውስጥ አንድ የሆርቲ ፓርክ ለማቋቋም ተሞክሮ እንደነበር የገለጹት አቶ አብደላ፣ በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሚፈለገው ልክ አልሄደም ብለዋል። ‹‹አሁን ግን ሆርቲ ፓርክ ያመጣውን ለውጥ የምናይበት ጊዜ ይሆናል፤›› ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፣ ነገር ግን በፀጥታ ችግር ምክንያት ሊሆን አልቻለም ብለዋል።
ከዚህ በሻገር ኢትዮጵያ 32 የአግሮ ኢኮሎጂ ዞኖች እንዳሏት የጠቀሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህም አገሪቱ ምንም ማምረት የማትችለው ነገር እንደሌለ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ አቶ አብደላ ገለጻ፣ በዘርፉ በተለይ ጥራት ላይ መሠረት በማድረግ በአገር ውስጥ አምርቶ ወድ ውጭ መላክ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሌሉ የአትክልትና ፍራፍሬና ሌሎች የሰብል ዓይነቶችን ወደ አገር ውስጥ አምጥቶ የማላመድና የማስፋፋት ሥራዎችን ለማናወን ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ስትራቴጂው ከወራት በፊት ተፈጻሚ እንዲሆን መታሰቡን የጠቀሱት አቶ አብደላ፣ አሁን የተሻሻለውን ስትራቴጂ ለተጠቃሚዎች ይፋ ማድረግ ይቀራል ብለዋል። እንደ አቶ አብደላ ገለጻ፣ ስትራቴጂውን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግ እንደሚቻልም አያይዘዋል።
የግብርና ሚኒስቴር የተለያዩ ፕሮጄክቶችንና ፕሮግራሞችን በመንደፍ ስትራቴጂው መሬት ላይ የሚወርድበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ተብሎም ይታመናል ሲሉም አክለዋል።
አገር አቀፍ ስትራቴጂው ሲዘጋጅ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳለፍ እኩል ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል መንገዱ መቀረፁን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸው፣ ክልሎችም ከየክልላቸው ተጨባጭና ዕምቅ አቅም ጋር የተያያዘ የራሳቸውን ስትራቴጂ መንደፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።
የተከለሰው አገራዊ ስትራቴጂም ክልሎች ይከተሉት የነበረውን አሠራር የሚያሻሽሉበትና ወደ መሬት የሚያወርዱበት ዕድል ይፈጥራል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ የስትራቴጂው ዋና ፈጻሚዎች ክልሎች እስከሆኑ ድረስ ለተፈጻሚነቱ ባለቤት ሆኖ መንቀሳቀስ አለባቸው ብለው እንደሚያምኑ ያወሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፣ ለአሠራሩ የሚያስፈልገውን ሀብት በራስ ከመመደብ አንስቶ ከሌሎች አጋር አካላት በማፈላለግ ወደ ተፈጸሚነቱ ከመግባት ጋር ተያይዞ ሰፊ ሥራ ማከናወን አለባቸው ብለዋል፡፡
ስትራቴጂውን በዘርፉ ለመሰማራት የሚሹ በርካታ የልማት አካላት እንደሚፈልጉት የጠቆሙት አቶ አብደላ፣ ወደ መሬት ማውረድ ላይ ቢሠራ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ተብሎ ይታመናል ሲሉም ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ የአንድ አካባቢ ልማትና ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው ያሉ አቶ አብደላ፣ ማኅበረሰቡ ከሰላም ጎን መቆም አለበት ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በክልሎች የሆርቲካልቸር ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ተብሎ በስፋት የማምረት እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
‹‹ለምሳሌ በአማራ ክልል ብቻ በርካታ ቶን የአቮካዶ ምርት ይላካል ተብሎ ዕቅድ ተይዞ፣ እንዲያውም በገበያው ረገድ በርካታ ጥያቄዎች ለሚኒስቴሩ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ሆኖም ጥያቄ ያቀረቡ አካላት የፀጥታ ችግሩን በመፍራት ክልሉ ውስጥ ገብተው ለመሥራት አልደፈሩም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሆኖም የተወሰነ መላክ ተችሏል፣ ነገር ግን በሚጠበቀው ልክ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚጎዳው ማኅበረሰቡን ነው፤›› ሲሉም አክለዋል። ‹‹ይህም የክልሉን የመልማት ዕድል ሊያቀጭጨው ይችላል ብለን እናምናለን፡፡ የመልማት ዕድልን እያጠናከሩ ለመቀጠል የሰላሙ ሁኔታ አሁንም መሻሻል አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመንግሥት ብቻ መጠበቅ ሳይሆን ትልቁን አስተዋጽኦ ማድረግ ያለበት ማኅበረሰቡ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ሆርቲካልቸር በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ምርትን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት፣ እንዲሁም የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጋር ተያይዞ ለአገሪቱ የራሱን የሆነ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ንዑስ ዘርፍ ነው ሲሉ ያወሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው ቡናና ሻይ፣ አበባ፣ ድንች፣ የእንሰት ምርት ከፍተኛ ገቢ ከሚገኝባቸው የሆርቲካልቸር ምርቶች መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸዋል።