
https://www.ethiopianreporter.com/139062/
የፍትሕ ሚኒስትሯ ሃና አርዓያ ሥላሴ
ዜና ‹‹የፕሪቶሪያ ስምምነት የተሳካ አፈጻጸም መንግሥት ለሰላምና ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ…
ቀን: March 9, 2025
‹‹መሬት ላይ ምንም የተፈጸመ ነገር የለም››
የትግራይ ክልል
‹‹የፕሪቶሪያ ስምምነት የተሳካ አፈጻጸም የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም፣ ለሰብዓዊ መብቶችና ለኢትዮጵያውያን መበልፀግ ያለውን ያልተገደበ ቁርጠኝነት ማሳያ ነው፤›› ሲሉ የፍትሕ ሚኒስትሯ ሃና አርዓያ ሥላሴ ገለጹ፡፡
የፍትሕ ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት በጄኔቫ ስዊዘርላንድ እየተካሄደ ባለው፣ እ.ኤ.አ. እስከ መጪው ሚያዝያ 4 ቀን 2025 በሚቀጥለው የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ግምገማ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ ነው፡፡
ሚኒስትሯ በንግግሯቸው በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት ታጣቂዎች መካከል የተካሄደውን ጦርነት እንዲቆም ያደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት፣ ‹‹ስኬታማ አፈጻጸሙ የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድና ከዚያም ያለፉ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ላለው ቁርጠኛነት ምስክር ነው፤›› ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2025 እ.ኤ.አ. እስከ 2027 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ አባል ሆና የተመረጠችው ኢትዮጵያ በሚኖራት የአባልነት ጊዜ፣ የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ምልዑነት መጠበቅ ላይ ትኩረት በማድረግ አንደምትሠራ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሯ በጄኔቫ ንግግራቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶችን በማሳደግ፣ ሕግና ሥርዓትን በማስጠበቅ፣ እንዲሁም አገራዊ ዕርቅን ለማረጋገጥ የተሠራውን ሥራ ስናገር የደስታ ስሜት ይሰማኛል፤›› ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ሃና የፕሪቶሪያ ስምምነት ስኬታማ ነው ይበሉ እንጂ፣ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክር ቤት የፕሪቶሪያ ስምምነት ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የባይቶና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ በርኸ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹መሬት ላይ ምንም የተፈጸመ ነገር የለም›› ብለዋል፡፡ ተኩስ መቆሙ ስምምነቱ ስኬታማ ነው? አይደለም? ለሚለው ጉዳይ አከራካሪ ይሆናል ብለዋል፡፡
‹‹የጦርነቱ መንስዔ ያልሆኑ መሠረተ ልማቶች በተለይም እንደ ኤሌክትሪክና ኢንተርኔት ከመለቀቁ ውጪ ዋነኞቹ ጥያቄዎቹ ግን አልተመለሱም፡፡ ከመጀመሪያ ጀምሮ በስምምነቱ መሠረት አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ሊቋቋም ሲገባው፣ ሁሉንም ሥልጣን ለሕወሓት መሰጠቱ አንዱ የስምምነቱ አፈጻጸም ስህተት ነው፤›› ያሉት አቶ ዮሴፍ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚያ መንገድ የተመሠረተ ባለመሆኑና ስምምነቱ ባለመተግበሩ በክልሉ ላይ አደጋ እየተፈጠረ መሆኑን አክለዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት መፈጸም የነበረባቸው በተለይም ግዛታዊ አንድነትና ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ አለመከናወኑን የተናገሩት ሰብሳቢው፣ ይህንን ሥራ ለማከናወን ከአገር መከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ የኤርትራ ሠራዊትና የአማራ ክልል ታጣቂዎች፣ ከትግራይ ክልል መውጣት የነበረባቸው ቢሆንም አሁንም በክልሉ መኖራቸው ለስምምነቱ አለመፈጸም ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ስምምነቱ የተወሰኑ ጅማሬዎች የነበሩት ቢሆንም አሁን በተገቢው መንገድ እየተፈጸመ ባለመሆኑ፣ ተኩስ መቆሙን ካልሆነ በስተቀር በስምምነቱ መሠረት የተደነገጉ ጉዳዮች ገና አንድ ብለን ለመጀመር እየተንቀሳቀስን ነው፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ዮሴፍ በማብራሪያቸው ከሰሞኑ የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ተከትሎ ለመምራትና ለማስፈጸም ምክር ቤቱ የተቋቋመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም. በዚሁ ጉባዔ በኢትዮጵያ ላይ ባቀረበው መግለጫ፣ በትግራይ ክልል በኤርትራ ወታደሮች የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያሳስበኛል ብሎ ነበር፡፡
በተመሳሳይ በዚሁ መድረክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ባቀረበው መግለጫ፣ የኤርትራ ወታደሮች የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የቆመበትን የፕሪቶሪያ ስምምነት እየጣሱ መሆናቸውን ጠቅሶ ከአካባቢው እንዲወጡ ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡